Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰሚ ያጣ ረሃብ

ሰሚ ያጣ ረሃብ

ቀን:

ከረሃብ ጦር ይሻላል ይላሉ የረሃብን አስከፊነት ለማስረዳት የሚሞክሩ ሰዎች፡፡ ጦርነት ፋታ ይሰጣል፣ ተዋጊዎች ምግብ ለመብላት አልያም ዕረፍት ለመውሰድ በምሽጋቸው ውስጥም ቢሆን ፋታ ወስደው ይመለሳሉ፡፡ ረሃብ ግን ይኼንን ዕድል አይሰጥም፡፡ ሌላው ቀርቶ በረሃብ ለመሞት እንኳን ጣረ ሞቱ ሰፊ ነው።

ረሃብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገሮች ውስጥ በየዘመኑ ብርቱ ክንዱን ያሳርፋል። በ1970ዎቹ አጋማሽ በቀድሞ ወሎ ክፍለ አገር ተከስቶ ከነበረው ድርቅ ጋር ተያይዞ በወቅቱ በነበረው ረሃብና ባስከተለው የሰውና የእንስሳት ዕልቂት ኢትዮጵያ ከረሃብ ጋር ስሟ እንዲነሳ ማድረጉ ይታወሳል።

ሰሚ ያጣ ረሃብ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ወቅቱ ለአብነት ተጠቀሰ እንጂ፣ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያን ዘመን ወዲህ በርካታ ሰዎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ ለሞት ተዳርገዋል። ምን አልባት የተራቢዎች ቁጥር መቀነስና መጨመር ካልሆነ በስተቀር፣ ኢትዮጵያና ረሃብ ጉዟቸው መሳ ለመሳ ነው ቢባል ይገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ምክንያቶች ይቀርባሉ።

ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች ታዳጊ አገርች ለከፋ ረሃብ ተጋላጭ ከሚሆኑባቸው ምክንያቶች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት፣ ድርቅና ሥር የሰደደ ሙስና፣ ወረርሽኝ ተጠቃሽ ናቸው። በእነዚህና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች ተራና ለፍቶ አዳሪ የሆኑ ዜጎች በከፋ ረሃብ ውስጥ እንዲያልፉና እንዲሞቱ ይፈረድባቸዋል።

ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የነበረው ጦርነት አቅጣጫውን እየቀያየረ መጥቶ መቋጫ ሳይበጅለት፣ ውሉ ሳይገኝለት ለ2016 ዓ.ም. ተላልፎ በዚያም በዚህም ጦርነቱ ቀጥሏል። በየአቅጣጫው እርስ በርስ እየተደረገ ያለው ጦርነት ሳይበቃ፣ ከ2014 ዓ.ም. መጨረሻ እስከ 2015 ዓ.ም. መግቢያ የዘለቀው የዝናብ እጥረት ወደ ከፋ ድርቅ ተቀይሮ በአሁኑ ወቅት በአፋር፣ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ ተስፋፍቶ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ይገኛል። ቁጥራቸው በርከት ያሉ እንስሳትንም በድርቅ የተነሳ እየሞቱ ይገኛሉ።

በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሳይበቃ በክልሉ ባሉ የተለያዩ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎችን ለህልፈት እየዳረገ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እጃቸውን ለዕርዳታ ዘርግተው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታን እየተጠባበቁ ነው።

በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ድርቁ ተባብሶ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ ሲሆን፣ ብዙዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቀዬአቸውን እየለቀቁና ከሞት የተረፉ ከብቶቻቸውን በመያዝ እግራቸው ወዳመራቸው አካባቢዎች እየተሰደዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

አቶ ጥፍጡ ጥሩነህ በሰሜን ጎንደር ዞን አዋሳኝ በምትገኘው በበየዳ ወረዳ ዋና ማርያም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ወረዳዋ በዞኑ በድርቅ ከተጎዱት ወረዳዎች መካከል አንዷ ስትሆን፣ ዋና ማርያም ቀበሌ ደግሞ የዋግ ኸምራ ብሔረሰብ ዞን ሰሀላ ሰዬምት ወረዳ ያዋስኗታል። ዋና ማርያም ቀበሌ ለወትሮውም ቆላማ እንደሆነች የሚናገሩት አቶ ጥፍጡ፣ በአካባቢው ካለው ወንዝ የመስኖ ውኃ በመጥለፍ ሰብልን አፈራርቀው በመዝራት ሕይወታቸውን በጥሩ ሁኔታ ይገፉ እንደነበር ያወሳሉ። በመስኖ ዘርተው በሚያገኙት አዝርዕት በምርቱ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ በገለባው ከብቶቻቸውን ያደልቡ ነበር።

ምንም እንኳን አካባቢው ቆላማ ቢሆንም፣ ክረምት ጠብቆ ዝናብ መጣሉ አይቀረም ነበር ሲሉ ይናገራሉ አቶ ጥፍጡ፡፡ ከዝናቡ የተሳተውን ደግሞ በመስኖ በማልማት ለልጆቻቸው ከዕለት እስከ ዓመት ጉርስ ለከብቶቻቸው ደግሞ የዓመት ቀለብን ይሰበስቡ ነበር። የ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ለ2015 ዓ.ም. መባቻ የነበረው ዝናብ በእጅጉ የተቆራረጠና ለመኸር ምርቱ መሠረትን ያልጣለ ክረምት እንደነበር ያወሳሉ። አሁን ላጋጠማቸው ከባድ ረሃብ መነሻውም የዚያን ክረምት የዝናብ እጥረት ነው የሚሉት አቶ ጥፍጡ ናቸው።

የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሷሊህ ሀሰን፣ የአርሶ አደሩን ሐሳብ በመጋራት የ2014/15 ዓ.ም. የምርት ዘመን በእጅጉ እንደሚቀንስና አሁን ላይ የሚታየው ሞት፣ ስደትና ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ቅድመ ትንበያቸውን አስቀምጠው እንደነበር ገልጸዋል።

የ2014 ዓ.ም. የክረምት ወቅት ከወትሮው በተለየ ዝናብ አጠር ነበር የሚሉት አቶ ሷሊህ፣ በዚህም የተዘራው ዘር ሳይበቅል መቅረቱን፣ የበቀለውም አድጎ ለፍሬ ሳይበቃ ገና በቡቃያነቱ በፀሐይ ተበልቶ እንደቀረ ያስታውሳሉ።

እነዚህ ምልክቶችም አሁን ላይ በወረዳቸው በአጠቃላይ በሰሜን ጎንደርና በአጎራባች ሰሀላ ሰዬምት ወረዳ የተከሰተውን ዓይነት ድርቅ ሊያስከትልና የሰዎችና የእንስሳትን ሞት ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ እንደ ባለሙያ ግምታቸውንና ሥጋታቸውን ያስቀምጣሉ። በእርግጥ የዘሩት ሲጠፋ፣ የበቀለውም ቡቃያ ከመሬቱ ሳይነሳ ሲከስም፣ ክረምት ያላንዳች የዝናብ ጠብታ ሲያልፍና ወንዞችም ሲደርቁ ነገ ረሃብና ቸነፈር ሞትና ስደት እንደሚመጣ እንኳንስ ለግብርና ባለሙያና ለአርሶ አደር ለማንም ሰው ግልጽ ነው።

አቶ ሷሊህም፣ ግምታቸውና ሥጋታቸውን ይዘው አልተቀመጡም፡፡ ከወረዳው አስተዳደር ጋር በመሆን ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ በ2015 ዓ.ም. ሰው በረሃብ ማለቁ አይቀርም፣ እንስሳትም አይተርፉም በማለት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመመዝገብና ሙሉ ቃለ ጉባዔ በማዘጋጀት ወደ ክልሉ የአደጋ ሥጋትና ምግብ ዋስትና ቢሮ በመሄድ ሰነዳቸውን አስገብተው እንደነበርና ከመንግሥት የምግብ እህል ዕርዳታ ካለ ሰው ከመሞቱ በፊት ድረሱልን ብለው ማመልከቻቸውን፣ አሁንም ድረስ ለክልል ምግብ ዋስትና ቢሮ ያስገቡት ቃለ ጉባዔ እንዳለ ይናገራሉ።

‹‹ዳሩ ግን ማን ሰሚ ተገኝቶ የሕዝቡን ጩኸትና ቅድመ ትንብያ ማን አድምጦት›› የሚሉት ኃላፊው፣ የክልሉ ምግብ ዋስትናና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ከዞንና ከወረዳ የተሰጠውን መረጃ ተቀብሎ መደርደሪያ ላይ ከማስቀመጥ፣ ችግሩ ምንድነው ብሎ ወርዶ ተመልክቶ ቅድመ ጥንቃቄ ቢያደርግ ኖሮ አሁን ላይ ሰውም ሆነ እየሞተ ያለው እንስሳ በዚህ ልክ ባልሆነ ነበር ሲሉ ያስረዳሉ።

በወቅቱ የነበረው የመኸር ምርት መጠን ከታሰበው 49 በመቶ ሲያሽቆለቁል፣ ድርቁም ሲበረታ ይህ ነገር ከ120 ሺሕ በላይ ሰዎችን አደጋ ላይ እንደሚጥል ለሁሉም ሰው ግልጽ ነበር፣ ይህ እንደሚመጣም አሳውቀናል ይላሉ፡፡ ሥጋታቸው ዕውን ሆኖ በአሁኑ ወቅት የወረዳው ብሎም የዞኑ ማኅበረሰብ ረሃብና ድርቅን ተንተርሰው በሚከሰቱ በሽታዎች እየሞቱ እንደሆነ በየወቅቱ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንስሳትም ቢሆኑ ለምግብነት እንኳን ሳይበቁ ለውሻና ለአሞራ ሲሳይ እየሆኑ ነው።

‹‹ርስቴን በማረስ በዝናብ አብቅዬ በፀሐይ አብስዬ ቤተሰቤን እመራበት የዓመት ጉርሴን አገኝበት የነበረውና እንደ ልጆቼ እወደው የነበረው በሬዬን የማበላው አጥቼ ሞተብኝ ምትክ ለሌላቸው ለልጆቼ ፈጣሪ ቶሎ ይድረስላቸው፡፡ አቅመ ደካማ የሆኑ ቤተሰቦችም አሉኝ፡፡ የእነሱንም ጉድ በዚህ ክፉ ቀን እንዳያደርግብኝ ፈጣሪን እየለመንኩ ነው፤›› ይላሉ አቶ ጥፍጡ።

ዩኒቨርሲቲዎችና አንዳንድ ለጋሾች በጣም ለደከሙና ሞት አፋፍ ላይ ላሉ ሰዎች በሚያደርጉላቸው ትንሽ ትንሽ ድጋፍ ነጋቸውን እየገዙ እየዋሉ እያደሩ እያየናቸው ነው የሚሉት አቶ ጥፍጡ፣ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ወገኖች እየሞቱ እንደሆነ መስክረዋል።

የሚታመሙ ሰዎች በወቅቱ ሕክምና ቢያገኙ መዳን ይችሉ ነበር የሚሉት እኚህ ሰው፣ ሰዎች ሲታመሙ ወደ ሕክምና ተቋም ለመውሰድ በቃሬዛ ተሸክሞ የ6፡00 ሰዓት ጉዞ ማድረግን እንደሚጠይቅ ያክላሉ፡፡ ሰው በልቶና ጠጥቶ በሚያድርበት ወቅት ጉዞው አጭር፣ ሸክሙም ቀላል ነበር፣ አሁን ግን ሰው በረሃብ ተወግቶ እንኳንስ ሰውን ያህል ነገር በትከሻው ተሸክሞ ሊሄድ ቀርቶ ከቤት ለመውጣትም አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በአሁኑ ወቅት ሰው ታሞ በቃሬዛ ለመውሰድ ሰዎችን አያይዙኝ ተብለው ሲጠየቁ ‘በምን አቅማችን ነው የምንሸከመው’ በማለት ይመልሳሉ፡፡ በዚህም ብዙ ሰዎች ሐኪም ሳያያቸው በቤታቸው ሆነው ይሞታሉ፣ የሚሉት አርሶ አደር ጥፍጡ፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ሥጋት ላይ እንደሆኑ ያስረዳሉ። ወጣት ልጆችና አቅመ ደካማ ቤተሰብ የሌላቸው ሰዎች አካባቢውን እየለቀቁ በብዛት እየሄዱ እንደሆነ ተናግረዋል። እሳቸውን ጨምሮ በርከት ያሉ ልጆችና ሽማግሌዎች ያሉባቸው ቤተሰቦች ግን ‹ተሰደንስ ምን እናበላቸዋለን› በሚል ሥጋት ባሉበት የሞተው እየሞተ የተረፈውም የመንግሥትንና የለጋሽ አካላትን እጅ እየጠበቀ እንደሆነ ያብራራሉ።

ድርቁ፣ ረሃብና ስደቱ የሰዎችና የእንስሳት ሞቱ መቋጫ አላገኘም የሚሉት የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ችግሩ በስፋት ቢወራም ጠብ የሚል ነገር አልደረሰም ብለዋል፡፡ ኃላፊው ሷሊህ፣ በተለይ የእንስሳቱ ሞት ተባብሶ መቀጠሉን፣ የሰዎች መፈናቀልም በየዕለቱ መበራከቱን ያስረዳሉ። በ50 ሺሕ እና 60 ሺሕ ብር የተገዙ በሬዎች ዛሬ ላይ ወደ ገበያም ሆነ ከበረት መውጣት ተስኗቸዋል፡፡

በወረዳው ከ6‚400 የሚልቁ የዳልጋ ከብቶች ሞተዋል ብለዋል፡፡ ድርቁ ለተከታታይ ዓመት የዘለቀ በመሆኑ ችግሩ ሥር የሰደደና የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ እንደሆነም አክለዋል። የ2016/17 ዓ.ም. የምርት ዘመንም ቢሆን፣ ተስፋ የሌለውና ዛሬ ካሉበት የተሻለ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት እንደማይቻል አቶ ሷሊህ ገልጸው፣ የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ዘላቂ መፍትሔ ሊፈልጉ ይገባል የሚለውን አስምረውበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...