Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕወሓት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መቋጨቱን አስታወቀ

ሕወሓት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ መቋጨቱን አስታወቀ

ቀን:

  • የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሐሰተኛ መረጃዎች እየተሠራጩ መሆኑን ገልጿል

በዳንኤል ንጉሤ

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. እና ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለት ተከታታይ ቀናት በመቐሌ ሲያደርግ የነበረውን የካድሬዎች ስብሰባ ስድስት የተለያዩ ውሳኔዎችን በመወሰን ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. መቋጨቱን ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ ዞን ሊቀመንበሮች በላኩት ደብዳቤ መሠረት የተጠራው ይህ ስብሰባ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ ካድሬዎችና የሥራ አስፈጻሚ የጋራ ኮሚቴ በዕለቱ እንዲገኙ የሚያሳስብ መሆኑ ይታወሳል።

‹‹በዚህም መሠረት በስብሰባው እንዲሳተፉ ከሚገባቸው ተሳታፊዎች ውስጥ 82 በመቶ የሚሆኑት ካድሬዎች ተገኝተዋል፤›› ያለው የሕወሓት መግለጫ፣ መድረኩም የፓርቲውን አሠራርና ደንብ ተከትሎ የተጠራ ሕጋዊ መድረክ መሆኑን ተሰብሳቢ ካድሬዎች በመስማማት መወሰናቸውን ገልጾ፣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ቁጥጥር ኮሚሽን በበኩሉ፣ መድረኩ ሕጋዊና ትክክለኛ ነው ሲል በስብሰባው እንዳስታወቀ ጠቅሷል።

መግለጫው የሕወሓት ካድሬዎች በየጊዜው እየተሰበሰቡ በትግራይ ክልል የሚታዩ ጊዜያዊ ችግሮችና ጉዳዮች ላይ  መፍትሔ እንዲገኝ የተቻላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን፣ የሥራ አፈጻጸም መገምገሚያ ተዘርግቶ ጭምር ተግባራዊ እየሆነ መቆየቱን አስታውሶ፣ ይሁን እንጂ ማዕከላዊ ኮሚቴውና የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ይህንን የካድሬዎች መብት ጊዜውን ጠብቀው ባለመፈጸማቸው በመንቀፍ በቀጣይ እንዳይደገም አሳስቧል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በየጊዜው ራሱን እየገመገመና ውስጡን እያፀዳ ባለመምጣቱ፣ ችግሮች እየተደራረቡ መጥተው አሁን ለደረስንበት አጣብቂኝ ውስጥ እንድንገባ ምክንያት ሆኗል ያለው ሕወሓት፣ አሁን ተፈጥሮ ያለውን ችግር እንደ ዕድል ተጠቅመን ፓርቲው (ሕወሓት) ገብቶበት ካለው ችግር መውጣት የሚችለው በተረጋጋ መንፈስ በውስጡ ሰፊ የማጥራት ግምገማ በማካሄድ ብቻ መሆኑን አረጋግጧል። ሕወሓት ችግሮች ብሎ ያላቸው ምን እንደሆኑ በመግለጫው አልጠቀሰም።

በሕወሓት ተይዘው የነበሩ ሁለት አጀንዳዎችን በተረጋጋ መንፈስ በቀጣይ ስብሰባው ላይ እንዲካሄዱ (ስለሁለቱ አጀንዳዎች ፓርቲው ያለው ነገር የለም)፣ ቀጣይ የሕወሓት ካድሬዎች ስብሰባ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ እንዲደረግ፣ ካድሬውን ወክለው በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሳተፉ ሁሉም ዞኖችና በየደረጃው ሕወሓትን የሚወክሉ በድምር አሥራ አምስት ካድሬዎች መርጦ የሚኖራቸውን ተልዕኮ ማጣራት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በሕወሓት ካድሬዎች ላይ የወሰደው ቋሚ አካሄድን ያልተከተለ ውሳኔ እንዲታረምና በቀጣይም የሚደረግ ምንም ዓይነት ቋሚ አሠራርን ያልተከተለ አካሄድ እንዲቆምና አፈጻጸሙን የሚመለከት አካል ጉዳዩን እንዲከታተል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ጥቅምት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሕወሓት አመራሮች፣ እንዲሁም ከትግራይ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ መግባባት፣ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያስቀመጣቸውን ሥራዎች እንዲሠራ፣ ማለትም የደረሱ እህሎች እንዲሰበስብ፣ የአንበጣ ወረራን እንዲከላከል፣ ጊዜውን ያልጠበቀ ዝናብ ከሚያደርሰው ችግር በመከላከል፣ ሕዝብ ወደሚጠቀምበት መንገድ ማመቻቸት ላይ በተቀናጀ መልኩ እንዲሳተፉ የጋራ ውሳኔ መወሰኑንና በዚህ መሠረት የሕወሓት አመራሮች ስብሰባውን ለሌላ ጊዜ እንደሚያስተላልፉትና የመጡትንም የሕወሓት ካድሬዎች ወደመጡበት እንዲሸኛቸው እንደሚደረግ ጠቁሞ፣ በመቐሌ ከተማ የሚካሄድ ምንም ዓይነት ስብሰባ እንደሌለ አስታውቆ ነበር።

በተያያዘም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ በተቋሙ ስም የማኅበራዊ ድህረ ገጽ በማውጣት የተለያዩ ሐሰተኛ መረጃዎት እየተሠራጩ መሆኑን ገልጿል።

ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በክልሉ ከተቋቋሙ ቢሮዎች መካከል፣ የትግራይ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ መሆኑን መግለጫው አስታውሶ፣ ነገር ግን ከተቋሙ እስካሁን በሚመለከተው አካል ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ድረ ገጽ ሳይኖረው፣ በተቋሙ ስም ሐሰተኛ መረጃ የሚያስተላልፉ በመኖራቸው ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ ሲል ተቋሙ አሳስቧል።

ተቋሙ በማኅበራዊ ሚዲያ ተሠራጭተዋል ካላቸው መልዕክቶች መካከል፣ ወጣቶች ለውትድርና በግድ እየተመለመሉ ነው፣ ተሰናብተው የነበሩ የትግራይ ሠራዊት አባላት ተመልሰው ሊቀላቀሉ ነውና የትግራይ ሠራዊት ወደ ኤርትራ ድንበር እየተጠጋ ነው የሚሉ መረጃዎች መሆናቸውን ገልጾ፣ ሕዝቡ ይህንን አውቆ ከሚመጣው መደነጋገር ራሱን እንዲጠብቅ አስገንዝቧል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...