የኤርትራን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ በዋዜማው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ማስነሳታቸው ይታወሳል፡፡ እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 4 ቀን 1993 በሺሕ የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ታላቂቱን አገር ኢትዮጵያ የሚከፋፍልና ወደብ አልባ አገር የሚያደርግ ነው ያሉትን የኤርትራን መገንጠል በመቃወም መውጣታቸው አይዘነጋም፡፡
የጊዜው መንግሥት ለዚህ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ ጠንከር ያለ ነበር፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ቆሰሉ፡፡ ሁለት ተማሪዎች በሆስፒታል እንዳሉ መሞታቸውም ተረጋገጠ፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር እንዳትሆን የሚለው የብዙ ዜጎች ጩኸት ሰሚ አጥቶ ቀረ፡፡ የኤርትራ መገንጠል ጉዳይ አፍጥጦ መጣ፡፡ ግንቦት 16 ቀን 1985 ዓ.ም. በተካሄደ ሪፈረንደም ኤርትራ ሉዓላዊት አገር ሆነች፡፡ ከኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ጎን ለጎን ይነሳ የነበረው የባህር በር ወይም የወደብ ጥያቄም በጊዜው በነበረው መንግሥት ሆን ተብሎ ወደ ጎን መገፋት መጀመሩን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከ1985 እስከ 1992 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን፣ እንዲሁም በአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ዘንድ በባህር በር ጉዳይ ከፍተኛ ውይይቶችና ክርክሮች ይደረጉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁኔታ ያልወደደው የጊዜው አስተዳደር ሆን ብሎ በሚመስል መንገድ እነዚህን ውይይቶች እንዲዳፈኑ አድርጓል ይላሉ፡፡
በጊዜው የነበረው ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ሌተና ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት እ.ኤ.አ. በ2007 ‹‹Ethiopian’s Sovereign Right of Access to the Sea Under International Law›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መመረቂያ ጽሑፍ፣ የባህር በር ጉዳይ ወደ ጎን የተገፋበትን መነሻ ምክንያት በሰፊው አብራርተዋል፡፡
‹‹የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እስከ 1994 ዓ.ም. ነበርኩ፡፡ የጦሩ ከፍተኛ አመራር እንደመሆኔ መጠን መንግሥት በባህር በር ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በቅርበት ማወቅም ነበረብኝ፡፡ በጊዜው የባህር በር ጥያቄን በተመለከተ የተለየ ሚስጥራዊ አቋም አልነበረንም፡፡ የእኛ ዋናው ትኩረት ኢትዮጵያ የባህር በር ጉዳይን ረስታ፣ ተጨባጩን ሀቅ ተቀብላ ሰላም በመገንባትና ድህነትን በማጥፋት ላይ ብታተኩር ይሻላል የሚል ነበር፡፡
‹‹በጊዜው እኔም ሆነ ብዙዎቹ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለ ሥልጣናት የባህር በር ጉዳይን ማንሳት፣ ከአዲሱ ሕገ መንግሥታችን ጋር የሚጋጭ ነው ብለን እናስብ ነበር፡፡ የባህር በር ጥያቄ የሚያነሱት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39 የደነገገውን የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት የሚቃወሙ ናቸው ብለን እናስብ ነበር፡፡ የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉ ያለፈው የፊውዳላዊና የወታደራዊ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው፡፡ የባህር በር ጥያቄ የሚያነሱት የሚል አመለካከት ነበረን፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር ወይም ወደብ ሊኖራት ይገባል የሚሉ ወገኖችን ፍፁም ስቃወም ነበር የኖርኩት፤›› በማለት ሌተና ጄኔራል አበበ በዚህ ጥናታቸው አሥፍረዋል፡፡
ልክ እንደዚህ ወደ ጎን ሲገፋ የቆየው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ከኤርትራ መገንጠል ጋር ተያይዞ ጠንከር ብሎ ቢነሳም፣ መንግሥት ጉዳዩ አይነሳብኝ በማለቱ ከውይይት መድረኮች ርቆ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ከ40 ያላነሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በ1985 ዓ.ም. ከሥራ መባረራቸው መንግሥት በአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ዘንድ የባህር በር ጉዳይ እንዳይነሳ በመፈለጉ እንደሆነ ይወሳል፡፡ በዚህ ጊዜ የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም የባህር በር ጥያቄ ገፍቶ እንደ መምጣቱ የመንግሥት ዕርምጃ ይህንኑ ፀጥ ለማሰኘት ያለመ ነበር የሚል ግምት አስነስቶ አልፏል፡፡
የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አድርጓታል ቢባልም፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች በነፃነት መገልገል እንደቀጠለች ታሪክ ያወሳል፡፡ በተመድ ሪሊፍ ዌብ በተባለ ድረ ገጽ ላይ የሠፈረው፣ ‹‹Eritrea – Ethiopia: IRIN Focus on Assab‚ 5 June 2000›› በሚል ርዕስ የቀረበው ሀተታ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ ከቀረጥና ከታሪፍ ነፃ በሆነ መንገድ መጠቀም መቀጠሏን ያወሳል፡፡
ስትገነጠል ለኢትዮጵያ አሰብ ወደብን በነፃነት እንድትገለገልበት ፈቅዳ የነበረችው ኤርትራ፣ በሒደት ግን ከጎረቤቷ ጋር አለመስማማት ውስጥ እንደገባች ተጠቅሷል፡፡ ለሁለቱ ተጎራባቾች አለመግባባት ምንጭ የነበሩት ደግሞ የወደብ አስተዳደር ጉዳይ፣ የኮሚሽን ክፍያና የመገበያያ ገንዘብ ጉዳይ አንደነበሩ ተመላክቷል፡፡
የሁለቱ ተጎራባቾች ውዝግብ በሒደት መካረሩንና ወደ ድንበር ጦርነት መሸጋገሩን ዘገባው ያትታል፡፡ ከድንበር ጦርነቱ በፊት ለኢትዮጵያም ሆነ ለራሷ ለኤርትራ ከፍተኛ የባህር ንግድ መተላለፊያ በር የነበረው አሰብ ወደብ በሒደት ጥቅም አልባ ወደመሆን መሸጋገሩን ይህ ዘገባ ጨምሮ ያብራራል፡፡
ኤርትራ ነፃ አገር ስትሆን የአሰብ ወደብ 70 በመቶ ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ወደቡን ላለመጠቀም ወስና ወደ ጂቡቲ ወደብ ፊቷን ስታዞር ግን ይህ ሁኔታ መቀየሩ ይነገራል፡፡ ሁለቱ አገሮች ወደ ጦርነት ሲገቡ ደግሞ አንዱ የሌላውን አገር ዜጋ በማስወጣቱ ከአነስተኛ ንግድ እስከ የወደብ አገልግሎት ሥራዎች ተሰማርተው የቆዩ አሰብ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታም መፈናቀል መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኤርትራ ሰዎች ለወደብ አገልግሎቱ ይከፈለን የሚሉት ኮሚሽን እየጨመረ መምጣቱ እንደ ችግር ተነስቷል፡፡ የመገበያያ ገንዘባቸውን ወደ ናቅፋ በመቀየር የንግድ ሚዛንን ለማስቀየር መሞከራቸውም ሌላው እንቅፋት ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል አንዲት ፍሬ ቡና ሳያመርቱ የኢትዮጵያን ቡና በርካሽ እየገዙ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና ላኪ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ መሞከራቸው ልዩነቱን የሚያሰፋ ብልጣ ብልጥ ዕርምጃ በሚል ይነገራል፡፡
ዘገባው እንደሚለው ኮሚሽን የሚቀበሉበትን የወደብ መሠረተ ልማት ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ልታድስ ይገባል የሚል አቋም ኤርትራዊያኑ ይዘው ነበር፡፡ በሌላ በኩል በሶቪየት ኅብረት ድጋፍ ተገንብቶ በነበረው የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ አጠቃቀም ላይ ጥያቄ መፈጠሩ ይነገራል፡፡ ለኤርትራም ሆነ ለኢትዮጵያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውንና የጋራ ሀብት ሆኖ የሚታየውን የነዳጅ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ታድሰ መባሉ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ካሻከሩ ምክንያቶች እንደ አንዱ ይወሳል፡፡
በዚህ ሁሉና በሌሎችም ተደራራቢ ምክንያቶች ወደ ጦርነት የገቡት ኤርትራና ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በኋላ መልሰው ጉርብትናቸውን ለማደስ በመቸገራቸው የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት አማራጭ በጂቡቲ ላይ ብቻ የተገደበ ሆኖ እንደቆየ ይነገራል፡፡ የታሪክ ምሁሩ ዳግማዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. አልጄርስ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ ጉዳይ የተከደነ አጀንዳ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡ ከሺሕ ዓመታት በላይ ወደብ አጥታ የማታውቀዋ ኢትዮጵያ ‹‹የወደብ አልባነት ክስተት ገጠማት›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
አክሱም የአዱሊስ ወደብን በ702 ዓ.ም. በዓረቦች ወረራ በማጣቷ መዳከሟን ያነሱት ምሁሩ፣ ሆኖም በመካከለኛው ዘመን አገሪቱ እንደዘይላ ባሉ ወደቦች መገልገሏን ያወሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ አገሪቱ መልሳ ወደብ አልባ መሆኗ በብዙ መንገድ ለጉዳት እንደዳረጋት ነው የሚናገሩት፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አህመድ ሸዴ እ.ኤ.አ. ጁላይ 16 ቀን 2013 ላይ ለወደብ ኪራይ አገሪቱ በቀን ሁለት ሚሊዮን ዶላር ትከፍላለች ማለታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አሁን ድረስ ታወጣለች መባሉንም ተጨማሪ የጉዳት ማሳያ አድርገው አስቀምጠውታል፡፡
የዓለም አቀፍ ሰላም ጥናት መምህሩ አቶ ጋረደው አሰፋ በበኩላቸው፣ ‹ኢትዮጵያ እንደ አሰብ ባሉ ወደቦች ካልተጠቀመች ወደቡ የግመል መጠጫ ይሆናል› በሚል የተንሸዋረረ ዕይታ መሪዎቿ ታላቂቱን አገር ወደብ አልባ አድርገዋት መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ አገር መሆኗ አገራዊ የሥነ ልቦና መቃወስን የፈጠረ ጉዳይ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ወደብ አልባ መሆን ከሥነ ልቦና አልፎ ዲፕሎማሲያዊ መሽመድመድንም በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በ1985 ዓ.ም. የተመድ ዋና ጸሐፊ ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ኤርትራን ለማስገንጠል አዲስ አበባ ሲገቡ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሰባት ተማሪዎችን መግደሉና ብዙዎችን ማቁሰሉ የሚነገረው የያኔው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በወደብ ጉዳይ አንዳችም ምክረ ሐሳብም ሆነ ተቃውሞ እንደማይሻ ቁርጥ አቋም የያዘ ይመስል ነበር ይባላል፡፡
‘በጂቡቲ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆነን እንዴት ልንዘልቀው ነው’ የሚሉ ድምፆች መስሚያ አልነበራቸውም ይባላል፡፡ የጊዜው መንግሥት በወደብ ጉዳይ የሚነሱ ሐሳቦችንም ሆነ ሐሳብ ሰጪዎችን በቀናነት መመልከት የተወ እንደነበር ታሪክ ከትቦታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለቀይ ባህር የተሠሩ ፊልሞች ከመድረክ እንዲወርዱ መደረጉ ይነገራል፡፡ በአርቲስት ጥላሁን ጉግሳ የተሠራው ፊልም የገጠመው ዕጣ ይህ ነበር ይባላል፡፡ ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በ1997 ዓ.ም. በሠራው አልበም ውስጥ ያካተተው ‹ካብ ዳህላክ› ሙዚቃ ሕዝብ ቢወደውም የወቅቱን አገዛዝ ክፉኛ ያበሳጨ እንደነበር ይነገራል፡፡
የኢሕአዴግ አስተዳደር የባህር በር ጉዳይ አይነሳ ቢልም ጉዳዩ ጭርሱን ተዳፍኖ አለመቅረቱ ይነገራል፡፡ ታሪክን፣ ጂኦግራፊን፣ ኢኮኖሚንም ሆነ ጂኦ ፖለቲካዊ መነሻ ነጥቦችን ተመርኩዘው የባህር በርና የወደብ አስፈላጊነትን በየጊዜው ለመተንተን የሞከሩ ወገኖች ግን ኢትዮጵያ በኪራይ ወደብ ያውም በጂቡቲ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መዝለቁ እንደሚከብዳት ለረጅም ጊዜ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ከጂቡቲ ጋር 349 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ ጋር 912፣ ከኬንያ 861፣ ከሶማሊያ 1‚600፣ ከሱዳን 744፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን ጋር 1‚114 ኪሎ ሜትር የድንበር መስመሮችን የምትጋራውና ምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ለሚባለው ቀጣና እምብርት የሆነችው ኢትዮጵያ ያለ ወደብ መቅረቷ ብዙ አገር ወዳድ ዜጎችን ሲያሳስብ የቆየ ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ በየቀኑ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ በርሜል ነዳጅ ዘይት ለሚተላለፍበትና የዓለማችን ወሳኝ ንግድ መስመር ለሆነው ለቀይ ባህር ቀጣና የቅርብ ሩቅ ሆና መኖሯ ቢዳፈንም፣ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ ጉዳይ ነበር ይባላል፡፡ በየቀኑ ከ160 በላይ ግዙፍ የንግድ መርከቦች የሚቀዝፉበት ቀይ ባህር ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዓለም ዓመታዊ ንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ነው፡፡ የስዊዝ ቦይና የህንድ ውቅያኖስ መገናኛ የሆነው ቀይ ባህር የእስያንና የአፍሪካ አኅጉራትን ከአውሮፓ አኅጉራት ጋር የሚያስተሳስር የዓለም ቁልፍ የንግድ መስመርም ነው፡፡
ለንግድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናዊ ጆኦ ፖለቲካ ባለው ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የተነሳ ቀይ ባህር የዓለም አገሮች ትኩረትን የሚስብ ሆኖ ከሺሕ ዓመታት በላይ ዘልቋል፡፡ በተለይ የዚህ ቀጣና ወሳኝ የንግድ በር የሆነው በየመንና በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ መካከል ያለው ቀጭን የባህር በር የሆነው ባብ ኤልማንዴብ ከዓለም ኃያላን መንግሥታት ትኩረት ወጥቶ የማያውቅ ስለመሆኑ ይነሳል፡፡ የፋርስ ጦረኞች፣ የዓረብ ነጋዴዎች፣ ከታላቁ እስክንድር እስከ ኢብን ባቱታ በየዘመናቱ የተነሱ ኃያላን ወይም አገር አሳሾች የዚህን መስመር ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ መስክረውለታል፡፡ ሌላው ቀርቶ በየዘመናቱ የተነሱ የባህር ጃዊሳዎች ይህን መስመር መተላለፊያቸው ሊያደርጉት ሲሻሙ ኖረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ማርች 2021 ኤቨርግሪን የተባለች መርከብ ከእስያ ወደ አውሮፓ ቀይ ባህርን አቋርጣ ስትጓዝ ግብፅ ባለው የስዊዝ ቦይ ላይ በአሸዋ ደለል ተቀርቅራ ጉዞዋ ተሰናከለ፡፡ መርከቢቱ በአግድመት በመቀርቀሯ የስዊዝ ቦይ መተላለፊያ ለስድስት ቀናት ዝግ ሆኖ ቆየ፡፡ ይህ የአጭር ቀናት የስዊዝ ቦይ መዘጋት ደግሞ ወደ 9.6 ቢሊዮን ዶላር የዓለም ንግድ ልውውጥን ነበር ቀጥ አድርጎት የቆየው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 ብቻ ከባህረ ሰላጤው አገሮች የተነሳ 20 በመቶ ነዳጅ ዘይት እንዲሁም 40 በመቶ የተጣራ ጋዝ ወደ አውሮፓ ያመራው በባብ ኤል ማንዴብ ቀይ ባህርን በማቋረጥ ስዊዝ ቦይን ተሻግሮ ነው፡፡
በዓለም ላይ ካሉ ዕውቅና ያልተሰጣቸውን ጨምሮ 49 ወደብ አልባ አገሮች መካከል 120 ሚሊዮን ሕዝቦች፣ እንዲሁም 1.1 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላት ኢትዮጵያ በብዙ መመዘኛዎች ትልቋ ወደብ አልባ አገር ናት ይባላል፡፡ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 አገሮች ወደብ አልባ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በዓመት 17.1 ሚሊዮን ቶን ጭነት ነው በባህር (በጂቡቲ ወደብ) በኩል ከዓለም ጋር የምትገበያየው፡፡ ይህ የጭነት መጠን ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2030 ወደ 30 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ይባላል፡፡ ለዓመታዊ የወደብና ትራንዚት አገልግሎቶች በአማካይ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ትከፍላለች የምትባለዋ ኢትዮጵያ፣ በየጊዜው በሚጨምረው የወጪና የገቢ ንግድ መጠን የተነሳ የወደብ ወጪዋ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡
ጂቡቲ ለኢትዮጵያ የተመቻቸ የወደብ አገልግሎት ለመስጠት በየጊዜው ብዙ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን የሚያነሱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የሎጂስቲክስ መምህር ማቲዎስ እንሰርሙ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷ ሲበጠስ ከጂቡቲ ጋር የወደብና የጉምሩክ ስምምነት በመፈራረም ፊቷን ወደጂቡቲ ማዞሯን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ ወደብ እስከ ስምንት ቀን ዕቃ ማራገፍ በነፃ እንደሚፈቀድና እስከ ስድስት ወራት ደግሞ በክፍያ ማቆየት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ጂቡቲዎች ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት ለመስጠት ሲሉ ብዙ መሠረተ ልማት ዘርግተዋል፡፡ በመሠረተ ልማት፣ በዋጋም ሆነ በቅልጥፍና የጂቡቲን ወደብ መጠቀሙ ለኢትዮጵያ እጅግ አዋጭ ነው፤›› ሲሉ የሚናገሩት ምሁሩ፣ ከጂቡቲ ውጪ ወደብ ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡
የወደብ ባለቤት መሆን ለአንድ አገር የወደብ አገልግሎት ወጪን በመቀነስና ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን በመጨመር የተወሰነ ጠቀሜታ ብቻ እንደሌለው ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡ ሚስጥራዊነታቸው የተጠበቁ ሸቀጦችን ለመለዋወጥ ጭምር የወደብ ባለቤትነት ወሳኝ መሆኑን ያክላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የባህር በር ባለቤትነት የራስ ወደብ እንዲኖር ከማስቻል በተጨማሪነት በርካታ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ነው ብዙ ምሁራን የሚናገሩት፡፡ የባህር በር ያላቸው አገሮች ለባህር ወጀብ ወይም በባህር ለሚመጣ የውጭ ጠላት ጥቃት ይጋለጣሉ ካልተባለ በስተቀር፣ የባህር በር ለአንድ አገር ቁልፍ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ መሆኑ በሰፊው ይወሳል፡፡ በባህር ከመነገድ በተጨማሪ የባህር ሀብቶችን በማምረት ውጤታማ መሆን ይቻላል ይባላል፡፡ የባህር ኃይል መገንባትና ማጠናከርም ሆነ የባህር ምርምሮችን ማሰብ የሚቻለው የባህር በር ባለቤት ሲኮን ነው ይባላል፡፡ የባህር መዝናኛና ቱሪዝምም ቢሆን ከባህር በር ባለቤትነት ጋር የሚመጣ ነው ይባላል፡፡ በሌላ በኩል በቀጣናዊ ጉዳዮችም ጂኦ ፖለቲካዊ ሆነ በዓለም አቀፍ ጂኦ ፖለቲካዊ መድረኮች ልቆ መታየት የሚቻለው የባህር በር ባለቤት አገሮች ሲሆኑ ነው ይባላል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት በአመዛኙ በራሷ መሪዎች የተዛቡ ውሳኔዎች ይህን አጥታ ቆይታለች የምትባለዋ ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ግን ከባህር በር ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትኩረትን ስባለች፡፡ ጉዳዩን የቀሰቀሰው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በአዳማ ከተማ ለተሰበሰቡ የፓርላማ አባላት አደረጉት የተባለውና ‹‹ከጠብታ ውኃ እስከ ባህር ውኃ›› በሚል ርዕስ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ገለጻ ነበር፡፡
ስለቀይ ባህር፣ ስለወደብና ስለአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ሰፊ ትንታኔ የሰጡበት ይህ ገለጻ የጎረቤት አገሮችን ምላሽ ጭምር የቀሰቀሰ ነበር፡፡ ‹‹የዓባይ ጉዳይ በግብፅና በሱዳኖች ያለ ዕረፍት የሚነሳ አጀንዳ ሆኖ ሳለ እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለወደብና ስለቀይ ባህር ለማንሳት ለምን እናፍራለን?›› በማለት በጥያቄ የተንደረደሩት ዓብይ (ዶ/ር) በኢኮኖሚ፣ በጂኦግራፊ፣ በዘር፣ እንዲሁም በታሪክ መነሻነት ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን ጉዳይ ለማንሳት ሁሌም እንደምትገደድ አስረድተዋል፡፡
በዚሁ ገለጻ ላይ ዓብይ (ዶ/ር) የባህር በርና ወደብ ኢትዮጵያ ማግኘት ስለምትችልባቸው መንገዶች በሰፊው ዘርዝረዋል፡፡ በኃይልና በወረራ የሚለው አማራጭን የማያዛልቅና መፍትሔ የማይሆን ያሉት ዓብይ (ዶ/ር) በሰጥቶ መቀበል መርህ የወደብ ባለቤት አገሪቱ እንደምትሆን ጠቁመዋል፡፡ ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽንን እንዲሁም የመሬት ልውውጥን እንደ አማጭ ያቀረቡት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ዓለም አቀፍ ሕጎች ጭምር እንደሚደግፏት አብራርተዋል፡፡ በምን መንገድ ይመለሳል የሚለውን በእንጥልጥል የተውት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እኛ ጉዳዩን ብንተወው እንኳን የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይን ልጆቻችን አይተውትም በማለት ነበር፤›› የገለጹት፡፡
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ ተከትሎ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ሰንብተዋል፡፡ ከቀናት በኋላ ማለትም ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. 116ኛው የመከላከያ ቀን ሲከበር ዓብይ (ዶ/ር) ባሰሙት ንግግር ገለጻቸው የፈጠረውን ግብረ መልስ ለማረም ጥረት አድርገዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በማንም ተሸንፋ እንደማታውቀው ሁሉ ማንንም አገር ወራም አታውቅም፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ በወንድም የጎረቤት ሕዝቦች ላይ ቃታ እንደማትስብ ተናግረዋል፡፡ በሰላማዊ መንግድ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ሌላ ፍላጎት እንደሌላት አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በቀደመ ገለጻቸው ላይ የራስ አሉላ አባ ነጋን ‹‹የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ድንበር ቀይ ባህር ነው›› የሚል ተጠቃሽ ንግግር ዓብይ (ዶ/ር) መጠቀማቸውና ስለቀጣናዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ብዙ ነጥቦችን መነካካታቸው፣ በጎረቤት አገሮች ዘንድ የተለያየ ግብረ መልስ ነበር የፈጠረው፡፡
ጉዳዩ ‹‹እኛ የጉዳዩ ባለቤቶችን አስገርሞናል›› በማለት የገለጸው የኤርትራ መንግሥት ምላሽ፣ ስለቀይ ባህርና ስለባህር በር በአንዳንድ ወገኖች ብዙ መባሉ እንደማያስደንቀው ገልጿል፡፡ በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቅ በበኩላቸው አገራቸው የራሷን ሉዓላዊ ግዛት የማስከበር ሙሉ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡
የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ከፍተኛ አማካሪ አሌክሲስ መሐመድ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያና ጂቡቲ ወዳጅ አገር ናቸው፡፡ ሆኖም ጂቡቲ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ነፃ አገር ነች፡፡ ሉዓላዊነቷ ደግሞ በፍፁም ለድርድር አይቀርብም፤›› በማለት ምላሽ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡
አብዲረሺድ ሀሺ የተባሉ የሶማሊያ የቀድሞ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን በበኩላቸው የዓብይ (ዶ/ር) ገለጻ ሶማሊያን ሥጋት ላይ የጣለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሰው አገርን ሀብት፣ ሉዓላዊ ግዛትም ሆነ የግዛት አንድነት በኃይል ለመንጠቅ የሚከጅል ንግግር ከመናገር መቆጠብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ከተለያየ አቅጣጫ ምላሽ እያስተናገደ የሚገኘው የባህር በርና የወደብ አጀንዳ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ነው የሚመስለው፡፡ የጎረቤት አገሮች የኢትዮጵያ የመንግሥትን አቋም የወረራ ዝግጅትና ጠብ አጫሪነት ቢሉትም፣ መንግሥት ግን በሚዲያዎች ጉዳዩን በሰፊው አጀንዳ ማድረግን ቀጥሎበታል፡፡
እንደ ማርቲን ፕላውት ያሉ አስተያየት ሰጪዎች በፖለቲካ የተከፋፈለችዋን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያግዛል በሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ተቺዎች በበኩላቸው ዓብይ (ዶ/ር) የቀይ ባህር ጉዳይ አቅጣጫ ለማስቀየስ የተጠቀሙበት ስለመሆኑ እየተናገሩ ነው፡፡
አንዳንዶች የባህር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ከጂኦ ፖለቲካና ከዲፕሎማሲ ተጠቃሚነት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ በቀይ ባህር ቀጣና ብዙ የዓለም ኃያላን አገሮች ወደብ በመግዛት፣ በመከራየት አልያም የመርከቦቻቸውን መልህቅ በመጣል የተፅዕኖ ፉክክር ውስጥ መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡ በጂቡቲ እንኳን ጦር ያሠፈሩ ኃያላን አገሮች ከአሥር ያላነሱ እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ሽኩቻና ፉክክር በበዛበት ቀጣና የባህር በር ይኑረኝ ብትል ኃጢያቱ ምንድን ነው ሲሉም የመንግሥተን አቋም በመደገፍ ላይ ናቸው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ብስለት፣ ስክነትና ጥንቃቄ ያልጎደለው ስትራቴጂካዊ ዕርምጃን መከተል አስፈላጊ ነው የሚሉ ጥቂቶች ግን ኢትዮጵያ ግብታዊ ከሆነ የሚዲያ ዲፕሎማሲ እንድትወጣ በመምከር ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ከበቂ በላይ ችግሮች ታቅፋና በግጭት ቀውስ ተንጣ ሳለ ከጎረቤት አገሮች ጋር መፋጠጡ ተገቢነት የለውም ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጉዳዩ የአማራ ክልል ቀውስን ትኩረት ለማስቀየስ በተለይ የባህር በር ጥያቄን ለረጅም ጊዜ ሲደግፍ የቆየውን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ደጋፊውን ቀልብ ለመሳብ የተደረገ ነው የሚል ትችትም ሲቀርብበት ይታያል፡፡ ከጎረቤት አገሮችም ከውስጥም ተቃውሞ ያላጣው ሰሞንኛው የባህር በር ፖለቲካ ወዴት እንደሚያዘግም ግን አልታወቀም፡፡