Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉበዔውን መቀሌ እንደሚያደርግ ተጠቆመ

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉበዔውን መቀሌ እንደሚያደርግ ተጠቆመ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ2016 ዓ.ም. መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ እንደሚያከናውን ተጠቆመ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጉባዔውን ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ለማከናወን ማቀዱ ተሰምቷል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ በዕለቱ 19ኛው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪሌ ውድድር ካላንደርን ይፋ ያደረገው ብሔራዊ ፌዴሬሽን፣ ኅዳር ላይ ለስምንት ቀናት ውድድሩን እንደሚያደርግ አሳውቆ የነበረ ሲሆን፣ ከውድድሩ ጎን ለጎነ ጠቅላላ ጉባዔውንም በክልሉ ለማድረግ ከውሳኔ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡

በዚህም መሠረት በውድድሩ ላይ ለሚካፈሉ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች፣ ተቋማት፣ እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች እስከ ኅዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲመዘገቡ ጥሪ ተደርጓል፡፡

የትግራይ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለሁለት ዓመታት ከማንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ተገድቦ የቆየ ሲሆን፣ በክልሉ የሚገኙ ክለቦች፣ እንዲሁም የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ማቆማቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የክልሉን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጉባዔውን፣ እንዲሁም የማራቶን ሪሌ ውድድርን በክልሉ እንዲከናወን ጥያቄ ማቅረቡ ታወቋል፡፡   

ጠቅላላ ጉባዔውንና ውድድሩን በመቀሌ እንዲያስተናገድ ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥያቄ ያቀረበው የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ምላሽ ማግኘቱን የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪዳነ ተክለሃይማኖት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ አስተያየት ከሆነ ክልሉ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውንና የማራቶን ውድድሩን ማስተናገድ መቻሉ ለክልሉ ስፖርት መነቃቃት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

ክልሉ በጦርነቱ፣ እንዲሁም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአጠቃላይ እንቅስቃሴ ማቆሙን አቶ ኪዳነ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎችና ስድስት የአትሌቲክስ ክለቦች የነቃ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱን ተከትሎ ከፍተኛ ውድመት በመድረሱ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ውስን ባለሙያዎችና ስፖርተኞች መኖራቸው ተነስቷል፡፡

ይህም ሆኖ ጦርነቱ ከቆመ በኋላ በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች፣ እንዲሁም ክልሎች ሲከናወኑ የነበሩትን የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ከሐምሌ ወር ጀምሮ እንደገና ማንቀሳቀስ እንደተጀመረ አቶ ኪዳነ ለሪፖርተር አክለዋል፡፡

ሆኖም ኅዳር 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቀሌ የሚሰናዳውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በጥሩ መልኩ የማስተናገድ አቅም ቢኖርም፣ በማራቶን ውድድሩ ላይ መካፈል አቅም ያላቸው አትሌቶች ማግኘት ግን አዳጋች መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ጠቅላላ ጉባዔውን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ በአንፃሩ በማራቶን ውድደሩ ላይ መካፈል አቅም ያላቸውን አትሌቶች ለማብቃት ግን በቀሪ ቀናት ውስጥ የበለጠ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፤›› በማለት አቶ ኪዳነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ ከመስከረም ወር ጀምሮ በክልል የሚገኙ ወረዳዎች፣ እንዲሁም ክለቦች እንደገና እንዲደራጁ ስፖርተኞችን፣ እንዲሁም ባለሙያዎችን ማሰባሰብ እንደተጀመረ ተጠቅሷል፡፡

በትግራይ ክልል የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች መሳተፍ የቻሉ አትሌቶችንና ክለቦችን ማፍራት ማለትም መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪነግ፣ ጉና፣ መሶቦ ሲሚንቶ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ሱር ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም የፖሊስ ክለብ ይጠቀሳሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ማስታወቂያ አውጥቶ ባለሙያዎችንና አትሌቶችን እየቀጠረ እንደሚገኘ አቶ ኪዳነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ክልሉ ስፖርቱን እንደገና ለማንቀሳቀስ የሀብት ችግር እየፈተነው እንደሚገኝ የሚያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

‹‹የክልሉን ስፖርት እንደገና ለማንቀሳቀስ የትግራይ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ በአንፃሩ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የባለሀብቶች ድጋፍ ለማሰባሰብ ያደረገው እንቅስቃሴ ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ሆኖም አሁንም ጥረቱን ይቀጥላል፤›› ሲሉ አቶ ኪዳነ ስለሁኔታው ያስረዳሉ፡፡

የክልሉን ስፖርት እንደገና ለማንቀሳቀስ አገር አቀፍ የቴሌቶን መርሐ ግብር እየተከናወነ ሲሆን፣ የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ወደ ቀድሞ አቋሙ እንዲመለስ ከፍተኛ የድጋፍና ርብርብ እንደሚያስፈልግው፣ ሁሉም የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...