Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል ሕገወጥ ግድያዎችና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በአሳሳቢ ሁኔታ መቀጠላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በአማራ ክልል ሕገወጥ ግድያዎችና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች በአሳሳቢ ሁኔታ መቀጠላቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

  • ከ200 በላይ ሴቶች መደፈራቸውንና በድሮን ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ገልጿል

በአማራ ክልል ለወራት በቀጠለው ግጭት የአስገድዶ መድፈር ወንጀልና ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ግድያ ተባብሶ መቀጠል እንዳሳሰበው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡

ኮሚሽኑ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዓይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችንና የተጎጂ ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማሰባሰብ አጠናከርኩት ያለውን ሪፖርት ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

በግጭቱ ዓውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ መሆናቸውን ገልጾ፣ በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደርጎ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡ ከተደፈሩ ሴቶች መካከል የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከ ወጣበት ቀን ድረስ ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት መመዝገባቸውን ጠቅሶ፣ ከተጎጂዎች መካከል የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ሴቶችና የጤና ባለሙያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ብሏል።

በሪፖርቱ እንደተመላከተው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት እንደተካሄደባቸው፣ የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያና አልፎ አልፎም በአየር የድሮን ድብደባ የታገዘ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በግጭቱ ሳቢያ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳት በመድረሱ ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ መገደዳቸውን የሚያብራራው መግለጫው፣ ለአብነትም በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ መጥተህ ብላ ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት፣ የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር አሁን ባለበት ሁኔታ ማወቅ እንደማይቻል፣ የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ ዳይሬከተር ታሪኳ ጌታቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ደግሞ ቢያንስ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ የአካባቢው ነዋሪዎችና የዓይን ምስክሮችን ዋቢ ማድረጉን በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትና ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ጠቅሶ፣ ከምንጃር አውራ ጎዳና ጎጥ 3,000 ያህል ነዋሪዎች በአንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ በዛፍ ሥር ተጠልለው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ቁጥራቸው ያልታወቀ ሌሎች ዜጎች መተሐራና አዋሽን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መፈናቀላቸውን ጠቁሟል፡፡

የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደወደመ፣ ንብረታቸው እንደተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣራያና በር እየተነቀለ መወሰዱን ገልጿል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤቶቻቸው ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደተጀመረ የኮሚሽኑ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከየትኛው አጎራባች ክልል የመጡ ናቸው በማለት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ ዳይሬክተሯ፣ የመጨረሻው ምርመራ ባለመጠናቀቁ መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

በመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሁንም መቀጠላቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎችን ኮሚሽኑ እየተቀበለ መሆኑን ገልጿል፡፡ ግጭቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች የመንግሥት የፀጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ ‹‹ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምፅ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ…›› በሚሉና እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን በኮሚሽኑ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡

በባህር ዳር ከተማ ሰባታሚት አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን አዴት ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሲቪል ሰዎች፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢያንስ ስምንት ሰላማዊ ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ መረዳቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ግንደወይን ከተማ ሞጣ በር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም. አንድ በጥይት የቆሰለን ግለሰብ እናቱና እህቱ በባጃጅ አሳፍረው ወደ ሕክምና ተቋም በመውሰድ ላይ እያሉ፣ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ባጃጁን አስቁመው ሁሉንም ተሳፋሪዎች ካስወረዱ በኋላ ‹‹የቆሰለው እኛን ሲዋጋ ነው›› በሚል ምክንያት የባጃጅ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራቱም ሰዎች በጥይት ስለመገደላቸው መረጃ ማሰባሰቡን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አካቷል፡፡

በባህር ዳር፣ በፍኖተ ሰላም፣ በጎንደርና በወልድያ ከተሞች በትጥቅ ግጭት ቆስለው ሕክምና ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ሰላማዊ ሰዎችና የታጣቂ ቡድን አባላት የመንግሥት የፀጥታ አካላት መሆናቸው በተጠረጠሩ ሰዎች ሕክምናቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ወዳልታወቀ ሥፍራ ከተወሰዱ በኋላ፣ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ወደ ሕክምና ተቋማቱ ሲመለሱ ቀሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ መግለጫው እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጥ አለመቻሉን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና ዕገታዎች በታጠቁ ኃይሎች መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሶ፣ ለምሳሌ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከባህር ዳር ወደ ደብረ ታቦር ሲሄዱ አለምበር ከተማ አካባቢ በታጣቂዎች መገደላቸውን በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...