ሐዘን ሲነኩት የሚለሰልስ ግና ጅማታምና ጠንካራ የሆኑ ጥንድ እጆች ማለት ነው፡፡ ልቦችን ጨብጦ ይዞ ያጣምርና ያሰቃያል፣ ዋህድነት ብቸኝነት የሐዘን እንደራሴ ምስለኔ ነው፡፡ የማናቸውም መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ቅርብ የልብ ወዳጅ እንደ ሆነው ሁሉ፡፡ በዋህድና በባታይነት ኃይል ስሜትና በሐዘን ተፅዕኖ መሀል የተወጠረች የልጅ ነፍስ እየፈካች ያለችን ፅጌ ደንጎለት ትመስላለች፡፡ ነፋሱ ሽው ሲል ትንቀጠቀጥና ለወገግታ ጮራ መሀልዋ ትዘረጋለች፣ የምሽቱ ጥላ ቢመጣም ቅጠሎችዋን መልሳ ታጣጥፋለች፡፡ ያ ልጅ ሐሳቤን የሚከፍሉለት የጊዜ ማሳለፊያዎች ወይ ስሜቶቹን የሚጋሩ ወዳጆች ከሌሎች መፃኢው የወደፊት ሕይወቱ የሸረሪቶች ድር እንጂ ሌላ የማያይባት፣ የነፍሳቱን የመንፏቀቅ ድምፅን እንጂ ሌላ የማይሰማባት እንደጠባብ ሳር ቤት ትሆናለች፡፡
(የተሰበሩ ክንፎች፣ ካህሊል ጅብራን /ትርጉም ርቱዕ ኢምላክ/፣ 1999ዓ.ም.)