Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አልባሳት አምራቾች ጥራትና ዋጋን በማስተካከል ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በርካታ ላኪዎች የሚሳተፉበት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የንግድ ትርዒት ሊካሄድ ነው

በኢትዮጵያ የሚገኙ አልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች የምርቶቻቸውን ጥራት፣ ዋጋና አቅርቦት አስተካክለው ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ እንዳልባቸው  ተገለጸ፡፡

በርካታ አልባሳት ከውጭ አገሮች በሕጋዊና በኮንትሮባንድ መንገዶች በመግባት ገበያ ውስጥ እንደሚውሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህን ምርቶች ለመተካትና የአገር ውስጥ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት መሰራት እንዳልበትም ተነስቷል፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር አመራሮች እንደገለጹት፣ አምራቾች በራሳቸው በኩል ያልተሠሩ ሥራዎች እንዳሉና በዋናነትም የጥራት፣ ዋጋና አቅርቦት ጉዳዮች ላይ መሥራት እንዳልባቸው ነው፡፡

‹‹አምራቹ እነዚህን ሦስት ነገሮች አስተካክሎ ራሱን ማቅረብ አለበት፡፡ አሟልቶ ሲያቀርብ የአገር ውስጥ ምርት በመሆኑ ብቻ ተጠቃሚዎች አንገዛም አይሉም፤›› ሲሉ የገለጹት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጎሹ ነጋሽ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህን የገለጹት ከዚህ ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ስለሚካሄደው የዘጠነኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ሳምንት (Africa Sourcing and Fashion Week – ASFW) ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ስለአገር ውስጥ አምራቾች ተጠይቀው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ስለ መርሐ ግብሩ መግለጫ ሲሰጡ እንዳሳወቁት፣ በርካታ የአገር ውስጥና ሌሎች ከ25 አገሮች የተውጣጡ ከ300 በላይ የአልባሳት ላኪ ድርጅቶች የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና የፋሽን ንግድ ትርዒት ያቀርባሉ፡፡

ከጥቅምት 23 እስከ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚካሄደው የንግድ ትርዒትና ኮንፈረንስ ከ50 አገሮች የሚመጡ ከ6,000 በላይ ተሳታፊዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና፣ ዘላቂ አምራችነት፣ እንዲሁም የአፍሪካ መንግሥታት ለዘርፉ የሚኖራቸው አስተዋጽኦን በሚመለከት ሰፋ ያሉ ውይይቶችም እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡

የንግድ ትርዒቱና ኮንፈረንሱ የሚዘጋጀው በጀርመኑ ግዙፍ የንግድ ትርዒት አዘጋጅ ድርጅት ሜሴ ፍራንክፈርት (Messe Frankfurt)፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማኅበር ነው፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጎሹ እንደገለጹት፣ በርካታ አገሮች በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶች ማደጋቸውንና እንደ እነዚህ ዓይነት ትርዒቶችና ኮንፈረንሶች ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንደሚያመጡ ተናግረዋል፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾችም በዚህ ትርዒት ላይ በሚደረጉ የጎንዮሽ ድርድሮችና የገበያ ትስስር እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች