‹‹አባት ዐልባ ሕልሞች›› የራስ እውነትን ፊት ለፊት በድፍረት ለመጋፈጥ ሲባል የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑን ደራሲው ማስረሻ ማሞ ይናገራል፡፡
ሥነ ልቦናዊ ሕመምን፣ አካላዊ ቁስልን፣ ስሜታዊ ሲቃንና ማኅበራዊ ሰቆቃን አደባባይ ላይ ማስጣትን የፈውስ ሒደት አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ ሲሆን፣ ሕይወት እንደወረደ የተንኮለኮለበት ነው፡፡ መጽሐፉ በአንድ ዓመት ከስድስት ወሯ እናቷ የሞተችባት፣ በሦስት ዓመቷ አባቷ ጥሏት የጠፋ፣ በአምስት ዓመቷ አያቷን በሞት የተነጠቀች፣ በአደራ የተቀበሉ ዘመዶቿ የቤት አገልጋይ ያደረጓት፣ በእህቷ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ የተደረገባትና ልጅ በወለደችላቸው ወንዶች ምንም ዓይነት ዕገዛ ስላልተደረገላት የቀጨኔ እናት በዋናነት የሚተርክ ነው።
በማስረሻ ማሞ የተጻፈው ‹‹አባት ዐልባ ሕልሞች›› 340 ገጽ ያለው ሲሆን፣ ዋጋውም 700 ብር ነው፡፡ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ከ8፡00 ሰዓት በስቴይ ኢዚ ፕላስ ሆቴል የሚመረቅ ይሆናል፡፡