የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን፣ ጋሻው ላፄ የተባሉ የፓርቲው አባል በአሰቃቂ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉበትና 28 አባላት እንደታሰሩበት አስታወቀ፡፡ የ24 ዓመቱ ወጣት የኢዜማ አባል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በዛይሴ ልዩ ወረዳ ምርጫ ክልል የነቃ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደነበራቸው ፓርቲው ገልጿል፡፡
ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ የኢዜማ አባል የሆኑት አቶ ጋሻው በግለሰቦች መካከል የተነሳ አለመግባባትን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች ባደረሱባቸው ኢሰብዓዊና አሰቃቂ ድብደባ ምክንያት፣ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕይወታቸው ማለፉን ኢዜማ አስታውቋል፡፡

ድብደባ መገደላቸው
የተነገረው የኢዜማ አባሉ
ጋሻው ላፄ
ስለግለሰቡ አሟሟት ተጨማሪ ማብራሪያ የተጠየቁት የፓርቲው የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ፣ ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ጉዳዩ ለፓርቲው እንደደረሰው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩን በራሳችን መንገድ ማጣራት ነበረብን›› ያሉት አቶ ዋስይሁን፣ ‹‹ካጣራን በኋላ ለኢሰመኮ፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለሚመለከታቸው በደብዳቤ አሳውቀናል፤›› ብለዋል፡፡
ሟቹ ገና ቤተሰብ ያልመሠረቱ የ24 ዓመት ወጣት የኢዜማ አባል መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ዋስይሁን፣ ለገላጋይነት በተጠሩ ፖሊሶች ድብደባ ለሞት እንደበቁ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድ ቤት ውስጥ በተፈጠረ የግል ፀብ መነሻነት የተጋጯቸው ሰዎች ፖሊሶችን ጠሩ፡፡ እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች ግን ጉዳዩን በመገላገል ወደ ሕግ ቦታ መውሰድ ሲገባቸው ወደ ድብደባ ነው የገቡት፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ዋስይሁን አክለውም፣ ‹‹ሟቹ አቶ ጋሻው በፀጥታ ኃይሎች በደረሰባቸው ኢሰብዓዊ ድብደባ የአርባ ምግጭ ሆስፒታል ጭምር ማረጋገጫ ሰጥቷል፤›› ብለው፣ ግለሰቡ በአሰቃቂ ድብደባ መሞታቸውን ያረጋግጣል ያሏቸውን የፎቶግራፍ ማስረጃዎችንም ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡
በሚዲያ ይፋ ለማድረግ ለዕይታ አሰቃቂ በሆኑት በእነዚህ ፎቶግራፎችም ሟቹ በአካላቸው የተለያዩ ክፍሎች ላይ ድብደባ እንደደረሰባቸው ለማየት ተችሏል፡፡ በአንገታቸው ላይ ቁስለት የሚታይ ሲሆን፣ አቶ ዋስይሁን በሥለት የመወጋት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢዜማ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዋስይሁን በተጨማሪ የሟቹን ግለሰብ ሁኔታ ይከታተሉ የነበሩ 28 የኢዜማ አባላት፣ የቀበሌ አጥር በድንጋይ ደብድባችኋል ተብለው መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአካባቢው እንደ አጋጣሚ ለሥራ በአካል ስለነበርኩ ሁኔታውን ሄጄ ታዝቤያለሁ፡፡ በድንጋይ ተመታ የተባለውን የቀበሌ ጽሕፈት ቤት በአካባቢው ካሉ የምርጫ ቦርድ ሰዎች ጋር ተመልክቼያለሁ፡፡ ደረሰ የተባለው ጉዳት ቀላል ነው፤›› ሲሉ ለ28 አባላት መታሰር መነሻ ነው የተባለውን ምክንያት ገልጸዋል፡፡
እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ከታሰሩት መካከል 15 ሰዎች መፈታታቸውን አቶ ዋስይሁን ጠቁመዋል፡፡ በአሰቃቂ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች ለተገደሉት አባላቸው በአስቸኳይ ፍትሕ እንዲሰጥና ያላግባብ የታሰሩ የፓርቲው አባላት እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡