- የብድር ክምችቱ ከ100 ቢሊዮን ብር ተሻግሯል
- –ያልተጣራ 5.07 ቢሊዮን ብር አትርፏል
በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት የአገር ውስጥ ባንክ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ያስተናገደበት ዓመት ቢሆንም ዳሸን ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ወደ 144.6 ቢሊዮን ብር ያደረሰበትና በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባሉ አፈጻጸሞችን ያስመዘገበበት መሆኑን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚና በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርትና ማብራሪያ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው ውጤት ከቀዳሚው ዓመት በብዙ መመዘኛዎች ብልጫ የታየበት መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይቼባቸዋለሁ ብሎ ከገለጻቸው መካከል በተቀማጭ ገንዘብ መጠን ያገኘው ውጤት አንዱ ነው፡፡
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ዱላ መኮንን በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት ባንካቸው በሒሳብ ዓመቱ 23.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ወደ 114.8 ቢሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ በ26 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 8.1 ቢሊዮን ብር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ባንኩ ከፍተኛ አፈጻጸም አሳይቼበታለሁ ብሎ የገለጸው አጠቃላይ ገቢውን በ39 በመቶ በማሳደግ ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ነው፡፡
ከዚህ ገቢ ውስጥ 74.8 በመቶ የሚሆነው ከብድር ወለድ የተገኘ ገቢ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር መጠንም ከፍተኛ የሚባል ዕድገት በማሳየት አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት መጠን ለመጀመርያ ጊዜ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ያሻገረበት ዓመት ሆኗል፡፡
የቦርድ ሊቀንበሩ በሪፖርታቸው እንደጠቀሱት ባንኩ በ2015 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከወለድ ነፃ የሰጠውን ብድር ጨምሮ በአጠቃላይ 22.2 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ማቅረቡን ጠቅሰዋል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት 28.15 በመቶ ዕድገት በማሳየት አጠቃላይ የባንኩ የብድር ክምችት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከ100.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ለባንኩ የብድር መጠን በከፍተኛ ደረጃ ማደግ የተለያዩ ምክንያቶችን የጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይ ግን በሒሳብ ዓመቱ ከወለድ ነፃ የሰጠው ብድር ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ጠቁመዋል። ከባንኩ የብድር ክምችት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ለአገር ውስጥ ንግድ የተሰጠ ብድር ሲሆን ለዚህ ዘርፍ የተሰጠው ብድር ከ30.38 ቢሊዮን ብር ላይ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት ውስጥ የአገር ውስጥ ንግድ ከያዘው የብድር ድርሻ በተጨማሪ ፣ ባንኩ ለገቢና ለወጪ ንግድ እንዲሁም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያቀረበው ብድር እንደ ቅደም ተከተላቸው 22.29 ቢሊዮን ብር እና 20.27 ቢሊዮን ብር ድርሻ መያዛቸውን ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡
በሌሎች የባንክ መመዘኛ መሥፈርቶች ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱን የገለጸው ዳሸን ባንክ፣ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 5.07 ቢሊዮን ብር ማትረፉንም አስታውቋል፡፡ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከቀዳሚው ዓመት በ31.9 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በሰጡት ማብራሪያ፣ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ተደራሽነቱን ይበልጥ ከማስፋትና አዳዲስ ደንበኞችን ከማፍራት ባሻገር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድ አዎንታዊ ውጤቶችን ያስመዘገበበት እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
እንደ ምሳሌ ከጠቀሱት መካከል ዳሸን ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት 253 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መክፈቱንና አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ወደ 835 ያደረሰበት ይህም የነበረውን የቅርንጫፎች ብዛት በአንድ ዓመት ውስጥ በ43.5 በመቶ ማሳደግ የቻለበት ነው፡፡
የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎቱም በየዓመቱ እየሰፋና እያደገ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ በ2015 መጨረሻ ላይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ በ36.7 በመቶ መጨመሩ ሌላው የባንኩ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ እንቅስቃሴውም የባንኩ የሀብት መጠን በ24.7 በመቶ በመጨመር 144.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ይህም የሆነው ባንኩ በአንድ ዓመት ውስጥ 28.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ሀብት ማሰባሰብ በመቻሉ ነው ብለዋል።
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየተሰበሰበ ያለው ተቀማጭ ገንዘብ በየዓመቱ ዕድገቱ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከ2013 የሒሳብ ዓመት ከወለድ ነፃ የተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 4.8 ቢሊዮን ብር፣ በ2014 ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2015 የሒሳብ ዓመት ላይ ደግሞ 8.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ለውጡን ያሳያል ብለዋል፡፡ የአስቀማጮች ቁጥርም በ83.2 በመቶ በማደግ 720,818 መድረሱን ተናግረዋል።
ከወለድ ነፃ የተሰጠውም ብድር በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ሲሆን በ2015 መጨረሻ ላይ የተሰጠው የብድር መጠን 5.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ63.7 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ በልዩ ሁኔታ አሳክቼዋለሁ ያለው በአገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ የመጀመርያ የሆነውን 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ብድር በቅርቡ ማግኘቱን ነው፡፡ ይህም በዘርፉ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ከመቅረፍና የግብርና ምርት ወደ ውጭ ከመላክ አንፃር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡
ባንኩ እንዲህ ያሉ አፈጻጸሞችን ቢያሳይም የሒሳብ ዓመቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በእጅጉ የተፈተነበት እንደሆነ የቦርድ ሊቀመንበሩና ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በኢትዮጵያ የነበረው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሁም ኢሚዛናዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ያመለከቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ በዋናነት የፀጥታ መደፍረስ፣ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝና የዋጋ መናር በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚው እንዲጎዳ አድርገውታል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የበጀት ጉድለትና የውጭ ብድር ጫና ዋነኞቹ ችግሮች ሆነው በዓመቱ መቀጠላቸውን አክለዋል፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ በቀጥታ ከሚመለከቱት አሉታዊ ክስተቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአገር ውስጥ ንግድ ባንኮች ከሚያቀርቡት አዲስ የብድር መጠን ውስጥ 20 በመቶውን በማስላት የብሔራዊ ባንክን የግምጃ ቤት ቦንድ (Treasury Bond) እንዲገዙ የሚያስገድድ መመሪያ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የመጀመሪያ ወራት ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉ በባንኮች የማበደር አቅም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ባንኮች ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ላይ አብላጫውን ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያዘው መመሪያም ሪፖርቱ በሚሸፍነው የሒሳብ ዓመት ተግባራዊነቱ በመቀጠሉ በባንኮች የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖው ማድረሱን የቦርድ ሊቀመንበሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
ሆኖም ግን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በመንግሥት በኩል የተለያዩ ዕርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን በዋናነትም የገንዘብና የምጣኔ ሀብት ማስተካከያ ዕርምጃ፣ የአክሲዮን ገበያ ማቋቋም፣ የታክስ መሠረቱን የማስፋት፣ የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ በስፋት ማውጣትና የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ የወጡ የባንክ ብድርን የሚመለከቱ መመርያዎች የባንኮችን የሀብት መጠን፣ የሥራ ማስኬጃና ተያያዥ ወጪዎችና ትርፋማነት ላይ ተፅዕኖ እንደነበራቸው የገለጹት አቶ ዱላ፣ በዘርፉ አዳዲስ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ሥራ መጀመራቸው ደግሞ በዘርፉ ያለውን ውድድር እያጠናከረው እንደሚሄድም ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ በቅርቡ እያደገ የመጣው የዲጂታል መሠረተ ልማት ለረዥም ጊዜ በባንኮች ብቻ ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ከባንክ ሥራ ዘርፍ ውጪ በሆኑ ተቋማት እንዲሰጥ መደረጉ ለባንኮች ጭምር ሰፊ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
‹‹በዓለም ላይ ኢትዮጵያ የዓለም ከፊል ስለሆነች በዓለም ላይ የሚኖሩ ተግዳሮቶች በባንካችን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያሳርፋል፤›› በማለት በሒሳብ ዓመቱ የነበሩትን ተግዳሮቶች ያብራሩት አቶ አስፋው በበኩላቸው፣ ‹‹የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ፈተና ውስጥ የወደቀበት ዓመት ‹‹ዓለም እያስቸገረ ያለው የዋጋ ንረት እኛንም እየፈተነን ነው›› ያሉት አቶ አስፋው በዚህ ምክንያት ማዕከላዊ ባንኮች ጠንከር ያለ የሞኒተሪ ፖሊሲ እንዲከተሉ ማስገደዱንም ገለጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታም በሚገባ እያስቸገረን ያለው ተፅዕኖ ማሳረፉን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህም ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ቅርንጫፎቻቸውን እስከ 50 በመቶ የዘጉባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡ የዋጋ ንረቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሒሳብ ዓመቱ ትልልቅ ከሚባሉ ተግዳሮቶች ውስጥ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰደ ያለው ጠንከር ያለ የሞንታሪ ፖሊስ እንዲሁም በአገር ደረጃ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች የራሳቸው ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡
ከሁሉም በላይ ግን በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ትልቅ ተግዳሮት ብለው የጠቀሱት የጥሬ ከገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ በገንዘብ ዝውውር ላይ አጋጥሞ የነበረውን ችግር ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ለጠቅላላ ጉባዔው የሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ባንካቸው የተለያዩ አማራጮች በመውሰድ ችግሩን መውጣት ቻለ እንጂ ሥራ የሰደደ ችግር እንደበር አመልክተዋል፡፡
‹‹ባለፉት ዓመታት የገንዘብ ፍሰት ላይ ችግር የገጠመበት ሁኔታ አለ፡፡ የውጭ ምንዛሪ መሠረታዊ ችግር በመሆኑ ደንበኞችን በሚፈለገው ደረጃ ማስተናገድ እየተቻለ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡
በተለይ ከባንክ ወደ ባንክ ገንዘብ ማስተላለፍ በጣም ከባድ የሆነበት ዓመት ነበር፡፡ በገንዘብ ፍሰት ችግር ውስጥ የገባበት ነው፡፡ ከባንኮች ወደ ባንኮች የገንዘብ ከማስተላለፍ ጋር ገጠመ ያሉትን ችግር ባንካቸው የተውጣጡ ቢሆንም ችግሩ አሳሳብ ስለመሆኑ ግን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ባንኩ ሾርት ተርም ኢንቨስትመንቶቻችን እንዲሁም ከውጭ በመሙላት ደንበኞቹን በአግባቡ ሊያስተናግድ ችሏል ብለዋል፡፡
በሌሎች የባንኩ የሥራ አፈጻጸምን በተመለከቱ ከተሰጡ መረጃዎች መካከል የባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን የተያያዘው ይገኝበታል፡፡ በቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት ዳሸን ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 11 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንኩን የተከፈለ ካፒታል 12 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በተወሰነው ውሳኔ መሠረት 885.69 ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች በሽያጭ ሒደት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ቀሪው 111.32 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በአጭር ጊዜ በመሸጥ የተከፈለ ካፒታሉን በአጭር ጊዜ 12 ቢሊዮን ብር ያደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የ12 ቢሊዮን ብሩ ካፒታል ከተሟላ በኋላ ግን እንደገና ካፒታሉን ለማሳደግ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራም ይጠበቃል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንደገለጹትም፣ ‹‹የ12 ቢሊዮን ብሩ ካፒትል ሙሉ ለሙሉ እንዳለቀ አዲስ የካፒታል ጭማሪ ለማድረግ በአጭር ጊዜ አስቸኳይ ጉባዔ እንደሚጠራ አሳውቀዋል፡፡
ዳሸን ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የደንበኞቹን ቁጥር ከ5.2 ሚሊዮን በላይ አድርሷል፡፡
ዳሸን ባንክ ባለፈው በሒሳብ ዓመት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን ለዚህም ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
ዳሸን ባንክ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ አጠቃላይ የሠራተኞቹ ቁጥር 17,571 ደርሷል፡፡