Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ!›

ሰላም! ሰላም! የአክብሮት ሰላምታዬ ለሁላችሁም ይደርስ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ውድ ወገኖቼ በደስታና በፍቅር ስሜት የማስተላልፍላችሁ ሰላምታዬ ከልብ የፈለቀ መሆኑንም ስነግራችሁ ከአክብሮት ጋር ነው፡፡ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መደጋገፍና መፈላለግ ብርቅ ባልነበረባት አገራችን መልካም እሴቶቻችን ደብዘዝ ቢሉም እንዳልጠፉ ግን እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፡፡ እንዴት ብትሉ እነዚህ እሴቶቻችን እኮ ስንኮራረፍም ሆነ በነገር ስንጣለዝ አብረውን አሉ፡፡ ለምሳሌ በቀደም ሊነጋጋ ሲል ኡኡታና ጫጫታ ይሰማል፣ ይህ የሆነው ጎጆዬ ባለበት በሠፈሬ ነው። መጀመሪያ ህልም መስሎኝ ነበር። ስነቃ ግን የማንጠግቦሽ ክንድ በማጅራቴ ሥር ተጠምዞ መጥቶ በዓይኔ ቁልቁል ይታየኛል። የቀለበት ጣቷ ላይ ቀለበቷ የለም። ይኼ ህልም አይደለም። አይገርምም? ‹‹እንዴ ቀለበቱስ?›› ብዬ ዘወር ስል ጩኸቱም ህልም አይደለም። ይቀልጣል እኮ ነው የምላችሁ። አሁን በደንብ እየነቃሁ ነው። ወድጄ ነው ቃል ኪዳን ሲወልቅ ዝም የምለው? ለመሆኑ ግን ሁካታና ጩኸት የማይደንቀው የኅብረተሰብና የመንግሥት አካል ግን አይገርማችሁም? ‹መድረሻ ቢጠፋ፣ ቃል ኪዳን እንዳይሆን ቢሆን፣ አንደኛዬን ተገላግዬ መሀል ቀለበት መንገድ ላይ እተኛለሁ› ብሎ ይሆን? እናንተኑ ልጠይቃችሁ እንጂ!

በጩኸቱ መበራከት ተደናግጠን እኔና ውዴ ማንጠግቦሽ ተንደርድረን ወደ ውጭ ስንወጣ፣ እንደ ዕድሜያቸው የማይተኙና እንደ ልጅነታቸው እየተመገቡ የማያድጉ ውሪዎች ናቸው። ‹ምን ጉድ ነው?› እያለ የጎረቤት ሰው ሁሉ የዓይኑን ማዝ ሳይጠርግ እየተጨናበሰ ነቅሏል። ‹‹አንተ አትናገርም? ምን ሆናችሁ ነው?›› በደርግ ጊዜ አብዮት ጠባቂ የነበረ ጎረቤቴ ይደነፋል። ‹‹ምን ይጮህባቸዋል? ልጆች መሆናቸውን ረሳው?›› ይላል በስተደቡብ የሚያዋስነኝ ጎረቤቴ። ‹‹ኧረ እግዜር ይስጠው፣ አሁን እንዲያውም በጣም ተሻሽሏል። በእሱ ጊዜ ቢሆን ምን አለፋችሁ ገና ከአልጋ ሳይወርድ ይኼኔ ታፍሰዋል…›› ይላል አንድ ልጅ እግር። ‹‹የት ታውቀዋለህ? ታሪክ ለመናገር እኮ ቢያንስ ከ40 ዓመት በላይ መኖር ይገባል…›› ብሎ ደግሞ እሱ ላይ አንዱ ይነሳበታል። ‹‹እንዲያማ ከሆነ የመምረጥ መብት ከ40 ዓመት በላይ አይሆንም ነበር?›› ብሎ ተራውን፣ ‹›ታሪክ ሳያውቁና ሳይዘክሩ ታሪክ መሥራት የሚጀምሩበት ዕድሜ እንዴት 18 ሆኖ በሕግ ይፈቀዳል?›› ይለዋል። እንዲህ ዓይነቱን ከእንቅልፍ ቀስቃሽና መሳጭ ታሪክ የሰማሁት በርግጌ ተነስቼም ስለነበር ደስ ነበር ያለኝ፡፡ ደስታ ከሥቃይ ውስጥም ይገኛል የሚሉ ፈላስፎች የተሳሳቱ አይመስለኝም፡፡ እንዲያ ነው እንጂ!

ታዲያ አረፋፍጄ ወደ ሥራዬ ላመራ ከቤት ስወጣ ሕፃናቱ ‹የሰይጣን ዶሮ› ዓይተው መጮሃቸውን አዛውንቱ ባሻዬ አጫወቱኝ። አልገባኝ አለ። ‹‹አሁን ማን ይሙት ደጅ ውለው ደጅ እያደሩ ነው የሰይጣን ዶሮ ዓይተን አናውቅም የሚሉት?›› ስላቸው ከአወቅኳቸው ቀን ጀምሮ አይቼባቸው የማላውቅ ድንጋጤ ሲደነግጡ አየሁ። ‹‹ምነው? ምን ተናገርኩ?›› ብዬ ኩምሽሽ ስል፣ ‹‹ብቻ አንተም እዚያ ኮሚቴ ውስጥ አለሁበት እንዳትለኝ?›› ብለው አፈጠጡብኝ። ለካስ ያ ሰበቡ ውኃ የማይቋጥር ሆኖ የተገኘው ሁካታና ጩኸት ‹ከበስተጀርባው የሽብር ተልዕኮ አለው? የለውም?› ተብሎ ‹ምርመራ› ተጀምሮላችኋል። ይኼን ስሰማ እኔ ራሴ ‹የሰይጣን ዶሮ› ታየኝ ብዬ ልጮህ ነበር። ‹‹ዝም ብሎ ይታያል እንዴ ሰይጣንና ዶሮ? ወይ ‹ቻፓ› ወይ ‹ኮድ› ያስፈልጋል ለዚህ ዓይነቱ ውስብስብ ነገራችን…›› የሚሉት የሠፈራችን አራዶች ናቸው፡፡ ‹‹የእኛ ሰው እኮ ባህላዊውን ከዘመናዊው እያዳቀለ ራሱን እንደሚያዝናናው፣ ቴክኖሎጂው ላይ በርታ ቢል እኮ እንግሊዝ አገር ከሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በአስማትና በመተት ማስተርስ ዲግሪውን እንደሚይዝ አይጠረጠርም…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ግሩም ድንቅ አትሉም!

ብቻ ምን አለፋችሁ ያ ሰማይ የአህያ ሆድ እንደመሰለ ተሰብስቦ እሪ ያለ ውርንጭላ ሁላ ታግቶ ዋለ። እማማ የለ አባባ የለ፣ ተማሪ ቤት የለ፣ አቧራ ማቡነን የለ። ኋላ እንደሰማነው ደግሞ አንድ ነገር የማይሞቀው የማይበርደው ሳያስበው ነገር የሚሰፋ ታዳጊ። ‹ምን ዓይታችሁ ነው እንዲያ ያስጮሃችሁ? አትናገሩም? እየጮሃችሁ ሠፈር አውኩ ያላችሁ አሸባሪ ማን ነው? ከተናገራችሁ ጉርሻ አላችሁ…› ሲባሉ አሉ እጁን አወጣ። ‹‹እሺ አንተ…›› ተብሎ ዕድል ተሰጠው። ‹‹ያየነው ዶሮ ነው…›› ብሎ የጉርሻ ሰጪውን ዓይን አየ። ‹‹እሱንማ ነገራችሁን፣ ቆይ እሺ ዶሮ ዓይታችሁ ጮሃችሁ እንበል። ከጩኸታችሁ ጀርባ ግን ከዶሮ ነጥቆ ጩኸትን ለእናንተ የሰጣችሁ ማን ነው?›› ሲል፣ ‹‹ልናገር?››፣ ‹‹በል እኮ አውጣው…›› ሲባል ምን ቢል ጥሩ ነው?  ‹‹ሰይጣን…›› ስሙን ስደጋግመው ዝም ትላላችሁ? ኮሚቴውም ይኼን እንደ ሪፖርት አቅርቦ ፈረሰ አሉ። ሠፈርተኛውም ‹ለልጅ ይታየዋል እኮ? አይገርማችሁም? ሳያስበው ከእያንዳንዱ ሽብር በስተጀርባ የማይታየውን ዓለም ተፅዕኖ አጋለጠ…› እያለ ያሳድግህ ሲለው ውሎ አደረ። እኛ እንዲህ ነን!

በበኩሌ መስማቱን እሰማለሁ ማየቱን አያለሁ እንጂ፣ ቀልቤ የማንጠግቦሽ የቀለበት ጣት ላይ ነው። የዚያ ብላቴና አንድምታ ሰፊ መልስ አወከኝ። እንዲያውም አንድ ቀን አንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ከማሻሽጥለት ደንበኛዬ ጋር በስልክ እየተነጋገርን፣ ‹‹ቁጥርህን ማን ብዬ ‹ሴቭ› ላድርገው?›› ሲለኝ ‹‹ሰይጣን…›› ብዬ አረፍኩት። ‹‹አቤት?›› ደንግጦ ጆሮዬ ላይ ከመዝጋቱ በፊት፣ ‹‹አንበርብር… አንበርብር ምንተስኖት…›› ብዬ መርበድበድ። ስርበደበድ ካርዴ ማለቅ። ይኼኔ፣ ‹‹የካርድ ፍጆታችን የጨመረው የሚለቀቅልን አጀንዳ አገላብጠን ሳንመረምር በየዩቲዩቡ ስንጣድ በመዋላችን ነው…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ትዝ ብሎኝ ከትከት ብዬ በራሴ ሳቅኩ። ሁኔታዬንና ንግግሬን በቅርብ ርቀት ሲያዳምጥ የነበረ መንገደኛ ሳይቀር፣ ከአሁን አሁን ወፈፍ ሊያደርገው ነው ብሎ መሰል ሸሸኝ። ሰው ግን ገሸሽ ለማለት ካልጠፋ ነገር በጠራራ ፀሐይ ሲባርቅ አይገርምም? እስኪ አሁን ‹ከጀርባው ህቡዕ ኃይል ይኖር ይሆናላ› ብላችሁ ደግሞ እናንተም አጣሪ ኮሚቴ ውስጥ ግቡ አሉዋችሁ። ዘንድሮ እኮ የሚቀር ጉዳይ አይመስለኝም!

በነገራችን ላይ የመብረቅን ነገር ካነሳሁ መቼ ዕለት ነው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከሴቶች ይልቅ ወንዶች በመብረቅ የመመታት ዕድላቸው አራት እጥፍ ነው…›› ሲለኝ ነበር። ‹‹የፆታ እኩልነትን ታሳቢ በማድረግ እኩል የምንመታበት ቀን እስኪመጣ…›› ብሎ አንድ ወዳጄ የመጎንተልና የመላከፍ ባህሪውን በአራት እጥፍ ጨመረው። እናላችሁ አንድ ቀን እንደለመደው፣ ‹‹የእኔ ቆንጆ በዚህ የኑሮ ውድነት አንቺን እያየሁ ቡና ሳላከትም ባልነሳ ኖሮ ምን እሆን ነበር?›› ሲላት ፖሊስ ልትጠራ ሄደችለታ። ‹‹ያው እሱ ነው…›› ብላ ስትጠቁምበት ያለ ምንም ጉሸማ ይቀደድ ጀመር። ‹‹ማርያምን እልሃለሁ ይኼው ድፍት ያድርገኝ፣ ቀንደኛ የብልፅግና ደጋፊ ነኝ። እውነት እውነት እልሃለሁ። መደመር የእኔ ብቻ ሳይሆን ሰባት ትውልዴ ድረስ እንደወረደ የተቀበልነው ነው…›› እያለ ምን ቅጡ ተንደቀደቀ። ቅቤ ምላሱም አላዳነውም ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ። ዕዳው ለወዳጆቹ ተርፎ ያን ቅጥቅጥ አይሱዙ አሻሽጬ የድለላዬን በመቀበያዬ ቀን ችሎት ልታዘብ አቀናሁ። ስንቱን ችሎት እንደምንታዘብ አላውቅም!

 እንዲያ አመዱ ቡን ያለው ወዳጄ የተከሰሰው በፆታዊ ትንኮሳ መሆኑ ሲነገረው እንደተረጋጋው፣ እርጎ እንደ እሱ ሲረጋ አላየሁም ስላችሁ። ይባስ ብሎ፣ ‹‹ክቡር ፍርድ ቤት…›› ሲል ጀመረ። ‹‹ለከፋ የመጣሁበትና የተገኘሁበት አካባቢ ባህል ነው፡፡  አያቴ ያየሁት አይለፈኝ ነበር ቅጽል ስማቸው፡፡ ከአሥራ አምስት ሚስቶች በጠቅላላው 47 ልጆች ወልደዋል። ‹ይህማ ለዘር› የሚባልላቸው ነበሩ አሉ፡፡  ክቡር ፍርድ ቤት  አባቴም የነኳት ሁሉ ሳትታቀፍ፣ ተሸሽጋ የተሳለችውን ሥለቷን በገሃድ በአደባባይ ጃንጥላ አስገብታ ሳትፈጽም የቀረች የለችም። ምንም እንኳን አባቴ የአባቱን ‹ሪኮርድ› ለመስበር ሳይታደል ሳል ጀምሮት ትንታ ቢጨርሰውም፣ ከወለዳቸው 29 ልጆች 23ኛው የሆንኩት እኔን የጀመረውን እጨርስ ዘንድ አደራ ብሎኝ አልፏል። ክቡር ፍርድ ቤት ዛሬ ያስከሰሰኝ ይህ የዘር ማንዘሬ ወግና ልማድ፣ አባቴ በጥኑ አስጠንቅቆ የቀረፀልኝ ዘር የመዝራት ራዕይ እንጂ የፆታ ትንኮሳ አይደለም…›› ሲል ሳቄን መቆጣጠር ስላልቻልኩ በዳኛው ትዕዛዝ ትዝብቴ እንዲደናቀፍ ተደረገ። የእምነት፣ የብሔር፣ የጎሳ፣ የባህል፣ የቋንቋና መሰል ጉዳዮች እኩልነት ቅድሚያውን በያዘበት ዘመን፣ ወዳጄ ‹ለከፋ የዘር ማንዘሬ መለያና አኩሪ ባህል ነው› ብሎ ክሱን ከተቃወመ፣ እንግዲህ ብይኑን ለእናንተው ልተወው። ምነው ደነገጣችሁ!

ያ ቅጥቅጥ አይሱዙ ተሸጠልኝ። ሌላም አይሱዙ እጄ ገብቶ ወጣ። የተከራዩት ለቀቁ። የለቀቁትም ተከራዩ። ጠቅልለው የሄዱት ጠቅልለው ሊኖሩ አገራቸው ገቡ። ጠቅልለው መጥተው አገራቸው ላይ ሠርተው ለመኖር የቋመጡት እንደ ቋመጡ ጠቅልለው ተመለሱ። ‹‹ተስፋዎቻችን በረጅም የዘመን ገመድ ላይ ተዘልዝለው የተሰቀሉ፣ አንድ ቀን እየወረዱ የሚበሉ ቋንጣዎች መሆናቸውን አየን…›› ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ሲናገር ሰማሁ። ሰማሁ እንጂ ስላልገባኝ አላብራራላችሁም። የገባኝና የማብራራላችሁ ግን አለኝ። የተከራየውን ሳስለቅቅ የለቀቀውን ሳከራይ፣ ጠቅልሎ የመጣውን ጥቅሉን ስፈታና ቦታ ሳደላድል፣ የተደላደለው በቃኝ ብሎ ሲጠቀልል ጓዝ ጉዝጓዙን አብሬ ስሸክፍ ሰነበትኩ። ገንዘብ ቆጠርኩ፣ ገንዘብ በተንኩ። የበተንኩትን ሰበሰብኩ፣ የሰበሰብኩትንም መልሼ በተንኩ። ‹‹ስለዓለም ጎደሎነት በጎጆዬ እልፍ ዘለላ ዕንባዎች ተንጠባጠቡ፣ ትንፋሼም አፈር አፈር ይላል…›› ያለው ባለቅኔ ስሙ የማይያዘኝ ግን ለምድነው? እንጃ!

እስኪ እንሰነባበት። ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ‹ዋን ዋን› እያልን ወግ ልንሰልቅ እዚያች የለመድናት ግሮሰሪ ተሰይመናል። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ብዙ ነገር ሰፍቶብናል አንበርብር…›› ይለኛል። መጠጥ ላይ ሰው የሚናገረውን ብዙም ከቁብ ስለማልቆጥር አላተኩርም። ‹‹የምር ብዙ ነገር ሰፍቶብናል። የሚጠብበው መጥበብ አለበት። ለነገሩ ብዙውም ነገር ጠቦናል። የጠበበንም መስፋት አለበት…›› እያለ ይህችኑ ሲደጋግምብኝ አመሸ። ጆሮዎቼ የሚለውን ይስሙ እንጂ ልቦናዬ የማንጠግቦሽ ባዶ የቀለበት ጣት ላይ ነው። ‹ቀለበቷ የት ሄደ?› ብዙ ነገር አወጣለሁ አወርዳለሁ። ‹ጠፋብኝ› ብትለኝ ስለማወጣው ያልታሰበ ወጪ አሰላለሁ። ግን ቀለበቷ ከጣቷ ሲወልቅ እሷም እንደ እኔ ሰንብታ አስተውላው ቢሆንስ? ‹ልጠይቃት አልጠይቃት?› እጉላላለሁ በሐሳብ። የሆነ ሰዓት ላይ አላስችለኝ ብሎ ሒሳቤን ከፍዬ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ውስጤ ንዴት ይንቀለቀላል። ለዘመናት የገነባሁት ብሶትና ባይተዋርነት የወለደው የሰመረ ትዳር ዕቃ ዕቃ ጨዋታ የሆነብኝ እየመሰለኝ፣ በሩን ከፍቼው ስገባ ማንጠግቦሽ በሙሉ ፈገግታ ስማ ተቀበለችኝ። ‹‹ውዴ ራት ቀርቧል…›› ብላ ወደ ማዕድ ስትጎትተኝ ክንዴን የጨበጠው የግራ እጇ ቀለበት ጣት ቆረቆረኝ። ውላ አድራ ሰፍቷት ልታስጠብበው አውልቃው እንደነበር የእኔ አለማስተዋል እንዳናደዳት አዋዝታ አስገባችልኝ። ለካ ሲሰፋ አልያም ሲጠብ ኪዳንም በልክ ይሠራል። ምነው ታዲያ እስከ ዘለዓለም ያልታሰርንባቸው ቃላት፣ ሕጎች፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍልስፍናዎች በልካችን የማይሰፉልን? ‹ወይ ልክክ አላለ ወይ አልወለቀ፣ እየተሙለጨለጨ አለ እየተነቃነቀ› የሚለውን ባሰብኩ ቁጥር ሽቅብ ሽቅብ ይለኛል፡፡ ሽቅብ ስንገፋ ቁልቁል ስንጎትት ቀኑ መሽቶ ይነጋል፡፡ የቅርቡን ትተን ሩቅ ስናማትር ከእጃችን የሚያፈተልከው ብዛቱ ሲታሰብ ግርም ያደርጋል፡፡ ‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ› መሆን ይህም አይደል እንዴ? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት