- የትግራይና የአፋር ክልሎች ተወካዮች ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት ማሟያ ምርጫ ይሳተፋሉ
ከሁለት ዓመታት በፊት በሕዝባዊ ውሳኔ የተመሠረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው የእግር ኳስ ጠቅላላ ጉባዔን እንደሚቀላቀል ተገለጸ፡፡
አዲስ የተመሠረተው ክልል ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ አዳራሽ በሚከናወነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመቀላቀል ጥያቄ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
ክልሉ ጠቅላላ ጉባዔውን ከተቀላቀለ በኋላ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአባልነት ማሟያ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ ዕጩዎችን ማቅረቡ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት የማሟያ ምርጫ ውድድር መሥፈርት ያሟሉ ሦስት ዕጩዎችን ክልሉ ማቅረቡ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማዕረጉ ሀብተ ማርያም፣ ሔለን ደበበና እስራኤል አታሮ የሚባሉ ዕጩዎችን አቅርቧል፡፡
ከዚህም ባሻገር በዘንድሮ ጠቅላላ ጉባዔ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የቀረው የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ አወል አብዱራሂም፣ ሕይወት አረፈዓይኔ፣ እንዲሁም አስፋው ፀጋዬን በዕጩነት አቅርቧል፡፡
በሌላ በኩል ዘንድሮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የማሟያ ምርጫ ውድድር፣ የአፋር ክልል የእግር ኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል ኢብራሂም ሙክታርና አሊያ አብዱልቃድር በዕጩነት ቀርበዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሦስት ዓመታት የምርጫ ዘመን ያገለገሉትን አቶ ዓሊሚራህ መሐመድ መሥፈርቱን ያላሟሉ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚከናወነው ጠቅላላ ጉባዔ አዲሱን ክልል ጨምሮ ሦስት ተወካዮች የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፊፋ ጋር በጋራ በመሆን ሲወጣ የነበረውን የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ለጠቅላላ ጉባዔ እንዲያቀርብ ተጠቁሟል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሚያቀርቡት የማሻሻያ ደንብ ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
ዓምና ከፍተኛ ውዝግብ ያስተናገደው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ፣ አቶ ኢሳያስ ጂራን ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡
በምርጫው የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ሚኒስትር አቶ መላኩ ፈንታ አማራ ክልልን ወክለው፣ እንዲሁም ቶኪቻው አለማየሁ (ዶ/ር) ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ይታወሳል፡፡
በአንፃሩ ምርጫውን ለሁለተኛ ጊዜ ያሸነፉት አቶ ኢሳያስ ሥልጣኑን ዳግም ቢረከቡ፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን ለውጥ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያሳኩትን ተግባራት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡