Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ተማሪዎች የሚማሩበትን ቋንቋ መገንዘባቸውንና መረዳታቸውን ካላረጋገጥን ውድቀቱ የሚቀጥል ይሆናል›› ብርሃኑ አሰፋ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተባባሪ ፕሮፌሰር ማዕረግ የኬሚካል ምህንድስና ክፍል መምህር

በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት ተዘጋጅቷል የተባለው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደምም በሙከራ ፕሮጀክት በተወሰኑ ትምህርት ቤቶችና ክፍሎች፣ ዓምና ደግሞ እስከ 9ኛ ክፍል ድረስ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ከአሥረኛ  እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መማር የጀመሩት ዘንድሮ ነው፡፡ ሆኖም በፍኖተ ካርታው ጥናት መሠረት ነው በሚል በአሥረኛ ክፍል የነበረው የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ ፈተና  ታጥፎ ተማሪዎች አራት ዓመታት ከተማሩ በኋላ፣ የ12ኛን ብሔራዊ ፈተና እንዲወስዱ መደረግ የጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት በ2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም በተሟላ የትምህርት ግብዓትና ጥራት ባለው ትምህርት ላላለፉት በመቶ ሺሕ ለሚቆጠሩ ተማሪዎች ሸክም ስለመሆኑ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተመዘገበው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና  ተፈታኞች የ97 በመቶ ወድቀት አንዱ ማሳያ መሆኑ ይነገራል፡፡ ብርሃኑ አሰፋ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተባባሪ ፕሮፌሰር ማዕረግ በኬሚካል ምህንድስና ክፍል መምህር ናቸው፡፡ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በተደረገው  የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ በዋና ተመራማሪ ሆነው ከተሳተፉ ምሁራን አንዱ ናቸው፡፡ ለፍኖተ ካርታው ግብዓት በተዘጋጀው ጥናት በተሰጡ ግብረ መልሶችና በአተገባበራቸው፣ እንዲሁም በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምሕረት ሞገስ ከእሳቸው ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ከመዘጋጀቱ አስቀድሞ ለግብዓት የሚሆን ጥናት አድርጋችሁ ነበር፣ የጥናቱ መነሻ ምን ነበር?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በ2007 ዓ.ም. አካባቢ በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ነበሩ፡፡ በርካታ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ሥራ አላገኙም ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሰላም ችግሮች በየገጠሩና በየከተማው ነበሩ፡፡ የተለያዩ ስያሜ ቢሰጣቸውም የተለያዩ አመፆችና ሥር የሰደዱ ችግሮች ነበሩ፡፡ በመሆኑም የመንግሥት አካላት ያጋጠመውን ችግር ለማርገብ በየከተማውና በየገጠሩ ወጥተው ሕዝቡን ሲያወያዩ ነበር፡፡ ከትምህርት ቤት የወጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ አጥነት አገራዊ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ቀድሞም ግልጽ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ አመፅ ሲቀየር ነው መንግሥት ማየት የጀመረው፡፡ በወቅቱ ከማኅበረሰቡ የተገኘው መልስ ልጆቹ ምን ያድርጉ፣ በተማሩት ትምህርት ሥራ የማያገኙ ከሆነ እንዴት አድርገን ልጆቻችንን ልንገራ እንችላለን የሚል ነበር፡፡ በዚህ ዕድሜ ቤተሰብ ልጆቹን ሊቆጣ አይችልም፡፡ በራሳቸው የሚወስኑበት ዕድሜ ላይ ናቸው፡፡ ይልቁንም ልጆቹን እንዴት እንዳስተማራችሁ ቆም ብላችሀ አስቡ፣ ተምረው ለወጡትም ሥራ ፍጠሩላቸው የሚል ነበር ከሕዝብ የመጣው መልስ፡፡ በኋላም በወቅቱ የነበረው ገዥ ፓርቲ ተሰብስቦ የትምህርት ሒደት እንዲገመገም ወሰነ፡፡ ኃላፊነቱም ለትምህርት ሚኒስቴር ተሰጠ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የተሰጠው ኃላፊነት ምን ነበር?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲና ስትራቴጂና ተዛማጅ ነገሮችን እንዲፈትሽ፣ የትምህርት ሥርዓቱን እንዲገመግም፣ የተከሰተው ምንድነው የሚለውን እንዲያይ፣ ተማሪ በምህንድስና፣ በግብርናና በሌሎች የተለያዩ ሙያዎች ተመርቆ ለምንድነው ሥራ ማግኘት ያቃተው? አሠሪዎችስ ባለው ሥራ እንኳን ክፍት ቦታ እያላቸው መቅጠር ያልፈለጉትና ለምሩቃን ሥራ መፍጠር ያልተቻለው የሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲታዩ ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቀማትና ማሠልጠኛዎች የተመረቁ ወጣቶች በአሠሪዎች፣ በፋብሪካ ባለቤቶችና በተለያዩ ድርጅቶች ምሩቃኑ ችሎታ የላቸውም በሚል ተፈላጊ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው ተብሎ እንዲጠና መደረግ ነበረበት፡፡ 

ሪፖርተር፡- ጥናቱን ካከናወኑት ምሁራን አንዱ እርስዎ ነበሩ፣ መሠረታዊ ችግሩ ምን ሆኖ ተገኘ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የቤት ሥራው የተሰጠው ለትምህርት ስትራቴጂ ማዕከል ነበር፡፡ ማዕከሉ ሰላሳ ስድስት አጥኚ ምሁራን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መልምሎ ወደ ሥራው ተገባ፡፡ ዋናው ችግሩ ምንድነው? ምን ደረጃ ላይ ነው ያለነው? ወዴትስ እንሂድ? የሚሉትን የጥናት ኮሚቴው እንዲሠራ ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ በወቅቱ የነበረውን የሥራ አጥነት ችግር መንስዔ አውቆ ሊፈታ የሚችል የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሥርዓተ ትምህርት እንደገና ለመዘርጋት ነው ጥናት የተደረገው፡፡ ጥናቱ ያሉትን የትምህርት ሚኒስቴር ሰነዶች ዓይቷል፡፡ ውጤታማ ትምህርትና ሥልጠና እንዴት እንሄድበታለን የሚለውን ለመመለስ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ተሞክሮ ለማየት  ብዙ  የምርምር ጽሑፎች ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡ በየክልሉ በመሄድ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች፣ መምህራንና ምሩቃን ምን እንደሚሉ፣ ቀጣሪዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ወይም ምክትሎቻቸው፣ የፓርላማ አባላት ያላቸውን ሐሳብ አሰባስበናል፡፡ በመጨረሻ ግልጽ ሆኖ የወጣው ሐሳብ ተማሪዎቹ በቂ ዕውቀት ያልያዙ መሆናቸው፣ ለቀጣሪዎች የሚያስፈልገው ክህሎት እንደሌላቸው፣ በራሳቸው ካለመተማመናቸው የተነሳ ምንም ዓይነት የሥራ ተነሳሽነት እንደሌላቸው፣ ለዚህም ብዙ ችግርች አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ነው የታየው፡፡

ሪፖርተር፡- ለእነዚህ ችግሮች መንስዔዎች ምን ነበሩ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ብዙ ጉድለቶችን እንደ መንስዔ ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛውንና ግልጽ የሆነውን ለማንሳት ያህል በየደረጃው ይሰጥ የነበረው ትምህርት ጥራትና ተገቢነት  ሥር የሰደደና ሰፊ ችግር የነበረበት መሆኑ ለችግሩ መንስዔ መሆኑ በጥናቱ ታይቶ ነበር፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያለው ትምህርት ሲገመገም የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ጥራት ችግር የሁለተኛ ደረጃን ትምህርት የጥራት ችግር እያወሳሰበ፣ ከዚያ በላይ ያሉትም የሙያና የዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ሥልጠና ውጤት እንዲበላሽ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ አብዛኞቹ ተማሪዎች የየደረጃውን ትምህርት ለመቀበል የሚያስችል የቋንቋ፣ የዕውቀትና የሥነ ልቦናም ዝግጅት ሳይኖራቸው ነበር የሚማሩት፡፡

ሪፖርተር፡- የትምህርት ሚኒስቴር ይህን የእናንተን ጥናትና ውጤት ለአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መነሻና ግብዓት አድርጎ እንዲያዘጋጅ ታሳቢ ተደርጎ ነበር? ይህስ ሆኗል ብለው ያምናሉ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ጥናቱ የተሠራው ለአዲሱ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ግብዓት እንዲሆን ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ግብዓቱን ወስዶ የፍኖተ ካርታ ዝግጅት ሴክሬታሪያት ብሎ አቋቋመ፡፡ አብዛኞቹ የሰክሬታሪያቱ አባላት የፍኖተ ካርታው ካጠኑት ምሁራን አልነበሩም፡፡ በወቅቱ የነበሩት የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች በራሳቸው መንገድ ያቋቋሟቸው ነበሩ፡፡ ቢሆንም ሴክሬታሪያቱ የፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረ ሐሳብ ግብዓት አድርጎ ይሠራሉ ተብሎ ነበር የተወሰደው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለውይይት ሲጠሩን መካተት ያለባቸውን ምክረ ሐሳቦችና መስተካከል ያለባቸውን እያነሳን ተከራክረናል፣ ሐሳብ ሰጥተናል፡፡ ወደ ሥራ እስኪተረጎም ድረስ ምን እንደተወሰደና ምን እንደተዘለለ እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡

ሪፖርተር፡- ካነሳችኋቸው ነጥቦች መካከል ቢጠቅሱልን?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- አዲሱ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ከሥርዓተ ትምህርት አንፃር እንዲካተቱ ከተሰጡት ምክረ ሐሳቦች አንዱ፣ ተማሪዎች የሚማሩበትን ቋንቋ በትክክል ማወቃቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚለው ይገኝበታል፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ተማሪ ሲያስተምር የሚያስተምርበትን ቋንቋ ማወቁን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የፍኖተ ካርታው አጥኝዎች ይህ ቁልፍና በመሠረታዊ ነገር በፖሊሲና በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ በእውነት ተማሪዎች የደረጃቸውን ትምህርት እንዲማሩና እንዲገነዘቡ ከፈለግን አስቀድመን ልንሠራበት የሚገባ መሠረታዊ ነጥብ ነው፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት አንስቶ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሚማሩበትን ቋንቋ ያውቁታል ወይ የሚለውን ሳናረጋግጥ የትምህርት ጥራትን ማምጣት አንችልም፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚማርበትን ቋንቋ በትክክል የሚጽፍበት፣ የሚያነበው፣ የሚናገርበትና የሚሰማበት ካልሆነ ዕውቀትን ከመግዛት አንፃር ትልቅ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ግልጽ ነበር፡፡ አሁን የታየውም ውጤት ይህ ችግር ባለመቀረፉ ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በምናይበት ጊዜ ሦስተኛ ክፍል ካሉ ተማሪዎች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ክፍል ቆጠሩ እንጂ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም ቢሆን ማንበብ አይችሉም ነበር፡፡ አራተኛ ክፍል ላይም ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሄዶ ስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና (ሚኒስትሪ) በሚፈተኑበት ጊዜ የራሳቸውን ቋንቋ አያልፉም፣ ሁለተኛ ደግሞ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የተማሩበትን እንግሊዝኛ አያልፉም፡፡ አፍ የፈቱበትን ቋንቋ አለማወቃቸው ሌሎች ትምህርቶችን በእንግሊዝኛ ሲወስዱም ሆነ እንግሊዝኛ ትምህርትን እንደ አንድ ትምህርት ሲማሩ በትክክል አለመገንዘባቸው ስምንተኛ ክፍል ውጤት ላይ ታይቷል፡፡ ይህንን የትምህርት ሚኒስቴር ያጠናውም ጥናት ያሳያል፡፡ ስምንተኛ ክፍል ላይ በእንግሊዝኛ ትምህርትተ 28 በመቶ ተማሪዎች ናቸው 50 በመቶና ከዚህ በላይ ውጤት እያመጡ ያልፉ የነበረው፡፡ ከስምንተኛ በኋላ የሚቀጥለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሁሉንም በእንግሊዝኛ የሚማሩበት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ፈተና የመናገርን፣ የመስማትን፣ የመጻፍን ሳይሆን ማንበብ መቻልን ወይም ዘዬውን ነው የሚፈተኑት፡፡ ብዙ ተማሪዎች እንግሊዝኛውን እንደ ቋንቋ እንኳን ሳያልፉ ትምህርቶችን ሁሉ በእንግሊዝኛ እንዲማሩ ይገደዳሉ፡፡ ይህ መሠረታዊ የቋንቋ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው 10ኛ ክፍል ላይ ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው እንግሊዝኛ 50 በመቶና ከዚህ በላይ አምጥተው የሚያልፉት ተማሪዎች ከ10 በመቶ አይበልጡም፡፡ ከ10ኛ ክፍል ተማሪዎች 20 በመቶ የሚሆኑት ናቸው በ11ኛ እና 12ኛ ክፍል የሚሰጠው የዩኒቨርሲቲ መሰናዶ ትምህርት የሚገቡት፡፡ ወደ መሰናዶ ከገቡት ውስጥ 35  በመቶው የእንግሊዝኛ ፈተና  50 በመቶ አምጥተው ነው የሚያልፉት፡፡ ሆኖም ዱሮ በነበረው አሠራር አብዛኞቹ የመሰናዶ ተማሪዎች  ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ይማሩ ነበር፡፡ 10ኛ ክፍል ከጨረሱት 70 በመቶ ወይም 80 በመቶ በቴክኒክና ሙያ ይሠለጥናሉ፡፡ አብዛኛው ወደ ቴክኒክና ሙያ የሚሄዱት እንግሊዝኛ የማያውቁ ናቸው፡፡ ለቴክኒክና ሙያ የሥልጠና መጻሕፍት የሚዘጋጁት በእንግሊዝኛ ነው፡፡ መምህሩ በእንግሊዝኛ ያስተምራል፣ ተማሪውም በእንግሊዝኛ የተማረውን ይረዳል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ መረጃዎችና ጥናቶች የቋንቋ አረዳድ ችግር ወይም አለማወቅ መኖሩን እያሳዩን ለብዙ ዓመታት ይኼንኑ ተከትለን ስንጓዝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን በጥናታችሁ ምን ምክረ ሐሳብ ሰጣችሁ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ይህ ልጆቹ ሥልጠና እየወሰዱ ወይም እየተማሩ እንዳልነበር የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም ጥናቱ በዩኒቨርሲቲም፣ በቴክኒክና ሙያም፣ በሁለተኛ ደረጃም የሚሰጠው ትምህርት እንግሊዝኛ ማወቃቸውን ወይም የመማሪያ ቋንቋውን ማወቃቸውን ሳናረጋግጥ በማስተማራችን ትምህርት እየወሰዱ አልነበረምና ይህ ይቀየር የሚል ሐሳብ በፍኖተ ካርታው እንዲገባ ነው የመከርነው፡፡ ተማሪዎች በየደረጃው ለሚሰጠው ሥልጠና፣ ሥልጠናው የሚሰጥበትን ቋንቋ ማወቃቸው ይረጋገጥ፣ ወይም ሥልጠናው ተማሪዎች በሚያውቁት ቋንቋ ይሰጥ በሚል አማራጩን ክፍት አድርጎ ነው ጥናቱ የተወው፡፡ ይችላሉ ከተባለ በእንግሊዝኛ ይሰጣቸው፣ ካልሆነ እንግሊዝኛ ላይ የተለየ ሥልጠና ተሰጥቶ ቋንቋውን መቻላቸው ሲረጋገጥ በእንግሊዝኛ ይሰጥ፣ ይህ ካልተቻለ ግን ልጆቹ በሚችሉት ቋንቋ ሥልጠና ይሰጥ ነው ሐሳቡ፡፡ ካልሆነ ግን ትምህርትና ሥልጠና ብንሰጥም ልጆቹ ዕውቀት እየተቀበሉ አይደለም ነው ያልነው፡፡

ሪፖርተር፡– አማራጭ የመማሪያ ቋንቋ ፖሊሲው ውስጥ ይካተት የሚል ሐሳብ በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ወቅት በነበሩ ውይይቶችም ይነሳ ነበር፡፡ እርስዎም ይህንን ሐሳብ ይደግፋሉ፡፡ ተግባራዊ አለመሆኑ የሚፈጥረው ችግር አለ?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- የማስተማሪያ ቋንቋ እንግሊዝኛ ይሁን ብለን የማሠልጠኛ ማቴሪያሎችን በእንግሊዝኛ አዘጋጅተን የምናስተምረው ቋንቋውን ለማይችሉ ሰዎች ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የሚደረግ ነው፡፡ ይህንን ማስተካከል ይቻል የነበረ ቢሆንም አልተደረገም፡፡ የመምህሩን የቋንቋ ችሎታ ስናይ፣ የአሠልጣኞች ችሎታ ስናይ፣ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲያስተምሩ ይመለመሉ የነበሩ መምህራንን ስናይ ከፍተኛ ክፍተት አለ፡፡ ዩኒቨርሲቲ በብዛት በተስፋፋበት ጊዜ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ለመመልመል ከ3.25 በላይ አጠቃላይ ውጤት ያላቸው እንዲያመለክቱ ተጠይቆ ፈተናው በትምህርት ሚኒስቴር ተሰጥቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ለዕጩ የዩኒቨርሲቲ መምህርነት አመልክተው ከፍተኛ ነጥብ አላቸው ተብለው ከተፈተኑ ዘጠኝ ሺሕ አመልካቾች አራት በመቶ አይሞሉም የእንግሊዝኛ ፈተና ያለፉት፡፡ ስለዚህ የእንግሊዝኛ ቋንቋን አለማወቅ መሠረታዊ ችግር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ዛሬ ሳይሆን በደርግ ጊዜ ጭምር ይታወቃል፡፡ የፈተናዎች ኤጀንሲ መረጃም ይህንኑ ያሳያል፡፡ የተለያዩ ተመራማሪዎችም አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የምንፈልግ ከሆነ እንደ ማኅበረሰብ የምንግባባት ቋንቋ ያስፈልጋል፡፡ ያ ቋንቋ ነው ትምህርት ሊሰጥበት የሚገባው የሚል እምነትም አላቸው፡፡ ምክንያቱም ይህ ዕውቀት ነው ወርዶ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ ዘመናዊ ሊያደርግ የሚችለው፡፡ አማራጭ የመማሪያ ቋንቋ ፖሊሲ ይኑር ብለን ሐሳብ ብንሰጥም ፍኖተ ካርታው ይህንን አልያዘም፡፡ ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ ውሳኔ ነው፣ ግን የትም አያደርሰንም፡፡ እንግሊዝኛ መሠረታዊና ወሳኝ ቢሆንም፣ ሁሉም በዚህ ቋንቋ መማርና መሠልጠን ይችላል ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው አማራጭ የመማሪያ ቋንቋ ፖሊሲ ያስፈልገናል ያልነው፣ ይህ ግንዛቤ ውስጥ አልገባም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ብቁ ካልሆኑ የማያልፉበት አካሄድ ይስተካከል ብላችሁም ነበር፡፡ ይህን እንዴት ይገልጹታል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- አንደኛ ደረጃ ላይ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚወድቅ ተማሪ አልነበረም፡፡ ይህ ተማሪው ራሱን በራሱ ችሎ የሚያልፍና መምህራኑ ልጆቹን አብቅተው ወደ የሚቀጥለው ክፍል ያሳፋሉ የሚል ከውጭ የተቀዳ አሠራር ነው፡፡ ይህ ከፊንላንድ ነው የተወሰደው፡፡ በፊንላንድ መምህራኑ ብቁ ናቸው፡፡ አምስት ወይም አሥር ልጆችን ኃላፊነት ወስደው ነው እየተከታተሉ ለሚቀጥለው ደረጃ የሚያደርሱት፡፡ መጀመርያ ቋንቋ መቻላቸውን ያረጋግጣሉ፣ አካባቢያቸውን መግለጻቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ባሉበት ደረጃ አነስተኛ የሚባለውን ማወቃቸውን ማረጋገጥ የመምህሩ ኃላፊነት ነው፡፡  በእኛ አገር ሁኔታ የመምህራን ብቃት ባልተረጋገጠበት፣ የትምህርት ቁሳቁስ ባልተሟላበት ነው ወደ ትግበራ የተገባው፡፡ ሳናስተምር፣ ፊደል ቆጠረም አልቆጠረም ችሎታ ሳይኖርና መሠረታዊ ዕውቀት ሳያገኝ እስከ አራተኛ ክፍል ይደርሳል፡፡ ይህ በፍጥነት ይታረም ነው ያልነው፡፡ ይህ ዘንድሮም አልተለወጠም፡፡ ከአምስተኛ ክፍል እስከ ስምንት ያለው ትምህርት የበለጠ ከበድ እያለ ነው የሚሄደው፡፡ የኢሕአዴግ የትምህርት ፖሊሲ ብቁ ገበሬ እናፈራለን፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ነውና ሊዳረስ ይገባል፣ እንደ አገር ዕድሜው ለትምህርት የደረሰ ሁሉ ትምህርት ሊደርሰው ይገባል የሚል ዓላማ ስለበረው ትምህርቱ ብዙ ነገሮች ታጭቀውበታል፡፡ ከአምስት እስከ ስምንት ባለው ደግሞ ይዘቱም ከበድ ያለ፣ ወደ አፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርቱ ተተርጉሞ የሚሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ከታች ከአንድ እስከ አራተኛ ተማሪዎች የሚመጡበት ሁኔታ ሲታይ፣ ትምህርቱ ከአምስት እስከ ስምንተኛ ድረስ መክበዱ ሲታይ ችግሩ የበለጠ ተወሳሰበ፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በደንብ መረዳት ሳይችሉ፣ ከአምስተኛ ክፍል በኋላ የታጨቁትን ዕውቀት ለመረዳት ችግር ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም በርካታ ተማሪዎች የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ይወድቃሉ፡፡ አንደኛ ክፍል ከጀመሩ ተማሪዎች ስምንተኛ የሚጨርሱት 20 በመቶ አይሞሉም፡፡ በየደረጃው እየተንጠባጠቡ ይቀራሉ፣ ስለዚህ ይህ ይስተካከል ብለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘጠኝ እስከ አሥር ያለውም ቢሆን በወቅቱ ችግር እንደነበረበት ተወስቷል፡፡ ከጥናታችሁ ጋር አያይዘው ቢገልጹልን?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- በዚህ ደረጃ ያለውን የትምህርት ይዘት ስንመለከት በኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ጊዜ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ይሰጥ የነበረው ነው ታጭቆ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲሰጥ የተደረገው፡፡ ይህ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት 10ኛ ክፍል ያልቃል ከሚለው ፖሊሲ የመነጨ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ያሉት 11ኛ እና 12ኛ ክፍሎች የከፍተኛ ትምህርት የመጀመሪያ ዓመት የዝግጅት ትምህርት ናቸው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ዝግጅት ተብሎ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ፍሬሽማን ኮርስ የሚባለው የበለጠ ተስፋፍቶ፣ በፍሬሽ ማን በመጀመሪያ ሴሚስተር ይሰጥ የነበረው ለ11ኛ ክፍል፣ በሁለተኛ ሴሚስተር ይሰጥ የነበረው ለ12ኛ ክፍል ይሰጥ ነበር፡፡ ትምህርትን ለሚችሉት ሳይሆን ለሁሉም ለማዳረስ አጭቀን ማስተማራችን ዋጋ አስከፍሎናልና መስተካከል አለበት የሚል ምክረ ሐሳብም ሰጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት እንዲስተካከል ነው ምክረ ሐሳብ የሰጣችሁት? በሰጣችሁት መሠረት ተተግብሯል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ከዘጠኝ እስከ አሥር የነበረውን አስፋፍተን ከዘጠኝ እስከ 12ኛ እናስተምር ነበር ያልነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ሁሉም ዩኒቨርሲቲ ሊገቡ ስለማይችሉ ለሙያ ቅርበት እንዲኖር የምናስተምረውን ተግባራዊ ወይም ሙያ ይደረግ ብለናል፡፡ ሳይንሱ ለምን ዓይነት ሙያና ልማት ያገለግላል የሚለውን ተጨባጭ ነገሮች ምሳሌ እያደረግን እናስተምራቸው ብለናል፡፡ ይህ በአራት ዓመት ውስጥ ተማሪዎች የተግባሩንም፣ የንድፈ ሐሳቡንም በጥሩ ሁኔታ ተምረው እንዲወጡ ያስችላል ብለን መክረናል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ትምህርት ከቴክኖሎጂና ከሜድስን (ሕክምና) ውጪ ለሦስት ዓመትም ነበር የሚሰጠው፡፡ ስለዚህ ከ11 እስከ 12ኛ ክፍል የሚሰጠው የፍሬሽማን ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲመለስ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሦስት ዓመት ይሰጥ የነበረው አራት ዓመት እንዲሆን፣ ቴክኖሎጂ አምስት ዓመት፣ ሜድስን ሰባት ዓመት ይስተካከል በሚል ነው ለፍኖተ ካርታው ግብዓት የተዘጋጀው ጥናት የመከረው፡፡

ሪፖርተር፡- የዩኒቨርሲቲው ተስተካክሏል፡፡ ነገር ግን ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባለው የአሥረኛ ክፍል ፈተና ቢቀርም፣ ፍኖተ ካርታውን መሠረት አድርጎ ተዘጋጅቷል ለተባለው ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ መጻሕፍት በአብዛኛው ከቀደመው የተለዩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ምን አስተያየት አለዎት?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- ከሰጠነው ምክረ ሐሳብ የተወሰነ ቁንፅል ሐሳብ ወስዶ ሌላው ሳይታይ የተሄደበት አካሄድ አለ፡፡ ከዘጠኝ እስከ አሥር ይሰጥ የነበረው ትምህርት ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ይሰጥ ያልነውን በተሳሳተ መንገድ ሰነዱ ሳይነበብ የተተረጎመ ይመስለኛል፡፡ በፊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይዘት አሥረኛ ላይ እንዲያልቅ ሲደረግ እስከ 12ኛ ክፍል የነበረው ትምህርት ታጭቶ ነው ከዘጠኝ እስከ አሥር እንዲማሩ የተደረገው፡፡ እዚህ ላይ ከጥናቱ ግብዓት በቁንፅል ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ይማሩ የሚው ብቻ ተወስዶ ላለፉት አራት ዓመታታ በፊት የነበረው ሥርዓተ ትምህርት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ስለዚህ ያገኘነው የ12ኛ ክፍል ዝቅተኛ ውጤት የሚጠበቅ ነበር፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ለምን ውጤት አልተሻሻለም ብለው ሲሟገቱ እናያለን፡፡ ነገር ግን የ11ኛና 12ኛ ክፍል የነበረው የቀደመው ሥርዓተ ትምህርት ማለትም ዩኒቨርሲቲ ፍሬሽማን ሥርዓተ ትምህርት የነበረው ሳይወጣ፣ የምክረ ሐሳቡ ይዘት ሳይወሰድ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ከዘጠኝ እስከ አሥር ቀድሞ እስከ 12ኛ ይሰጥ የነበረው ትምህርት ታጭቶ ይማራሉ፣ 11ኛ እና 12ኛ በፍሬሽማን ትምህርት የተቀረጸውን ይማሩና የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና እስከ አሥር የተማሩት የታጨቀ ትምህርት ላይ የፍሬሽማኑ ሥርዓት ትምህርት ተጨምሮ ይፈተናሉ፡፡ በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲ በአንድ ዓመት ይሰጥ የነበረው ተከፋፍሎ ከ11 እስከ 12 በሁለት ዓመት ይሰጥ የነበረውና ድሮ እስከ አሥር ይሰጥ የነበረውና የአራት ዓመት ትምህርት የታጨቀበትን ሥርዓተ ትምህርት፣ በጣም ጎበዝና ልዩ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች ይችሉት ይሆናል እንጂ ሌላው ተማሪ አይቋቋመውም፡፡ ለዚህም ነው በዓምናም ሆነ በካቻምና የ12ኛ ብሔራዊ ፈተና ውጤት 97 በመቶ ተማሪ የወደቀው፡፡ ተማሪዎች በዚህ ሁኔታ እንዲማሩና እንዲፈተኑ ከተደረገ ደግሞ ይህ ውጤት የሚጠበቅ ነው፡፡ በድሮው ከዘጠኝ እስከ አሥር ይማሩ ከነበሩትና 10ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከሚፈተኑት በአማካይ የሚያልፉት ከ15 እስከ 20 በመቶ ብቻ ነበሩ 50 በመቶና ከዚህ በላይ የሚያመጡት፡፡ ከፍኖተ ካርታው ግብዓት ምክረ ሐሳብ አንፃር እነዚህ ተማሪዎች በሁለት ዓመት ሲወስዱት የነበረው በአራት ዓመት ሰፋ ተደርጎ ተሰጥቶ ቢሆን የተሻለ ዕውቀት ሊይዙ ይችሉ ነበር፡፡ 12ኛ ሲፈተኑም ወደ 40 በመቶ ያህል ያልፋሉ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ ዓምና የተፈተኑትን ብናይ ከዘጠኝ እስከ አሥር፣ በድሮ እየተማሩ አሥረኛ ብሔራዊ ፈተና ሳይፈተኑ 11 እና 12ኛን የፍሬሽማን ወሰዱ፡፡ ከዚያም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ተፈተኑ፡፡ ተማሪዎቹ ያለ ፈተና ነው 11ኛ ገብተው ቀድሞ የዩኒቨርሲቲ መሰናዶ የምንለውን የተማሩት፡፡ ድሮ 10ኛ ከተፈተኑት የሚያልፉት 20 ከመቶ ከነበሩ፣ ያለ ምንም ልየታ ቀሪዎቹ 80 በመቶ ተጨምረው ሙሉ ለሙሉ ወደ 11ኛ አልፈው፣ 12ኛ ሲደርሱ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ወሰዱ፡፡ ቀድሞ 20 በመቶ ብቻ ከነበረ መሰናዶ የሚገባው፣ ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ ብቻ ከነበረ፣ 50 በመቶና ከዚህ በላይ አምጥቶ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው በድሮውም አካሄድ ቢኬድ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ያልፋል ተብሎ የሚጠበቀው ስድስት በመቶ ነው፡፡ አሁን ስርቆት ስለተከለከሉ፣ ወደ ማያውቁት ቦታ ሄደው ስለተፈተኑ በሥነ ልቦናና በሌሎች ችግሮች አስተዋጽኦ አድርገው ያለፉ ሦስት በመቶ ያህል ሆነዋል ይባላል፡፡ ነገር ግን 97 በመቶ ተማሪዎች የወደቁት ዛሬ ላይ ኩረጃ ቀርቷል ስለተባለ ሳይሆን፣ ቀድሞንም ትምህርቱን አውቀውት ስላልመጡ ነው፡፡ ኩረጃ ነበር በሚባልበት ጊዜም ቢሆን ከዚህ ቁጥር ብዙም የተለየ ተማሪ 50 በመቶና ከዚያ በላይ አያመጣም ነበር፡፡ በድሮ ሥርዓትም ቢሆን 50 በመቶና ከዚያ በላይ አምጥተው የሚያልፉት ከስድስት በመቶ በላይ አልነበሩም፡፡

ሪፖርተር፡ከመጻሕፍት ዝግጅት አንፃር በተለይ የሁለተኛ ደረጃን እንዴት ያዩታል?

ብርሃኑ (ዶ/ር)፡- አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ግብዓት መሠረት አድርጎ የተሠራ ነው ለማለትም አያስደፍርም፡፡ የተወሰኑ የሁለተኛ ደረጃ መጻሕፍትን ከሶፍት ኮፒው ለማየት ሞክሬ ነበር፡፡ ለምሳሌ የ12ኛ ክፍል ሒሳብ መጽሐፍ ቀድሞ ከነበረው የፍሬሽማን ኮርስ መሠረት አድርጎ ከተዘጋጀው የተለየ አይደለም፡፡ ከአንድ ምዕራፍ በስተቀር ካልኩለስ፣ ዴሪቬቲቭስ፣ ሊሚትና ኢንተግራል የምንላቸው በዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ላይ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ያው ኮርስ 12ኛ ክፍል እየተሰጠ ነው፡፡ ይዘቱ ተመሳሳይ ከሆነ ለምን አዲስ መጽሐፍ ወይም ሥርዓተ ትምህርት አስፈለገ? አንዳንዱ ራሱ ሆኖ ምዕራፍ የተቀያየረ አለ፡፡ ከ80 እስከ 90 በመቶ ከቀደመው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱን ያዘጋጁት ሰዎች የፍኖተ ካርታ ጥናቱን ማየታቸውን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ የእኔ ሥጋት ሥርዓተ ትምህርቱ ከፍኖተ ካርታው፣ ፍኖተ ካርታው ደግሞ ለግብዓት ከተሠራለት ጥናት አልተዘጋጀም የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች በፈተና ብቻ የማይመዘኑ ቢሆንም ውድቀታቸው ገና ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን ውድቀትን ማስቀረት አለብን፡፡ የፍኖተ ካርታው ጥናት የሚለውም በመጨረሻ ዓመት ፈተና በመፈተን ብቻ የተማሪዎችን ብቃት መለየት አንችልም፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ ሰባትና ስምንት ትምህርት ከመፈተን ይልቅ፣ መሠረታዊ የሆኑትንና የአፕቲትዩድ ፈተናዎች መፈተንና ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ ክህሎቶች እንዲኖራቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ምሁራንም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ›› አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የውኃ ሀብት ተመራማሪ

በምርጫ 97 ጊዜ በእጅጉ ከሚታውሱት ውስጥ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የነበረው ሚና ሲሆን፣ በጊዜው የታሪክ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስብስብ ነበር፡፡ ቅንጅትን ከመሠረቱት አራት የፖለቲካ ድርጅቶች...

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...