Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡናን በቱሪስት መዳረሻዎች በውጭ ምንዛሪ ለመሸጥ የሚያስችል መመርያ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኤክስፖርት ደረጃ እሴት የተጨመረበት ቡና በአገር ውስጥ በቱሪስት መዳረሻዎችና በተመረጡ ቦታዎች፣ በውጭ ምንዛሪ ለመሸጥ የሚያስችል መመርያ ተዘጋጅቶ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችል ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች እየተጠበቁ ነው፡፡  

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያዘጋጀው መመርያ፣ ጥሬ ቡናን ቆልቶ ወይም ፈጭቶ ወደ ውጭ አገር ለመላክ፣ የላኪነት የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው አካላት የሚሰማሩበት የንግድ ሥርዓት መሆኑን ያስታውቃል፡፡

ቡናን በቱሪስት መዳረሻዎች በውጭ ምንዛሪ ለመሸጥ የሚያስችል መመርያ ተዘጋጀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በመመርያው መሠረት ቡናው የሚሸጠው ለውጭ አገር ጎብኚዎችና መንገደኞች፣ ኢምባሲዎች፣ ለዓለም አቀፍና ለአኅጉር አቀፍ ስብሰባዎች ተሳታፊዎች ነው፡፡

ግብይቱ በተፈቀዱ ቦታዎች ብቻ የሚፈጸም ሲሆን፣ ገዥው ክፍያውን የሚፈጽመው በክሬዲት ካርድ ወይም በሌሎች የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ አማራጮች መሆን እንዳለበት በመመርያው ተደንግጓል፡፡ ግብይቱ በጥሬ ገንዘብ ሊከናወን የሚችለው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቁጥጥርና ክትትል የእያንዳንዱን ሽያጭ ክፍያ ሲያረጋግጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የግብይት ሥፍራዎች የሚከፈቱት በዋናነነት በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማለትም በሆቴሎችና ሞቴሎች፣ በሎጆች፣ በፔንሲዮኖች፣ በካፌዎች፣ በኤርፖርቶች፣ በቱሪስት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የሁነት ማዘጋጃ እንደሚሆን መመርያው ያስረዳል፡፡

በቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ማስታወቂያ ክፍል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ገለታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዚህ ሥራ የሚሳተፉ አካላት ቀድሞውንም ቡናን ቆልቶ ወይም ፈጭቶ ወደ ውጭ የመላክ ፈቃድ ያላቸውና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፈቃድ የተሰጣቸው መሆን አለባቸው፡፡

ለመመርያው መውጣት አስገዳጅ የሆነውን ምክንያት ሲያብራሩ፣ የኢትዮጵያን ቡና ገዝተው ወደ አገራቸው መውሰድ የሚፈለጉ የውጭ ዜጎች ፍላጎትና ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት፣ የቡና ምርት እሴት ጨምሮ ለመሸጥ በሚል ዕሳቤ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ የውጭ ዜጎች እሴት የተጨመረበትን ቡና ከኢትዮጵያ ይዘው ሲወጡ፣ ከገዙበት ቦታ አስገዳጅ የሆነ ሕጋዊ ደረሰኝ ተቀብለው ማሳየት አለባቸው ተብሏል፡፡

እሴት የተጨመረበት ቡና ገዝተው የሚሸጡ አካላት ሕጋዊ ዕውቅና ካለው ቡና ሻጭ የመግዛት ግዴታ እንዳለባቸው በመመርያው ተደንግጓል፡፡

አቶ ካሳሁን እንደገለጹት መመርያው፣ ወጥቶ ወደ ሥራ ቢገባም እስካሁን ፍላጎት ያሳዩ ድርጅቶች የሉም፡፡ ነገር ግን ፍላጎቱ ይመጣል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡ የመገበያያ የውጭ ምንዛሪ ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው አሠራር መሠረት ይወሰናል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች