Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ከአፍሪካ አገሮች ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ተጠቆመ

በኢትዮጵያ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ከአፍሪካ አገሮች ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚገኝ ተጠቆመ

ቀን:

የትምባሆ ኢንዱስትሪን ለመቆጣጠር ጠንካራ ሕጎች ከሏቸው አገሮች የምትመደበው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ካሉ 18 አገሮች በትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት በዝቅተኛ ደረጃ እንደምትገኝ፣ ‹‹የአፍሪካ ቶባኮ ኢንዱስትሪ ኢንተርፊራንስ ኢንዴክስ፣ 2023›› ሪፖርት አመለከተ፡፡

ባለፈው ሳምንት በበይነ መረብ በተደረገ መድረክ የቀረበው ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ፣ በዑጋንዳና በቦትስዋና ያለው የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ዝቀተኛ መሆኑን አሳይቷል፡፡

እንደ ሪፖርቱ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያና ካሜሩን ከፍተኛ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ያለባቸው ሲሆኑ፣ ቦትስዋና ጣልቃ ገብነቱን በመቆጣጠር ጥሩ አፈጻጸም አስመዝግባለች፡፡

የአገሮች የ2023 ደረጃቸው እ.ኤ.አ. በ2021 ከነበራቸው ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ፣ ቡርኪና ፋሶና ቦትስዋና ጣልቃ ገብነቱን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ ለውጥ ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ኮትዲቯርና ዛምቢያ ያሳዩት ለውጥ ዝቅተኛ መሆኑ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ ስምንት አገሮች በ2021 ከነበራቸው አፈጻጸም ዝቅ ብለው ሲገኙ፣ ኬንያ ደግሞ ከፍተኛ ምስቅልቅል ያለባት ሆናለች፡፡

የአፍሪካ ቶባኮ ኮንትሮል አሊያንስ (ኤቲሲኤ) ከአፍሪካ ሴንተር ፎር ቶባኮ ኢንዱስትሪ ሞኒተሪንግ ኤንድ ፖሊሲ ሪሰርች እንዲሁም ከግሎባል ሴንተር ፎር ጉድ ገቨርናንስ ኢን ቶባኮ ኮንትሮል (ጂጂ-ቲሲ) ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ኢንዴክስ፣ መንግሥታት የአገራቸውን የጤና ፖሊሲ ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ምን ዓይነት ምላሽ እየሰጡ እንደሆነና የዓለም ጤና ድርጅት የትምባሆ የኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነትን ለመገደብ ያወጣውን የትምባሆ ቁጥጥር የሕግ ማዕቀፍ አርቲክል 5.3 ለመተግበር እያደረጉ ያለውን ምላሽ መሠረት ያደረገ ነው፡፡

የሪፖርቱ መሪ አዘጋጅ አርቲ ሲን (ዶ/ር) እንዳሉት፣ 18ቱ የአፍሪካ አገሮች በሰባት አመላካቾች የተመዘኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጋር አላስፈላጊ ግንኙነትን መፍጠር፣ የጥቅም ግጭት መኖርና ኢንዱስትሪው በፖሊሲ ዝግጅት ላይ መሳተፍ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ቦትስዋና፣ ጋቦንና ሞሪሺየስ በ2023 በወጣው ሪፖርት ከትምባሆ ኢንዱስትሪ ጋር አላስፈላጊ ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆን፣ ማዳጋስካር፣ ደቡብ አፍሪካና ታንዛኒያ ከትምባሆ ኢንዱስትሪዎች ጋር በከፍተኛ ሁኔታ አላስፈላጊ መስተጋብር እንደነበራቸው ሲን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የጥቅም ግጭትን በተመለከተ ሪፖርቱ ሲጠናከር፣ ኢትዮጵያና ዑጋንዳ ማናቸውም ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው የትምባሆ ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀሉ እንዳልታዩም አክለዋል፡፡

በ2023ቱ የትምባሆ ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ኢንዴክስ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዚምባቡዌ፣ ሞሪሺየስ፣ ኮትዲቯር፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክን ጨምሮ የ18 የአፍሪካ አገሮች ደረጃ ተካቷል፡፡ አገሮቹ ትምባሆ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ብሎም የኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነትን ለማስቀረት በሠሩት ሥራ ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አፈጻጸም ቢያሳዩም፣ ሁሉም አገሮች በአገራቸውም ሆነ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ሕግና መመርያ በመተግበር በኩል ክፍተቶች አሉባቸው፡፡ በመሆኑም ሁሉም አገሮች የሲቪል ማኅበረሰብን ማበረታታትና ማብቃት፣ የሥነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀት፣ አማራጭ አኗኗርን ማስተዋወቅ፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ የትምባሆ ኢንዱስትሪዎችን ከማኅበራዊ አገልግሎት ማገድ፣ ማጨስን እንደተለመደ ነገር አለመቁጠር እንዲሁም የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ሲን (ዶ/ር) ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትምባሆ ማጨስ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የተለያዩ ሕጎችና መመርያዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመራቸው ለውጥ ቢያሳይም፣ በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአጫሾች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ውስጥ እየጨመረ በመሆኑ፣ ጠንካራ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ማውጣትና መተግበርም ግድ ይላል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገሮችም ትምባሆ አምራቾች ጠንካራ ሕጎች እንዳይወጡ ጣልቃ ይገባሉ፡፡ ሕግ እንዳይወጣ እንቅፋት ከመሆን ባለፈም፣ ከወጣ በኋላ እንዳይተገበርና ደካማ አፈጻጸም እንዲኖር ከማድረግ አንፃር ተፅዕኖ ይፈጥራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በ2011 የወጣው የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ በውስጡ ጠንካራ ድንጋጌዎችን በመያዙ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ሕጎችና ስምምነቶች አንፃር ጠንካራ ቢባልም፣ በአተገባበሩ ዙሪያ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ስለትምባሆ አጫሾች ቁጥሮች ምን ያሳያሉ?

ትምባሆ በዓለምም በአገርም ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ ትምባሆ ከሚያጨሱ መካከልም ግማሽ ያህሉ በትምባሆ ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች የሚሞቱ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች በዚሁ ምክንያት ሲሞቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ያህሉ ሁለተኛ አጫሾች ወይም የማያጨሱ ሆነው ከሚያጨሱ ሰዎች በሚለቀቀው ጭስ ምክንያት የሚሞቱ ናቸው፡፡

በዓለም ትምባሆ ከሚያጨሱት መካከል 80 በመቶ ያህሉ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ የሚኖሩ ሕዝቦች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያም ከዚሁ የምትመደብ መሆኗን  የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ አጫሹ ማኅበረሰብ ሁለት ዓይነት የትምባሆ ምርቶችን ማለትም በፋብሪካ የተመረተ ወይም በእጅ የሚጠቀለል ሲጋራ፣ ሲጋራዎች፣ የቱቦ ትምባሆ፣ ጋያና ሺሻ እንዲሁም ጭስ አልባ የሆነ ትምባሆ በማሽተትና በማኘክ ይጠቀማል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሠራው የአዋቂዎች ትምባሆ የመጠቀም ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አምስት በመቶ አዋቂዎች  የትምባሆ ምርቶችን ይጠቀማሉ፡፡ የትምባሆ ዓይነቶችን በተመለከተ፣ 2.7 በመቶ አዋቂዎች በፋብሪካ የተመረቱ ሲጋራዎች ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ 1.7 በመቶ ያህሉ ጭስ አልባ ትምባሆ ተቃሚዎች ናቸው፡፡

የትምባሆ አጠቃቀም ከዕድሜ አንፃር ሲታይ፣ 2.4 በመቶ በመያዝ በዝቅተኛው እርከን የተቀመጡት ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ያሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ 8.9 በመቶ በመያዝ ከፍተኛው የትምባሆ ተጠቃሚዎች ደግሞ ዕድሜያቸው ከ45 እስከ 64 የሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ናቸው፡፡

  የትምባሆ አጠቃቀም በክልሎች ልዩነት የሚያሳይ ሲሆን፣ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር በምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢ ያሉት አፋር፣ ሶማሌና ሐረሪ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ አዋቂዎች በብዛት ትምባሆ ይጠቀማሉ፡፡

በኢትዮጵያ የትምባሆ አጠቃቀም ከጎረቤት አገሮች ጋር ሲነፃፀር በአንፃራዊ ሁኔታ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ከትንባሆ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በሳምንት 259 ወንዶችና 65 ሴቶች፣ በዓመት ደግሞ 16,800 ሰዎች ከማጨስ ጋር በተያያዙ በሽታዎች እንደሚሞቱ የቶባኮ ኮንትሮል ዳታ ኢንሽየቲቭ መረጃ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...