Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት ተሳትፎ በመገለሉ የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ቅሬታ አቀረበ

ከዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት ተሳትፎ በመገለሉ የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ቅሬታ አቀረበ

ቀን:

ከዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት ተሳትፎ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እንዲገለል በመደረጉ፣ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ቅሬት ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መሀል ፒያሳ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር እየተካሄደ ያለው የዓድዋ ሙዚየም ዜሮ ኪሎ ሜትር ግንባታ የመጨረሻው ሥራ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ያካተተ ቢሆንም፣ በፕሮጀክቱ የሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ተሳትፎ እንዳይኖረው መደረጉን ለከተማ አስተዳደሩና ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡ 54 ዓመታት ማስቆጠሩንና ከ450 በላይ አባላት እንዳለው የገለጸው ማኅበሩ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ደቦ ቱንካ (ኢንጂነር) ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ፣ ለማኅበሩ ቅሬታ ምላሽ በመስጠት አሁን ያለውን የሥራ ሒደት በማያደናቅፍ አኳኋን ለሥራው ተጨማሪ የባለሙያ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል መገለጹን ያወሳል፡፡

በተጨማሪም ከግንባታው ጋር በዓይነት 19 የሚጠጉ ቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች ብቻ በዋና ተቋራጩ አማካይነት መሆኑን በመግለጽ፣ የሥዕል ሥራዎቹ የግንባታ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሚኖረው ተግባር በበጎ ፈቃድ መስጠት እንደሚችሉ በደብዳቤው መገለጹን ሪፖርተር የደረሰው መረጃ ያሳያል፡፡

ዓድዋ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ የድል ታሪክ በመሆኑ በሙዚየም የሥነ ጥበብ ሥራዎች ሠዓሊያን፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ የሥነ ጥበብ ባለሙዎችና የታሪክ ጸሐፊዎች በጋራ በመምከር የሚተገበር መሆን ስለሚገባው ከደብዳቤ ምላሹ በተጨማሪ፣ የንድፈሐሳብ ምክክር ሊደረግ እንደሚገባ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ወንደሰን ከበደ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የፕሮጀከቱ ባለቤት የሆነው ጽሕፈት ቤቱ በታሪክና በኪነ ጥበብ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች የተካተቱበት የሥነ ጥበብ ሥራውን የሚያስፈጽም ግብረ ኃይል ማቋቋም አለበት ብለዋል።

 ከሠዓሊያን ማኅበር በተጨማሪ በግል የሥዕል ሥራ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ተመሳሳይ ይዘት ያለው ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ለአርበኞች ማኅበር፣ ለቱሪዝን ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለቅርስና ጥበቃ ባለሥልጣን ያስገቡዋቸውን ቅሬታዎች ሪፖርተር ተመልክቷል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የዓድዋ ድልን ታሪካዊ ዳራ መነሻ አድርጎ እየተገነባ የሚገኘው ዓድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም፣ የኢትዮጵያ ጀግኖችንና የዓድዋ መልክዓ ምድርን በሚገልጽ መንገድ ታሪካዊ እሴቱን ጠብቆ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸው ይታወሳል።

ሙዚየሙ 11 ብሎኮችን የያዘ 45 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ በውስጡ የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች፣ የዓድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ፣ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጀግኖችን ጉዞ የሚያሳይ ሙዚየምና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ300 እስከ 400 ሰው ድረስ የሚይዙ የተለያዩ አዳራሾች የሚገኝበት መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸው ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትልልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት በሥነ ጥበብ ላይ ያተኮሩ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ከተለያዩ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ኅዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ምክክር ከተደረገ በኋላ፣ ተጨማሪ ምክክር አለመደረጉንና አሁንም ድረስ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን አቶ ወንደሰን ተናግረዋል፡፡

በከተማው የትልልቅ ፕሮጀክቶች ጽሕፈት ቤት የሚተገብረው 4.6 ቢሊዮን ብር የተበጀተለትና ግንባታው በመስከረም 2012 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በተቋራጭነት ቻይና ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ኩባንያ የሚሠራው ሲሆን፣ እንዲሁም የቻይናው ተቋራጭ የግንባታ ዲዛይኑንና ግንባታውን በ730 ቀናት ውስጥ ሠርቶ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ውል መግባቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር በ1962 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ሠዓሊያን ኅብረት” በሚል የተመሠረተ፣ እንዲሁም ሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ፣ ሥዩም ወልዴ ራምሴ፣ አብዱራህማን ሸሪፍ፣ ሎሬት ደስታ ሐጎስ፣ ሥዩም አያሌውና አክሊሉ መንግሥቱ በሥራ አስፈጻሚነት የሚመሩት የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ማኅበር እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...