Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቴክኒክና ሙያ ምራጭ ወይስ ተመራጭ?

ቴክኒክና ሙያ ምራጭ ወይስ ተመራጭ?

ቀን:

ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ሳይመጣላቸው ሲቀር ወደ ተለያዩ ቦታዎች ያማትራሉ፡፡ ብዙዎችም የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋምን እንደ አንድ አማራጭ አድርገው ሲጠቀሙበት ይስተዋላሉ።

አሥረኛ ክፍል ላይ ሲወድቁ አልያም 12ኛ ክፍል ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት ሳይችሉ ሲቀሩ ወደ ቴክኒክ ኮሌጅ በመግባት ተቋሙን እንደ አማራጭ አድርገው ይገቡበታል እንጂ ጥሩ ወጤት አስመዝግበው ሙያውን ለመቅሰም ብለው የሚገቡ ተማሪዎች እስከዚህም አይደሉም፡፡

ለችግሩ መፈጠር ደግሞ ብዙ ዓይነት ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ ‹‹ችግሩ የትውልዱ አይደለም እኛም የመራንበት ጉድለት ነው ብለን እናምናለን›› ያሉት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥልጠና ዘርፍ የአገር ውስጥ አማካሪ አዝመራ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተማሪ አሥረኛ ክፍል ሲወድቅ የሚገባበት ተደርጎ እየተሳለ ነው የመጣው፣ ይህንንም ለማስቀረት በአዲሱ የሥልጠና ፖሊሲ ላይ ተደርጎበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የትምህርት ፖሊሲ ለሙያው የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደነበር በአሁኑ ወቅት በተለይ ከቅድመ አደኛ ደረጃ ጀምሮ ተማሪዎች ችሎታቸውን እየለዩ፣ እየተለማመዱና እያወቁ እንዲመጡ ለማስቻል የትምህርት ፍኖተ ካርታ አንዱ አካል ተደርጎ እየተሠራ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

እንደ አዝመራ (ዶ/ር)፣ በሚቀጥለው ዓመት ምናልባት የዝግጅት ሥራው ካለቀ ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ሲደርሱ በመረጡት ሙያ ሠልጥነው ወደሚፈልጉት እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ 

ከዚህ በኋላ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ምራጭ ሳይሆን መርጠውት የሚመጡበት ዘርፍ እንዲሆን የሚያስችል አዲስ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑንና ተማሪዎች ይኼንን አውቀው ዕድሉን ለመጠቀም ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ አዝመራ (ዶ/ር) አሳስበዋል።

ባለፉት ዓመታት የትምህርት ዘርፉ የመጣበትን ሁኔታ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙህራን በትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ያሉ ድክመቶችና ፈተናዎች ምንድናቸው?  ቀጣይስ ችግሮች እንዴት መፈታት አለባቸው? በሚል ጥናት አቅርበው እንደነበርና ከጥናቱ በመነሳትም የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ ሊመራ የሚገባበትን ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተው ማቅረባቸውን የተናገሩት አዝመራ (ዶ/ር)፣ ከዚሁ ፍኖተ ካርታ በመነሳት አዲስ ፖሊሲ ተቀረፆ ወደ ሥራ ከገባ ከስድስት ወራት በላይ እንዳስቆጠረ አክለዋል፡፡

በዋናነት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የትምህርት አግባብነትና የጥራት ችግር አለበት ተብሎ መወሰዱን፣ ችግሩን በአገር ደረጃ ባለው አቅም ብቻ መፍታት እንደማይቻል፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ልምዶችን መጠቀም ስለሚያስፈልግ ከተለያዩ አገሮች ጋር በትብብር እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለይ ቻይና የሰው ሀብት ልማት ላይ በሰፊው ዕገዛ እያደረገች እንደሆነ ጠቁመዋል።

በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ቅበላ ዙሪያ ለሪፖርተር ማብራሪያ የሰጡት አዝመራ (ዶ/ር)፣ ቅበላው በሁለት ዓይነት መንገድ መሆኑንና የመጀመሪያው አጫጭር ሥልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሠልጣኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልጸው በመደበኛ ሥልጠና ደግሞ እስከ ግማሽ ሚሊዮን መቀበል እንደሚችሉ አብራርተዋል።

ስለ አጫጭር ሥልጠናዎች የተናገሩት አዝመራ (ዶ/ር)፣ በዋናነት ከዚህ በፊት የነበረው አሠራር ሠልጣኞችን ለረዥም ጊዜ አሠልጥኖ ደረጃ ሦስት አራት የሚል ሠርተፍኬት መስጠት ነበር፡፡ ይኼ አሠራር ቀርቶ በአጭር ጊዜ ሥልጠና ሰጥቶ ወደ ገበያ በማስባት ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ትልቅ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ትምህርት 8ኛ ክፍል ፕሮዳክቲቨ ቴክኖሎጂ ኮሜርስ (Productive Technology Commerce) በሚል እንዲሁም ከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶች ግብርና ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱት ደግሞ አቶ ፈለቀ ውቤ የባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ናቸው።

በወቅቱ ይሰጥ የነበረው ትምህርትና ሥልጠና በቂ አልነበረም የሚሉት አቶ ፈለቀ፣ አሁንም ዕድገት አለው እንጂ ያለበት ቁመና የሚያወላዳ አይደለም፣ ብዙ መፈተሽ ያለበት ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡

ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ያለው ተቋማትን በየወረዳው ለማዳረስ የተደረገው ጥረት ትልቅ እመርታን ያሳየ ነው ያሉት አቶ ፈለቀ፣ በአብዛኛው በአማራ ክልል ያሉ ገጠራማ ወረዳዎች የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተደራሽ ሲሆኑ፣ በየዓመቱ ከመሰናዶ ትምህርታቸውን የጨረሱና አሥረኛ ክፍል ለመሰናዶ ትምህርት ውጤት ያልመጣላቸውን ተማሪዎች በመቀበል እያሠለጠነ መቆየቱን አብራርተዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ ከ123 በላይ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጆች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ ወስጥ 23ቱ ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ናቸው፡፡

 ዓመታዊ የተማሪዎች የቅበላ አቅማቸው በአጠቃላይ 6,500 እንደሚደርስ የተናገሩት አቶ ፈለቀ፣ ሆኖም ተቋሞቹ እንደ ሌሎች የትምህርት ተቋማት ራሳቸውን ችለው የቀጠሉና በቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ለማለት እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል።

ለምን እንደሆነ ባይታወቅም ከዓመት ወደ ዓመት የተማሪ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የሚናገሩት ዋና ዲኑ፣ እንደ ባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለምዝገባ እየመጡ ያሉ ተማሪዎች በተጨባጭ ከሁለት ሺሕ አይበልጡም ብለዋል።

ተማሪዎች ሠልጥነው በሠለጠኑበት ሙያ የሥራ ዕድልን አለማግኘት ምናልባት አንዱ ችግር ሊሆን ይችላል ያሉት አቶ ፈለቀ፣ የትምህርትና ሥልጠና ጥራት መጓደል አሳሳቢ እንደሆነ አክለዋል።

ለትምህርት ሥልጠና ጥራት መጓደል ደግሞ የግብዓት አቅርቦት አለመሟላት አንዱ መንስዔ ሲሆን፣ ከመንግሥት የሚገኘው ገንዘብ ውስን በመሆኑ ተቋሙ ኢንተርፕራይዞችን በእንጨት ሥራ፣ በሽመና፣ በምግብ ዝግጅትና በየዘርፉ በማቋቋም ራሱን እንዲችል የታለመ ቢሆንም፣ አሁንም ያሉ ውስንነቶችን ማሻሻልና ረጂ ድርጅቶች እንዲያግዙ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን በሰው ሀብት ልማት በኩል ቻይና አጫጭርና ረዣዥም የሙያ ሥልጠናዎችን እየሰጠች ቢሆንም፣ የቴክኖሎጂ ማቴሪያል ድጋፍ ግን ብዙም አይደለም ብለዋል።

ይህ በመሆኑም ሠልጣኞች በበቂ ሁኔታ በተግባር ለመሠልጠን ከመቸገራቸው ባሻገር፣ የሥልጠና ጥራቱን ይቀንሰዋል፡፡ ተማሪዎች በተግባር ብቁ ሆነው ካልተመረቁ በየፋብሪካዎች ሥራ ለመፍጠርና ለመቀጠር ውስንነት ያጋጥማቸዋል ብለዋል።

በዚህም የሥራ ትስስሩ ተጠቃሚ ከሚሆኑት በየዓመቱ ከሚመረቁት ተመራቂዎች ከ50 እና ከ60 በመቶ አይበልጡም ብለዋል።

በየዓመቱ በቀላሉ እስከ 1500 ተማሪዎች ተምረው ይወጣሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ሥራ የሚያገኙት ከ70 በመቶ የሚሆኑት ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ ሥራ ይዘዋል የተባሉትን በመቁጠር እንጂ በተመረቁበት ሙያ የሚገቡት በጣም አናሳ ናቸው ሲሉ አቶ ፈለቀ ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች መፍታት አለብን፣ ይህ ደግሞ የተቋሙም የመንግሥትም ሥራ ነው። በአጠቃላይ በትምህርት መስኩ ለውጥ አለ ነው የምንለው እንጂ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሰናል ለማለት አይቻልም ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...