Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን? (ክፍል አንድ)

ከብሔር ፖለቲካ እስረኝነት ለመገላገል መዘጋጀት እንደምን? (ክፍል አንድ)

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ከዚህ ቀደም እንደተባለው፣ ለሕዝብ ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ መከታ መሆንና አደፍራሾችን እረፉልን የማለት ቁርጠኝነት በመከራ ከመመከር ብቻ አይገኝም፡፡ ሕዝብ በብሔር ፖለቲካ አመጣሽ መከራ ስለተጠበሰ ከዚያ መገላገያውም ጎዳና በግብታዊነት ወለል ይልለታል ማለት አይደለም፡፡ የነቃ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ያ ደግሞ ልሂቃዊ ዕገዛን ይጠይቃል፡፡ የነቃ (ነፃነት በየት በኩል እንደምትገኝ ያወቀ) ልሂቃዊ ሚና ሰላም ማጣትና አሳር ካስመረረው ከብዙኃን ልቦና ጋር መገናኘት አለበት፡፡ የሁለቱ ተሳልቶ መገናኘት ብቻውን በዝቅተኛው የነፃነት ዓውድ ውስጥ የመግባት መሰናዶ ይሆናል፡፡ ይህ ለምን እስካሁን ራቀን? ፖለቲከኞቻችን ለምን አላገዙም? ከዚህ በፊት የፖለቲካ ድህነትን እንደ አንድ ሰበዝ አንስተናል፡፡

የብሔርተኞች መጨረሻ ከጥፋት የመማር ብቻ ሳይሆን መመለሻ በሌለው ደረጃ በጥፋት የመዝቀጥም ጥግ እንዳለው፣ በዚህም ውስጥ አዎንታዊ ፖለቲካ ልዩነት መፍጠር እንደሚችል ከዚህ ቀደም አውስተናል፡፡ ቀደም ሲል ያነሳሳናቸው እንቆቅልሻዊ ጥያቄዎች የሚነግሩን፣ የመከራ ምክር ተራውን ሕዝብ ሊዘልቅ ቢችል፣ ለዚህ ለዚያ ሕዝብ ቆሜያለሁ ባይ ብሔርተኛን ላይዘልቀው እንደሚችል ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጥሮ በታደለ ሰፊ ሥፍራ ሠፍሮ የማንንም ፊት ሳያይና ደጅ ሳይጠና ሕይወቱን ለመቀየር የሚያደርገው የልማት ርብርብ የሸኔን ቡድን አልበገረውም፡፡ የሕዝቡን ርብርብ ከመቀላቀል ይልቅ የጨካኝ ግፍ አዳይ ወደ መሆን ነው የዞረው፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝቦች ያለፉበት መከራና ዛሬ ያሉበት ሁኔታ የሚያንገበግበው አስተዋይ ሰው፣ ስቅየታቸውን ማውሳት እንኳ ያሰቃየዋል፣ ከዕንባ ጋር ያታግለዋል፡፡ ይህንን ስሜትና የሕዝብ አበሳን በማቃለል ተግባር ላይ መጠመድን ‹‹የሕዝብ ጉስቁልና አንቀረቀበን›› በሚሉ የብሔርተኛ ፖለቲካ ጩኸቶች ውስጥ ማጣታችን የሚያስገነዝበን፣ ለሕዝብ አሳቢነታቸው በበደል/በቂም ቆጠራና በስስት ፖለቲካ ውስጥ ከመገተር እንደማይበልጥባቸው (ህሊናቸውን የሚመራው የሕዝብን መከራ የማቅለል ዒላማ እንዳልሆነ) ነው፡፡

  1. ከብሔርተኛ አዙሪት ስለመውጫችን ከመነጋገራችን በፊት፣ ከብሔር ፖለቲካ መውጣትን ትክክለኛ የሚያደርጉ ምክንያቶቻችንን በጭማቂ መልክ ቁጭ ቁጭ እናድርግ፡፡
  • የትኛውም ክፍልፋይ ብሔርተኝነት ለብሔር መብት (ለቡድን መብቶች) እታገላለሁ/እቆማለሁ ባይነቱ ሸብራካ ነው፡፡ የትኛውም ብሔርተኛነት ከሚያለቅስለት ከራሱ ብሔረሰብ ውጪ ሌላውን ብሔረሰብ በእኩልነትና በአክብሮት ዓይን ማየት አይችልም፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ያየነው የትኛውም ብሔርተኝነት አድልኦኛ ነው፡፡ ሌላውን ያገልላል/ያንጓልላል፡፡ በእኔ ሠፈር ውስጥ የበላይነት (የገዥነት መብት) የእኔ ነው/የእኔን የበላይነት ተቀብለህ እደር ይላል፡፡ ከዚህ አልፎም፣ በራሱ ብሔረሰብ ማንነት ውስጥ ሌላውን እየሰለቀጠ የራሱን ማኅበረሰባዊ ክምችትና ይዞታ ለማግዘፍ አያቅማም፡፡ ‹‹ያልጠራ/የተበረዘ›› ሆኖ የሚታየውን ወይም የተሰባጠረ ማኅበረሰብን እንዳለ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ ‹‹ያልጠራ››ን ‹‹ከማጥራት››፣ የተሰባጠረን በራሱ ማኅበረሰባዊ ባህርይ ለመቅረፅ ከመሥራት አይመለስም፡፡ ይህ ሲሆን ዓይተናል፡፡
  • የአማራ ብሔርተኝነት ብቅ ሲል ‹‹በብሔርተኛ ሥርዓት ውስጥ እስከተኖረ ድረስ ብሔረሰባዊ ጥቅምን/መብትን ለማስከበር ብሔርተኛ መሆን ያስፈልጋል›› የሚል መከራከሪያ ዕሳቤም አብሮ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ዛሬ አማራ በብሔርተኝነት ያፈራው ጥቅም ሰላም ማጣትና በውስጡ የክፍልፋይ ብሔርተኛነት መባዛት ነው፡፡ አማራ በምሳሌነት ተጠቀሰ እንጂ የትኛውም የአገራችን ብሔርተኛነት ያፈራው የኪሳራ ሀብት ነው፡፡ የትኛውም የብሔርተኛነት እንቅስቃሴ የማያስቀና ቅናትን ይፈጥራል፤ ‹‹እኔስ ለምን ይቅርብኝ›› በሚል ትርፍ የለሽ መቅበጥበጥ ውስጥ ይጥላል፤ ‹‹ማንነቴ ይታወቅልኝ/ወሰን ይበጅልኝ፣ ወዘተ›› እያሉ ወደ ትንንሽ ሠፈርነት መበጣጠስን ያነሳሳል/ይቀሰቅሳል፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት መሰስ ማለትም በራሱ የአገውና የቅማንት ብሔርተኛነት እንዲመጣ ቀስቅሷል፡፡ ትልቅ ብሔር/ብሔረሰብ ሆኖ መግዘፍ የሚሻ ብሔርተኝነት ከውስጡ ሌላ ክፍልፋይ ሲመጣበት መብትህ ነው ባይ ዕውቅና የመስጠት አንጀት የለውም፡፡ ‹‹አንተማ የእኔ ብሔር/ብሔረሰብ አካል ነህ ሌላ ማንነት የለህም›› ይላል፡፡ በዚህ ውዝግብ ውስጥ የመሬትም ጥቅም ስላለበት ውዝግቡ እስከ ደም መፋሰስ ይሄዳል፡፡ ይህንን መሳዩ ግጭትና ደም መፋሰስ በየትኛውም የኢትዮጵያ ብሔርተኛነት ውስጥ የመከሰት ዕድሉ እንደታመቀ ገሞራ ጊዜና ሰበብ የሚጠብቅ ነው፡፡
  • ብሔርተኛነት በዋና መለኪያነት ቋንቋን ይጠቀም እንጂ ክፍልፋይ እንቅስቃሴን ባሉት ቋንቋዎች ብዛት ገድቦ ማቆም አይችልም፡፡ የዘዬ ልዩነቶች የተባሉ ሒሳብ ውስጥ ገብተው፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ወደ 75 አካባቢ ናቸው ቢባልም፣ የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች በአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት ውስጥ ሆነውም ማንነታችን ሌላ ነው እስከ ማለት ሲሄዱ ዓይተናል፡፡ የአንድ ቋንቋ ዘዬዎች የምትናገሩ አንድ ማኅበረሰብ ናችሁ የተባሉም፣ ‹‹አይደለንም/የተለያየ ማኅበረሰብ ነን፣ ቋንቋችንም ይወራረስ እንጂ የየራሳችን ነው/የየፊና ማንነታችን መታወቅ አለበት!›› ብለው ነውጥ ሲያስነሱ ታይተዋል፡፡ እናም በቋንቋ መመዘኛ የብሔርተኛ ክፍልፋይነትን ማስቆም አይቻልም፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ሲመጣ የእነ ቅማንት ብሔርተኝነት መምጣቱ አይደንቅም፡፡ የአማራ ብሔርተኝነትም ሆነ የትኛውም ፖለቲካ ‹‹አንድ ቋንቋ ስለምትናገሩ ማንነታችሁ አንድ ነው›› ብሎ የመፍረድ ሥልጣን የለውም፡፡ ዛሬ ‹‹ወልቃይት አማራነት ነው፣ ራያ አማራነት ነው›› ይባል እንጂ ዋል አደር ብሎ ‹‹ራያ አማራም ሌላም አይደለም የራሱ ማንነት አለው/ወልቃይትም ወልቃይት ነው›› የሚል የማንነት አቋምም ፈክቼ ልውጣ ማለቱ የሚቀር አይደለም፡፡ ብሔርተኛነት እስከቀጠለ ድረስ እንዲህ ያለው ክፍልፋይነት አማራ ውስጥ ብቻ የመጣና እየመጣ ያለ የሚመስለው ካለ በኢትዮጵያ የ30 ዓመት ታሪክ ውስጥ በየቦታው እየተፍተለተሉ የመጡ የብሔርተኛ ክፍልፋዮችን አዝማሚያ በቅጡ አላጤነም፡፡ ችግሩ ሁሉንም ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ነኝ ባዮችን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡
  • ብሔርተኝነት በሰብዕናና በዜግነት መተሳሰብንና በእኩል ዓይን መተያየትን ይገዘግዛል፡፡ በዳይነትና ተበዳይነትን ስለሚያመነዥግ ‹‹የእኔ ወገን ያልሆነ ባይተዋር›› በሚል አግላይነት ውስጥ ስለሚያስብና ቅያሜን/ጥላቻንና ቂምን ‹‹ንቃተ ህሊና›› ብሎ ስለሚያፋፋ፣ ቁርቁስና ደም መፋሰስ ያመርታል፡፡ ከዚህ ተሻግሮም፣ አለኝ የሚላቸውን ጥያቄዎች ለማግኘት ማኅበረሰብን ማፈናቀልን፣ በጭካኔና በደቦ መቅጣትን፣ የሃይማኖት ግጭት ማስነሳትን ሁሉ እንደ ታክቲክ ሲጠቁምባቸው ታይቷል፡፡ የቀድሞ የበደል ትርክትና ቂም ይዞ የትናንትና ሒሳብን ዛሬ ያሉ ሰዎችን በመቅጣት ሲያወራርድም አስተውለናል፡፡ ጭራሽ በሆነ ሰበብ ቦግ ብሎ የሚጦዝ ቁጣ ሲፈጠር፣ የሰዎችን ሕይወትና ንብረት በቁጣ ማብረጃነት ማወራረድ ተደጋግሞ ተፈጽሟል፡፡
  • በብሔር ቡድኖች የሚንቀሳቀስ ፖለቲካ እስካለ ድረስ ቡድኖቹ ሥልጣን ባይዙም፣ ለእነዚህ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድል አብሮን ይኖራል፡፡ በብሔርተኛ ፖለቲካ ድባብ ውስጥ ከተኖረ ብሔርተኛ የሆነውም ያልሆነውም የመጨረሻውን ዝቅተኛ ነፃነት እስከማጣት ድረስ እስረኛ ይሆናል፡፡ የሃይማኖት ግጭት/የብሔር ግጭት ሲፈጠር፣ ፀቡ ‹‹ባይተዋር›› ወይም ንዑስ ከተባለ ማኅበረሰብ አባል/አባላት ጋር ከሆነ፣ የዚያ ንዑስ ማኅበረሰብ አባላት ሁሉ በፍርኃት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ ትርምስና ግጭት እስካለ/የመፈንዳት ዕድሉ እስከተንጠረበበ ድረስ ወይም ሰዎች ከሥጋት የተላቀቁበት ሁኔታ እስከሌለ ድረስ ያለ ጭንቅ ራቅ ያለ መንገድ ለመሄድ እንኳ አይቻልም፡፡ በመደበኛ ሁኔታ የሆነ አውራጃ/ክፍለ አገር ደርሶ ለመመለስ ሰው ሲያቅድ፣ ከሞላ ጎደል በሰላም ስለመመለሱ ተስፋው ሙሉ ነው፡፡ የቤተሰቡ አባላትም የሚጠብቁት በሞላ ተስፋ ነው፡፡ ብሔርተኛ ንቁሪያዎችና ኮሽታዎች ይህንን ዝቅተኛ ነፃነት ነው የሚነጥቁት፡፡ በጥርጣሬና በሥጋት መበጠር ውስጥ መግባት (የዝቅተኛ ነፃነት ዕጦት ውስጥ መውደቅ) የግለሰቦችና የማኅበረሰቦች ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ነው፡፡
  • ይህን ያህል ግለሰቦችም፣ ማኅበረሰቦችም፣ መንግሥትም ዝቅተኛ ነፃነትን ከማጣት ዕድል ጋር አብረው ይኖራሉ (እስረኞች ናቸው) ብሎ ማለት፣ በሌላ አነጋገር የብሔርተኞች እንቅስቃሴዎች እስካሉ ድረስ የመንጓለል/ሰላም የማጣትና የመታመስ አደጋ አብሮን ይኖራል ማለት ነው፡፡ በአጭሩ ማኅበረሰባዊ መብቶችም የግል መብቶችም መከበር አይችሉም ማለት ነው፡፡
  • የብሔረሰቦች ማንነት፣ ቋንቋዎቻቸው፣ ባህሎቻቸው፣ ታሪኮቻቸው በእኩልነት ዓይን የመከበር መብት የሚረጋገጠው በዴሞክራሲ ሥርዓት ነው፡፡ የሃይማኖቶች እኩል መስተንግዶ በሃይማኖተኛ መንግሥትና በሃይማኖት ፓርቲዎች እንደማይጨበጥ ሁሉ የብሔረሰቦች መብት መከበርም (የእነ ወልቃይት የእነ ራያ፣ አገው፣ ወዘተ፣ ወዘተ ሁሉ ህልውናና ማንነት መከበርም) የሚሻው ብሔርተኝነትን ሳይሆን ኅብራዊ አመለካከትንና ዴሞክራሲን ነው፡፡ ዴሞክራሲን የመገንባትና የማቋቋም ጉዳይ ከብሔርተኛነት አዙሪት ለመውጣት ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል፤ ይኮስኩስም ይድላም የሞት ሽረት ያህል ከአገር ህልውና ጋር ከተጣበቀ ከአንድ ፓርቲ ገዥነት ለመላቀቅ ቁርጠኛ ሆኖ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ የዚህ ዓይነት ነፃነትን የመሻቱና ተጨባጭ የማድረጉ ትግል፣ ሞት ሽረታዊ የአገር መሪነት ዕዳ ውስጥ የወደቀውንም ፓርቲ (ከእነ አባላቱ) የሚመለከት ነው፡፡ ያ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ይሁንታ በውድድር እያገኘ ወደ ሥልጣን የመውጣትና የመውረድ ነፃነትን በዘላቂነት የሚያገኘው ወደ ዴሞክራሲ በመጓዝ (ለኅብረተሰብ የሚፈይዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲጎለብቱ ምቹ በመሆንም) ነው፡፡ ከኅብረተሰብ ጋር ተቃቅፎ ዴሞክራሲን የመገንባት ጉዞን ያላራመደ የሞት ሽረት ፓርቲ፣ ውሎ አድሮ በጉምጉም ውስጥ ተሸሽጎ በሚያደባ አመፅም ሆነ የመንግሥት ግልበጣ የመበላት አደጋ ያገኘዋል፡፡
  1. ዴሞክራሲን የማማጣትና የመገንባት ዕዳ የመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያም ከመንግሥትም ይበልጥ ኃላፊነቱ በቡድንና በግል መብቶች ውስጥ መኖር የሚሹ ዜጎች ሁሉ ነው፡፡ እስካሁን እንደታየው ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ግንባታን ለማረጋገጥ የአገራችን እውነታ ምን ዓይነት ሚና እንደሚሻብን በአግባቡ የገባን አይመስልም፡፡ አሁን ያለው መንግሥት ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር በተቆራኘበት ሁኔታ ውስጥ፣ አገራችን ከዓለም አቀፋዊ-አካባቢያዊና ውስጣዊ ብዙ ፈተናዎች ጋር እየተንገላታች ነች፡፡ እነዚያን ፈተናዎች በብልኃት ማለፍም ሆነ እያለፉ ዴሞክራሲን የማቋቋም ተግባር የሁላችንንም ርብርብ ሲጠይቅ የቆየና እየጠየቀ ያለ ነው፡፡ ከማዶ ቆመን ‹‹ዴሞክራሲን አምጣ/ተቋማትን ገንባ/ሕግ አስከብር›› እያልን ምላሳችንን ብንዘረጋ፣ ጠብ የሚል ውጤት አይኖርም፡፡ ለሕግ አክባሪነትና ለዴሞክራሲ ግንባታ መንግሥት እንዲደፋፈር የሚጠቅሙ ኃላፊነቶችንና የሕግና ሥርዓት መከበርን የሚያግዙ/ቀውስ የሚያበርዱ ሁኔታዎችን ማልማት፣ ዴሞክራሲንና የሰላምን አስተማማኝነት የሚሹ ፖለቲከኞች ዜጎች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ በትንሽ በትልቁ (አንዱም ሳይያዝ) በሌላው አገር ያየሁት የዴሞክራሲ መብት ሁሉ አማረኝ ዓድማ ላድም/ሠልፍ ልውጣ ባይነት፣ በቁጣ ቱግ እያሉ የደቦ ቅጣት መፈጸም/መሠረተ ልማት ላይ እልህ መወጣት፣ ወዘተ በዴሞክራሲ ዕድል ላይ እባብ ይዞ ከማስፈራራት ቁጥር ነው፡፡ እዚህም እዚያም እየተኮሱና ሰላም እየነሱ ‹‹የዴሞክራሲ መብቶች አይጣሱ! ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ! የሕግ የበላይነት ይከበር!›› ብሎ ነገር፣ ወይም የውጭ ሰው ዓይነት ሥፍራ ይዞ ‹‹መንግሥት የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት አለበት…›› የሚል ምክር መስጠት አሳዛኝ ቧልት ነው፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ በየጫካው የሚተኮሰው ጠመንጃ ከሕዝብ ፍቅርና ዓላማ ጋር የተገናኘ አይደለም፤ በጥላቻና በበቀል የሚነቃነቅ፣ ንፁኃን ላይ ጥይቱንና እሳቱን የሚለቅ፣ ሥልጣን ቢይዝ ዴሞክራሲን ሊያቋቁም ይቅርና/መንግሥት ሊመራ የማይችል መሆኑን እናወቃለን፡፡ ይህንን እያወቅንም በዚህ ዓይነት ጠመንጃ ከአካባቢ አካባበር ኑሯችን ሲታመስ ቆይቷል፡፡ ይህን ያህል የከሰረ ብሔርተኝነት መከራ እያስቆጠረን ወይም በደፈናው ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ያለ ሥጋት መዘዋወር በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ጥሎን ሳለ፣ ቢያንስ ጎጂነቱን እንኳ አንድ ላይ ቆሞ ለማውገዝ አልቻልንም፡፡ መላ ኅብረተሰባችን የዚህ ዓይነት የጫካ ተኳሾችን ራቁታቸውን እንዲያስቀር አንድ ላይ ማሠለፍማ ገና ያልተነካ ተግባር ነው፡፡ እዚያም እዚያም የሚካሄደውን የውር ውር ሰላም ነሺነት ትተን፣ ከትግራይ ተነስቶ በነበረው አገርን መከላከያ ኃይል ሊያሳጣና ሊበትን ይችል በነበረ ግዙፍ ጥቃት ጊዜ፣ የረባ የአገር ወዳድነት ሠልፍ ያላሳዩ ፖለቲከኞች (ከብሔርተኞችም ውስጥ ለኢትዮጵያ ከመቆም ውጪ ሌላ ፖለቲካ የለንም ከሚሉትም ውስጥ) ነበሩ፡፡ የትግራይ መከላከያ ኃይል ነን ባዮቹ ጦረኞች ደብረ ብርሃን ደረስን እነ እንትና ካልፈረጠጡ አሳደን እንይዛቸዋለን እያሉ ሲታበዩ፣ የውጭ አጫፋሪዎቻቸውም አገር ያለ መሪ እንድትቀር የሚያደርግ የሥነ ልቦና ጦርነት ሲያጦፉ፣ ነገ ጦረኞች ከሚያንፈራፍሯት ኢትዮጵያ የሥልጣን ትሩፋት ይደርሰናል ብለው በዝምታ የሚጠባበቁ ነበሩ፡፡ ጦርነት ቆሞ በድርድር ውጤት ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ከተቋቋመ በኋላም፣ አገር ከማዳን ተጋድሎ ውጪ ከነበሩ የዳር ተመልካቾች  ውስጥ በአደባባይ መድረክ ላይ ወጥተው፣ በጦርነቱ ጊዜ የነበረውን የተማረረ አነጋገርና ሰላም ከተፈጠረ በኋላ የነበረውን ለስላሳ አነጋገር በ‹‹ሁለት ምላስ የፖለቲካ ቀባጣሪነት›› እየነቀፉ የተመፃደቁም ኃፍረት የለሾች ነበሩ፡፡ ለእነሱ የአንደበት መለሰለሱ ለሰላም/ለዕርቅና ለአንድነት ሲባል የተደረገ ክፍያ መሆኑ ከግንዛቤያቸው ውጪ ነው፣ ወይም ‹‹ብልጣ ብልጥ›› መሆናቸው ነው፡፡ ከጦርነቱ ጀርባ ግዙፍ የፖለቲካና የሻጥር/የግፍ ጥፋቶች የነበሩ መሆናቸውን ለጊዜው እንተወው፡፡ ግን ጦርነት ውስጥ የገቡ ኃይሎች በሚዋጉበት ጊዜ ‹‹ወድሽና ውዴ›› የሚል የፍቅር ቃላት  እየተለዋወጡ ይዋጉ ይመስል፣ ከጦርነት በኋላ ሰላም ሲወርድ ደግሞ በየትም የዓለም ሁኔታ  የተዘራጠጠ ቋንቋ የማይቀየር ይመስል፣ ‹‹ሁለት ምላስ ንግግር! አቋምን መቀያየር! ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ መፈናጠር!›› እያሉ ለመሳለቅ መድፈር በምን ይብራራል!? በቁማርተኝነት? በደነዝነት? ያ ሁሉ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ውድመት የደረሰበት አማራ፣ እንደገና ከውስጡ በወጡ ተኳሾች ሲታመስ ድርጊቱን ጥፋት ብሎ ለመንቀፍ የደፈረ ከተቃዋሚዎች አንድ ኢዜማ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ሁሉ እንደ ገለልተኛ ብጤ ሆኖ ‹‹ችግሩ በሰላም ይፈታ›› ከማለት ያለፈ አቋም አላሳየም፡፡ እንዲህ ያለው ራስን ከውጪ አድርጎ ለመንግሥትና ለተዋጊ የይምሰል የመፍትሔ ቃል የመወርወር ፖለቲከኝነት በምን ይብራራል? ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት፣ ‹‹ሻይ ቡና›› የተባለ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በሕወሓትነቱ ተጋብዞ የተገኘ ሰው ምን ይናገራል ብለን ስንጠብቅ፣ በሕወሓት በኩል ስለነበረው የጦረኝነት ጥፋት ትንፍሽ ሳይል ጦርነቱ በመቆሙ የተቆጩና የትግራይ ሕዝብ እንዲጠፋ የሚሹ እንደነበሩ እስከመናገር ደፈረ፡፡ የኦነጉም ተጋባዥ በ50 ዓመት ምንም ስላልተለወጠ ‹‹የቅኝ ወረራና ተገዥነት›› አቋምና መሬት ብሔር ያለው ስለመሆኑ ሲያወራ ሰማን፡፡ ሰዎች ብዙ ጉድ ወይም ክስረት ያለበትን እንዲህ ያለ አቋማቸውን ምንም ቅሌት/ትዝብት አያገኘንም ብለው በልበ ሙሉነት ለመናገር የሚደፍሩት እንደምን ነው? ይህ ድክመት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ አወላልቆ የሚፈታ አጋላጭነት ሳይነካው ማለፉ ተደጋግሞ መታየቱ በምን ይብራራል? እንዲህ ያለው እንቆቅልሻምነት ምን ተብሎስ ይፈታል?

  1. ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማዊ ሥጋትና ጥቃት በነበረበት ጊዜ የአፍ-የአፍንጫ ሽፋን፣ የፅዳትና የርቀት ጥንቃቄዎችን አለማክበርና ክትባትን ችላ ማለት በአገራችን ውስጥ ፈተና ነበር፡፡ ‹‹እኛ አይዘንም/አመጋገባችን ይጠብቀናል›› ከማለት አንስቶ ‹‹ፀሎትና ፀበል ይጠብቀናል›› ባይነት ብዙ ይገዳደር እንደነበርም እናስታውሳለን፡፡ በቅርቡ በእጅ አዙር በማውቀው ሰው ላይ የደረሰውን ላካፍላችሁ፡፡ የአንድ ሰው ልጅ ታማ አዲስ አበባ የሚኖር ዘመዷ ዘንድ ትመጣለች፡፡ ዘመድ ሐኪም ቤት ወስዶ ያስመረምራል፡፡ የምርመራው ውጤት የታይፈስና የታይፎድ ሕመም ሆኖ መድኃኒት ይሰጣትና ታማሚዋ ወዳረፈችበት ቤት ትመለሳለች፡፡ ለትንሽ ጊዜ መድኃኒቱን ከደካማ የምግብ ፍላጎት ጋር ስትወስድ ከቀየች በኋላ፣ ትውልድ ሥፍራዋ ወዳለ ፀበል የመሄድ ፍላጎት ይመጣል፡፡ ምግብ በአግባቡ እየወሰደች መድኃኒቱን ትቀጥል የሚለው ቁምነገር ከየአቅጣጫው የሚመጣውን አላዋቂ አማካሪነት ሊረታ አልቻለም፡፡ ልጅቷ መድኃኒቱንና ሕክምናን ንቃ ወደ አገር ቤት ተመለሰችና ጠበል ጀመረች፤ ከአንድ ሁለት ሳምንት ጊዜ በኋላም አረፈች፡፡ እንዲህ ያለ ብዙ ጉድ በየቤቱ አናጣም፡፡ እንዲህ ያለው የአገራችን ድንፈፍ አኗኗር ውስብስ ሰበዞች ያሉበት ነው፡፡ የደነዘ የአስተሳሰብና የኑሮ ዘይቤ ሁለመናው ነው፡፡ ትናንትም ዛሬም ነገም በተለመደው የኑሮ ሥልት ውስጥ መንገላወድን ኑሮዬ ብሎ የተቀበለ፣ ጥያቄ በማይነካቸው እስበቶች/ወሬና ምክሮች ዕለት በዕለት የሚጠቀጠቅ ኑሮ ነው፡፡ በጥቅጠቃው ውስጥ የፈጣሪን ዕገዛንና የራስ ጥረት ድርሻን አፋልሶ መረዳት አለ፡፡ የዕለት በዕለት የመንደር ጥቅጥቃቱ፣ የሚባለውን ሳያጣሩ የማስገባት ዝንባሌውና መሳነፉ በኑሮ ውስጥ የደደረ ዘልማድ ፈጥሯል፡፡ ይህ ድድር ሁሉን በሚያዳርስ የተባ ተሃድሶ ካልሆነ በቀር ሄድ መለስ በሚል ምክር የሚበገር አይመስልም፡፡ በፖለቲካችን ውስጥ እንዲሁም በ‹ልሂቅ› እና ኅብረተሰባችን መስተጋብር ውስጥ ቅጣ አምባር አልባነት፣ እክትነት፣ ንቁ አሳቢና ተሳታፊ ለመሆን መስነፍ፣ የደደረ ነገር ሳያበጁ አልቀሩም፡፡

በንባብና በጥናት ትጋት ከመበልፀግ የቦዘነ፣ ጭራሽ የተጨፈነ፣ የኢትዮጵያን እውነታ በአግባቡ ያልተረዳ ኦና ፖለቲከኛ በሬዲዮ/በቴሌቪዥን ላይ ወጥቶ ያልተጣራና የተምታታ ነገር ይዞ ለመንዘባዘብ የሚደፍረው፣ ይህንኑ ባዶነቱን እንደታቀፈ በምርጫ ተወዳድሮ የአካባቢ/የአገር ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚከጅለው፣ ሜዳው ውስጥ ከእሱ ብዙ የተሻለ ነገር እንደሌለ ስለሚያስብ ነው፡፡ ቁንፅልፅልና ያልበሰለ ነገር የያዘ ደፋር በኢንተርኔትና በቴሌቪዥን የፖለቲካም ሆነ የኑሮ ክህሎት አንቂ ነኝ የሚለው፣ ምኅዳሩ ውስጥ የሚያሳጣኝ ብስለት የለም ብሎ ነው፡፡ በሻይ ቡና ላይ ያስተዋልነው ንግግር እንደዚያው ነው፡፡ የኦነጉ ሰውዬ ‹‹ስለመሬት ብሔር›› ስለኦሮሞ ‹‹ቅኝ ተገዥነት›› ማውራት እንዲያውም፣ አጋላጭ ትንታኔ በኮሰሰበት ምኅዳር ውስጥ የተዘነጋ አቋምን በመደበኛ ቴሌቪዥን ላይ ባወራራው ‹‹ትኩስ ንቃት›› ማድረግ እችላለሁ የሚል ተስፋና ብልጠትም ያለበት መሳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ተብተው ሕዝብን የሚያተቡና የኅብረተሰብ ድጋፍን በዙሪያቸው ያሰባሰቡ አንድ ሁለት ፓርቲዎች ኖረው ቢሆን፣ ምሁራንና ሊቃውንት ታዝቦ ዝም ከማለት ያለፈ ተከታታይ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተው ቢሆን (ከጥናታዊ/ምርምራዊ ሥራዎች የፈለቁ ትንታኔዎችን በተከበሩና በሚናፈቁ መጽሔቶች፣ በፓናል ውይይቶች፣ በቃለ መጠይቆች፣ በኮንፈረንሶች፣ ወዘተ እየተረተሩ ቢያቀርቡ፣ ዋነኛ የሬዲዮና የቴሌቪዥን መድረኮችም እነዚሁኑ የማፍታታት ሥራ ቢሠሩ፣ በአጠቃላይ በምሁራንና በኅብረተሰብ መሀል የዚህ ዓይነት አበልፃጊ ተራክቦ ቢኖር ኖሮ ቀደም ብለን የጠቃቀስናቸው አጥፍተው ንፁህ ሊመስሉ የሚሞክሩ/አሮጌም ሆነ ቁንጽል ነገር ይዘው እናንቃ የሚሉ ደፋሮች ምንተፍረትን ባወቁ፣ ላሳውቅ ከማለት በፊት ልወቅ ወደ ማለት በሄዱ ነበር፡፡ ይህ በመጉደሉ (የፖለቲካ ድህነትና በዝምታ መታዘብ በመንተርከኩ) ይኼው እንደ አሎሎ የጠጠረና የባተተ ግንዛቤን በአግባቡ አወላልቆ ማሳጣት እንኳ ከብዶ፣ አሮጌው ነገር ልክ የመምሰል ስሜት ሲፈጥር አስተዋልን፡፡

የተፈጠረው ‹‹ልክ መሳይነት›› እንዳደናገረ መቆየት እንዳይችል ለማገዝ ብችል ጥቂት ነጥቦችን ላስፍር፡፡ የኦነጉ ሰው መሬት ብሔር እንዳለው መርቻ ማሳመኛ ይሁነኝ ብሎ ያቀረበው ‹ስኮትላንድ›፣ ‹አየርላንድ›፣ ‹ኢንግላንድ›… የሚባሉ ስሞችን  ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አጠራር ሁሉ መሬት ብሔር እንዳለው ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ በአጠራሩ መሠረት ‹አየርላንድ› የተባለው ምድር (መሬቱ) ‹‹ብሔሬ አይሪሽ ነው››/‹ኢንግላንድ› የሚባለውም ምድር ‹‹ብሔሬ ኢንግሊሽ ነው›› ይላል ብንል፣ በዚህ አካሄድ ‹ኒውዚላንድ› ምድሩ ብሔሩ የማን ነኝ ባይ ይሆን? የኦነጉ ሰው ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ አለው? የእነ አውስትራሊያና የእነ ካናዳ መሬት ብሔራቸው ምን እንደሆነ ሊያስረዳን ይችላል? ማኅበረሰባዊ ማንነት በገንዘብ አይሸጥም አይገዛም፣ ይህ ጥቅል ‹‹እውነት›› ነው፡፡ የኦነጉ ሰው ብሔር አለው ያለው መሬት በአውሮፓና በአሜሪካ በሌሎችም አያሌ ሥፍራዎች በገንዘብ ይሸጣል፣ በገንዘብ ይገዛል፡፡ የገዥውን ሰው የብሔር ተወላጅነት ሳይመርጥ መሬት በዚህ ዓይነት የገበያ ግንኙነት ውስጥ ሊገባ ይችላል፣ ገብቶም በሰፊው እያየን ነው፡፡ በሌላ በኩል ብሔረሰብ/ማኅበረሰብ በአንድ ሥፍራ የነበረ በተለያየ ምክንያት ሊገፋና መሬቱ በሌላ ሊያዝ ይችላል፡፡ ማኅበረሰብ በሒደት ጥንቅሩ ሊቀየር ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ለውጥ መሬቱ ከበደኝ ሳይል የሚቀበል ግዑዝ ነው፡፡ የመጣውን ሊቀበል የሚችልና በገበያ ግንኙነት ውስጥ ሊውል የሚችል መሬትን ‹‹ብሔር አለው›› እያሉ መከራከር ምን ዕርባና አለው? በታሪክ ውስጥ ከጥሬ መሬት ባሻገር፣ መሬቱ ከያዘው ሰው ጋር በቅኝ መስፋፋት ጊዜ ለአውሮፓውያን ሲሸጥም ታይቷል፡፡ ከመሬት ይልቅ የብሔር መገለጫ የሆነና ከተወሰነ አካባቢ ሕዝብ ድጋፍና ፍቅር ጋር የተጣበቀ የስፖርት ቡድን ዛሬ ባለንበት ጊዜ እንደ ንግድ ኩባንያ በባዕድ ቱጃር ተገዝቶ ሲነገድበት እያየን ነው፡፡ በካፒታሊዝም የማይሸጥና የማይከራይ ነገር የለም፡፡ ነፍስ ያለው ሰው ከእነችሎታው ሊገዛ/በኪራይ ኮንትራት ተይዞ ሊነገድበት ይችላል፡፡ የሰው ችሎታ በውሰት ትርፍ ሊታፈስበት ይችላል፡፡ ሐዘኔታና ሳቅ ይገዛል፣ ይሸጣል፡፡

የኦነጉ ሰው መሬት ብሔር እንዳለው ለማሳመን ‹ስኮትላንድ› ምንትሴ የሚሉ የሥፍራ መጠሪያ ስሞችን እንዳቀረበ ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ‹‹ቅኝ ገዥ ኤምፓየር›› እንደነበረች ለማሳመን ፈረንጅ ጸሐፊያን የሰጧትን መጠሪያና ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙ ቃላትን ነበር ያቀረበው፡፡ አፄ/ንጉሠ ነገሥት ‹‹ኤምፐረር›› ተብሎ ተተርጉሟል፤ አንድ ‹‹ማስረጃ››፡፡ የተገነባው ልል አገር ‹‹ኢምፓየር›› ተብሎ ተሰይሟል/የእኛም ሰዎች ልክ መስሏቸው ወይም ሞገስ መስሏቸው ሲጠቀሙበት ኖረዋል፣ ሌላ ‹‹ማስረጃ››፡፡ አፄዎችና መሳፍንቶች ዘምተው ግዛት ሲያሰፉ ‹‹አቀናሁ›› ይሉ ነበር፡፡ እንግዳ ዕሳቤ ይዞ ለመጣ የውጭ ቃል የትኛውም ቋንቋ በውስጡ ካሉ ቃላት መግለጫ ሲያፈላልግ እንግዳውን ቃል ትክክል የሚተረጉምለት ቃል አያገኝም፡፡ ፈረንጆች ወደ ግሪክና ላቲን መለስ እያሉ ለአሁናዊ ዕሳቤዎቻቸው መግለጫ ቃል ሲመሠርቱ የተወሰነች የትርጉም ዝምድናን እንደ መፈንጠቂያ በመጠቀም ነው፡፡ ለእንግሊዝኛው ‹ኮሎኒያሊዝም› ወካይ እንዲሆን ‹ቅኝ አገዛዝ/ቅኝ ገዥነት ‹‹ማቅናት›› ከሚል ቃል ሲመሠረትም መርሁ ያው ነው፡፡ ይህንን ያልጨበጠ ወይም መጨበጥ ያልፈለገ ግንዛቤ ለ‹ኮሎኖሊያሊዝም› የወጣውን ‹ቅኝ አገዛዝ/ገዥነት› ስያሜ  ከ‹ማቅናት› የመጣ ስለሆነ የነባሩን የ‹ማቅናት› ትርጉም ከቅኝ አገዛዝ ጋር አንድ አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ የቅኝ ገዥነት ዕሳቤ እንደነበር ማረጋገጫ አስረጅ ተደርጎ ተቆጠረ፡፡ በኢትዮጵያ ‹‹የነበሩት/ያሉት›› ቅኝ ገዥዎችም ፈረንጅ ጸሐፊያን ‹‹አቢሲኒያውያን›› ወይም ‹‹አቢሲኒያ›› እያሉ የጠሯቸው መሆናቸው ነው፡፡

ይህ ሁሉ ግን መልክ ብቻ የሆነ መከራከሪያ ነው፡፡ በቅድሚያ ራሱን እንደ ሕዝብ ‹‹አቢሲኒያውያን›› ሕዝብና መሬቱን አንድ ላይ ደግሞ ‹‹አቢሲኒያ›› ብሎ የሚጠራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ አልነበረም፡፡ ሐበሻን አጣመው ወደ አቢሲኒያና አቢሲኒያውያን የወሰዱት የፈረንጅ ጸሐፊያን ናቸው፡፡ ሁለተኛ ንጉሠ ነገሥት ‹‹ኢምፐረር›› ተብሎ ስለተተረጎመና ፈረንጆች በመዘማመት እየሰፋች የሄደችውን ኢትዮጵያን ‹‹ኢምፓየር›› ስላሏት፣ እየተበጠሰ እየተቀጠለ ለረዥም ጊዜ በልል ግንኙነት ውስጥ የቆየው የኢትዮጵያ አገር ግንባታ የቅኝ ግዛት ‹‹ኢምፓየር›› አይሆንም፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው የአገር ግንባታ ታሪክ፣ ከቅኝ ግዛት ኢምፓየር ግንባታ የሚለይባቸው ወሳኝ ባህሪያት ነበሩት፡፡

በኢትዮጵያ የአፄዎችና የዘመቻ ታሪክ ውስጥ፣ የማልዘምትበት መብቀያ አገሬ የሚሉት የጋራ ሥፍራ አፄዎቹ አልነበራቸውምና በዘመቻ ሲሳይ መበልፀግ የመብት ድርሻው የነበረ (የሚዘመትባቸውን ምድሮች ቁልቁል የሚያይ) ‹‹አቅኚ አገር›› ተብሎ ተለይቶ የሚታወቅ ሥፍራ አልነበረም፡፡ ለአፄው ማደርን ላከበረ ገዥነቱን ማክበር፣ የአመፅ ገዥንና የደገፈውን ሕዝብ ቀጥቶ ልክ ማስገባት (መስቀል፣ አካል መፎነን፣ መዝረፍ፣ ማቃጠል፣ በባርነት መንዳት፣ ወዘተ ፈረንጆቹ ‹‹አቢሲኒያ›› ባሉት ሥፍራም ሆነና የባህር ላይ በሌሎቹ ሥፍራዎች ሲሠራበት የነበረ ሥልት ነበር፡፡ የአፄነት ገዥነቱም በአንድ ሥፍራ ለበቀሉ መሳፍንት የተገደበ ወይም ለአንድ ማኅበረሰባዊ የዝርያ ሐረግ ብቻ የተመደበ አልነበረም፡፡ አፄነቱ ከትግራይም፣ ከአገውም፣ ከአማራም፣ ከኦሮሞም ሁሉ ጋር ሲወራረስ ታይቷል፡፡ ‹‹ሐበሻነት››ም ለተወሰነ አካባቢ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ ከመሣፍንትና ከነገሥታቱ ትውልድ ጋር በጋብቻ መዛመድም ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልና አካባቢ ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ በአፄዎቹ ግቢ ውስጥ የነበረው የገዥነት ልማድ ይጠይቅ የነበረው በዋናነት በባለሟልነት መመዘዝንና ኦርቶዶክስ ክርስትናን መቀበልን፣ ከዚያ ከዘለለ ደግሞ በኃይል ማየልን ነበር፡፡ በአጭሩ፣ ከተገዥዎች ተለይቶ የታወቀ የገዥ ማኅበረሰብ የሚባል፣ ወይም አቅኚዎችና ተቀኚዎች (ከአቅኚዎች ጋር መቀላቀል የማይፈቀድላቸው ማኅበረሰቦች) የሚባል ልዩነት በኢትዮጵያ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከኦሮሞ የወጡ ገዥዎች በትውልድ ሐረግ እየተተካኩ ለ75 ዓመታት ግድም ኢትዮጵያን ገዝተዋል፣ አፄዎችን እየጎለቱና የተለመደውን የፖለቲካና የዘመቻ ሥልት እየተጠቀሙ፡፡ በቅኝ ግዛት ኢምፓየር ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር የለም፡፡

ኦነጎችም ሆኑ የኦሮሞ ብሔርተኞች በአያሌው የሚከፉበት ምኒልክ ከኦሮሞ የተወለደ ነበር፡፡ ንግሥቲቱ ጣይቱም የኦሮሞ ትውልድ ነበራት፡፡ ምኒልክ የዙፋኑ ወራሽ እንዲሆን ፈቃዱን ሰጥቶት የነበረው የልጅ ልጁም ከኦሮሞ የተወለደ ነበር፡፡ ምኒልክ በጦር ኃይሉ ውስጥ ከኦሮሞ የተገኙ በርካታ ባለሟሎችና ወታደሮች እንደነበሩትም ዕውቅ ነው፡፡ ምኒልክ ይገለገልበት የነበረውን ግዛት የማስፋት ሥልት ኦሮሞ ላይ ሲደርስ አልቀየረውም፡፡ በውዴታ ተገዛልኝ አለዚያ ዘምቼ እቀጣህና ትገዛልኛለህ የሚል ሥልቱ በሁሉም ላይ ያለ አድልኦ የሠራ ነበር፡፡ ይህ ከኦሮሞ ትውልድ የተገኘ ንጉሥ፣ ያደረገውን የግዛት ማስፋፋት ከአገር ማስፋፋት ፋንታ የቅኝ ግዛት ማስፋፋት አድርጎ መተርጎም፣ ከኦሮሞ የበቀለ ሰው ኦሮሞን በቅኝ ግዛትነት ያዘ የሚል ቅጣ አንባር የለሽ ታሪክ ከመፍጠር አይለይም፡፡ ‹‹ኦሮሞ አልነበረም፣ ኦሮሞነቱን የካደ ነው/ከኦሮሞ ይወለድ እንጂ አማራ ነው…›› የሚል መከራከሪ የዛሬዎቹ ብሔርተኞች እንደሚያቀርቡም አውቃለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ማንነትን መካድ ብሎ ነገርና የብሔረሰብ ማንነት የሚሉት ፖለቲካዊ ንቃት አልነበረም፡፡ ከአንድ ሃይማኖት ወደ ሌላ መዞር በነገሥታትና በመሣፍንቱ ዘንድ እንደነበር ሁሉ በተራው ሰው ዘንድም ነበር፡፡ በጋብቻ ላይ ሃይማኖትን ማስማማት ከክህደት አይቆጠርም ነበር፡፡ ከአንድ መስፍን/ንጉሥ ወደ ሌላ ገልበጥ ብሎ መግባትም እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ በእነ ምኒልክም ዘንድ፣ በእነ ጎበና ዘንድም የብሔር ንቃት ብሎ ነገር አልነበረም፡፡ በኃይል ላሸነፈ ጌታ ማደርና መገዛት የጊዜው ዘይቤ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ኦርቶዶክስ ክርስትና ርዕዮተ ዓለማዊ ኃይላቸው ለነበረ ገዥዎች ክርስትናን ተቀብሎ ባለሟል የመሆን ዕድል ከየትም ለተወለደ ሰው ክፍት ነበር፡፡ ‹‹አማራ›› መባልም ኦርቶዶክስ ክርስትናን የተቀበለ ሰውን ሁሉ የሚሸፍን እንጂ ‹‹የአማራ ብሔረሰብ አካል መሆን›› ማለት አልነበረም፡፡ የዚያ ዓይነት ግንዛቤ ያኔ አልነበረም፡፡

ከጦርነት ዘመቻ ባሻገር በብዙ ውስብስብ ማኅበራዊ መስተጋብሮች እየተሳሰሩ እዚህ ዘመን ላይ የደረሱ ሕዝቦች ከሞላ ጎደል ኢትዮጵያ አገራቸው በብረትና በእሳት፣ እንዲሁም በማኅበረሰባዊ ፍልስትና መዘናነቅ መገንባቷ እንጂ ቅኝ ግዛታዊ ኢምፓየር ነች የሚል የምርኮ ግንዛቤ አይታያቸውም፡፡ ቅኝ ተይዘናል አይሉም፡፡ ‹‹አቢሲኒያውያን/ሴሞች ኦሮሞን ቅኝ ገዙ/ኦሮሞን ብቻ ሳይሆን ደቡባዊ ሕዝቦችን በቅኝነት ይዘዋል›› የሚል ትርክት ላይ 50 ዓመት ያህል ድርቅ ያለው ኦነግ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሕዝቦቻችን ብለዋል አላልኩም፣ ኦሮሞዎች ብለዋል አላልኩም፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች ብለዋል አላኩም፣ ያልኩት ኦነግ ብቻ ነው፡፡ ይህንን አሮጌ አቋም እየተው ከኦነግ የወጡም አያሌ ናቸው፡፡

ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ ከተጋቡ ኦሮሞዎች የተወለደውና ከአፄ ቴዎድሮስ አምልጦ ለመጣው ትንሹ ምኒልክ አለሁልህ ያለው ጎበና ዳጬ የምኒልክ ጦር መሪ ሆኖ የምኒልክን ግዛት ሲያስፋፋ፣ ራሱን የ‹አቢሲኒያውያን› ሎሌ አድርጎ የሚያይበት ግንዛቤ በውስጡ አልነበረም፡፡ ያልነበረውም የዚያ ዓይነት አንጓላይ ግንኙነት ስላልነበረ ነበር፡፡ የግዛት ማስፋቱም የ‹አቢሲኒያኖች›ን ቅኝ ግዛት የማስፋፋት ሆኖ አልታሰበውም፣ የአገር ግዛት (ቴሪቶሪ) ማስፋፋት እንጂ፡፡ ለምኒልክም ለጎበና ዳጬም በኦሮሞዎች አካባቢ በቅጣትና በሰላም ወዶ ገባነት የተካሄደው የግዛት መስፋፋት በሌሎች አካባቢ በቅጣትና በሰላም ከተከናወነው መስፋፋት ጋር የባህሪይ ልዩነት አልነበረውም፡፡ ምኒልክም ጎበናም የራሳቸውን ዘር ቅኝ የማስገባት ኃጢያት አልተሰማቸውም፡፡ ምኒልክ ከኦሮሞ ለተወለደው የልጅ ልጁ ዙፋን ሲያወርስም ከቅኝ ተገዥ ለተወለደ ልጅ የማውረስ ጥፋት ህሊናውን አልጎረበጠውም፡፡ በሌሎች ዙፋኑን ፈላጊዎችም ዘንድ የነበረው ሽኩቻም፣ እንደምን ከቅኝ ተገዥ ለተወለደ ልጅ ዙፋን ይተላለፋል ከሚል አስተሳሰብ ጋር የተገናኘ አልነበረም፡፡ ይህንን ሁሉ ለማሳመን ማስረጃ አያስፈልገኝም፣ ዘመኑ የነበረው የመስተጋብር ባህርይ በራሱ ጠንካራ ምስክሬ ነው፡፡

በግዛት ማስፋፋት ጊዜ በምርኮ የተያዘው ባልቻ ሳፎ ምኒልክ ግቢ ገብቶና በራስ መኮንን የክርስትና አባትነት ክርስትና ተነስቶ በባለሟልነት እየተኮተኮተ ሲያድግና ጎበዝ ተዋጊ ሆኖ ሲወጣ፣ በዓድዋ ጦርነት ጊዜም በጀግንነት ሲያበራ፣ በኋላም በስተርጅና ኃይል አሰባስቦና ከሌሎች አርበኞች ጋር ተጋግዞ አዲስ አበባ የገባውን የጣሊያን ፋሽስትን ሲዋጋ አገሬን ብሎ እንጂ የአቢሲያኒያ ቅኝ ገዥዎች ታማኝ አገልጋይ በመሆን ስሜት አልነበረም፡፡ ነጥቤን በሌላ መልክ ላምጣው፡፡ ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት በስተደቡብ ተካሂደው ከነበሩት የምኒልክ የግዛት መስፋፋት ክንዋኔዎች ጋር የነበራቸው የጊዜ ርቀት፣ የዓይንና የአፍንጫ ርቀት ያህል ነበር፡፡ ሆኖም በዓድዋ ዘመቻ ከሁሉም አካባቢዎች የምኒልክን ጥሪ ተቀብለው ተዋጊዎች ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በዓድዋ ጦርነትም ላይ በወኔ ተዋድቀዋል፡፡ በዚህ ትርዕይት ውስጥ ኦሮሞዎች የጀግንነት ዝናቸው ጣሊያኖችን ሲያርድ ታየ እንጂ፣ ‹‹የአቢሲኒያውያን ቅኝ ተገዥ ሆኜ ለማን ብዬ ደሜ ይፈሳል›› በሚል መክዳት የምኒልክ ጦር ሲደክምና ሲፈታ አልታየም፡፡ የኦነጉ ሰው ይህንን በምን ያብራራዋል? በ‹ንቃት ጉድለት›? የትኛውም ሕዝብ በቅኝ ተገዥነት ሥር ሲወድቅ ይህንን ለመረዳት አንቂ ፈልጎ አያውቅም፡፡ በቅኝ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ቅኝ በወደቁ ሕዝቦች ዘንድ ቅኝ ተይዘናል ወይስ አልተያዝንም የሚል ክርክርና መደናገር ተነስቶ አያውቅም፡፡ ይህ የግንዛቤ ልዩነት የመጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ፣ ያውም በአንድ ኦነግ ነው፡፡ ይህ በራሱ ቅኝ ተገዛን ባይነቱ ልቦለድ መሆኑን ያሳብቃል፡፡ ወይስ ‹‹ሻይ ቡና›› ላይ ላየነው ሰው የተከሰተለት ታሪክ ለእኔ ዓይነቱና ለቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ኦነግን ለማይከተሉ አያሌ ኦሮሞዎች ጭምር) አልከሰት ብሎን ይሆን? የኦነጉ ሰው ይህችን እንቆቅልሽ የሚፈታ ትንታኔ ያምጣና እስኪ ያንቃን!! ይህችን የመጨረሻዋን መከራከሪያ ማክሸፍ ከቻለ፣ ሌሎቹንም መከራከሪያዎች እንደ ረታ እቆጥርለታለሁ፡፡ የሚያመጣው መከራከሪያ ሕዝቦች ስላልነቁ/ እንደ ኦነግ ታሪክ የገባቸው ልሂቃን ስላላገኙ የሚል መሳይ መከራከሪያ የሚያፍተለትል ከሆነም አቀርቅሬ መንገዴን እቀጥላለሁ፡፡

እኔ ይህን ያህል ከተንፈራፈርኩ ለመላ ኅብረተሰባችን የተሟላ የታሪክ ግንዛቤ ከመስጠት አኳያ የታሪክና የፖለቲካ ሊቃውንቶቻችን የተፍታቱ ጽሑፎች እንዲያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ የመከራ ልምድ የሚሰጠንን ምክር አጥብቀን አስተሳሰብና አካሄዳችንን ለማቃናት የምንበቃውም፣ ከዚህ ቀደም እንደ ተጠቆመው የተንሰራፋብንን የፖለቲካ ድህነት የሚያካክሱ መፍትሔዎች ካበጀን ነው፡፡ ከእነዚህ መፍትሔዎችም አንዱ በምሁራንና በኅብረተሰባችን መሀል አዕምሮ አብሪ ተራክቦ በተከታታይ መኖር መቻሉ ነው፡፡

(ክፍል ሁለት ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...