Monday, December 11, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር ሰላምና ደኅንነት ሲባል ችግር አባባሽ ድርጊቶች ይወገዱ!

የኢትዮጵያ ውሎና አዳር አስተማማኝ ባልሆነበት በዚህ አስጨናቂ ጊዜ፣ ከምንም ነገር በላይ ግጭቶችን ማስቆም ቅድሚያ የሚሰጠው የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊከበሩ የሚችሉት፣ ለግጭቶች መነሳትም ሆነ መባባስ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ የጋራ ጥረት ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ ኢኮኖሚውን ካለበት የችግር መንጋጋ ለማላቀቅ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ አሁን ካለበት አስፈሪ አዘቅት ውስጥ ለማውጣት፣ ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚገባ የሚከበሩበት ሥርዓት ለማነፅና ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለመገንባት ከምንም ነገር በፊት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰላም በሁሉም ኢትዮጵያውያን ይሁንታ ማግኘት የሚችለው ግን ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምኅዳር ሲኖር ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች አለመኖር ምክንያት ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቧ ከመጠን በላይ ተሰቃይተዋል፡፡ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር በሚፈጠሩ አዳዲስ ቅራኔዎች ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው፡፡

አገርን እያስተዳደረ ያለው የብልፅግና ፓርቲም ሆነ የሚመራው መንግሥት በበርካታ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወስን፣ ግራና ቀኙን በመመልከት ካልሆነ በስተቀር ችግሮች ከመቃለል ይልቅ ይደራረባሉ፡፡ ለምሳሌ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በዲፕሎማሲና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶችና በመሳሰሉት በተግዳሮት የተሞሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ የገዥው ፓርቲም ሆነ የመንግሥት ውሳኔዎች በተለያዩ መስኮች ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች ካልታገዙ፣ ከልማት ይልቅ ለግጭትና ለውድመት የሚያነሳሱ ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ እነዚህም በተለያዩ ጊዜያት ከመጠን በላይ በማጋጠማቸው ኢትዮጵያ የግጭትና የውድመት የስበት ማዕከል እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱና ብሔራዊ መግባባት ያልተፈጠረባቸው የአንድ ወገን ውሳኔዎች፣ ከጥቅማቸው ይልቅ ጥፋታቸው ተባብሶ አገርን የግጭቶች አምባ በማድረግ ብዙዎችን ለጉዳት ዳርገዋል፡፡ በተዛቡ ውሳኔዎች ሳቢያ በተፈጠሩ ችግሮች የሕዝቡ ኑሮ ከዕለት ወደ ዕለት እየቆረቆዘ ነው፡፡ ለበርካታ ሚሊዮኖች በቀን አንዴ ምግብ ማግኘት እያዳገተ ነው፡፡ ድህነቱ ሥር እየሰደደደ መካከለኛ ገቢ የነበራቸው ሳይቀሩ ችጋር እየገረፋቸው ነው፡፡

ለዓመታት ትውልዱን ሲገድል የኖረው የትምህርት ሥርዓት ላይ ሁነኛ ለውጥ ሳይታይ ፈተና ላይ ብቻ መተኮሩ፣ በትምህርት ባለሙያዎችም ሆነ በባለድርሻ አካላት ጥያቄ እየተነሳበት ስለሆነ ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ በሁለት ተከታታይ ዓመታት በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተመዘገበው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ውጤት የሚያሳየው፣ ለ30 ዓመታት ያህል በሥራ ላይ የቆየው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን ድክመት ነው እየተባለ ነው፡፡ በፈተናው የተገኘው ዝቅተኛ ውጤት የትምህርት ፖሊሲው ነፀብራቅ እንጂ፣ ፈተናው በራሱ የትምህርት ጥራት ለማስገኘት የሚረዳ መሣሪያ ወይም ዘዴ አይደለም የሚሉ ድምፆችም እየተሰሙ ነው፡፡ በዚህ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የመጻሕፍት እጥረት ባለበት፣ በበርካታ ሥፍራዎች ከባድ ጦርነቶችና ግጭቶች ተካሂደው፣ ተማሪዎች ለትምህርትና ለጥናት በቂ ጊዜ ሳያገኙና ሌሎች በርካታ ችግሮች እየተስተዋሉ ጫናውን እነሱ ላይ መከመር ተገቢ አይደለም የሚሉ ማሳሰቢያዎችም እየቀረቡ ነው፡፡ መሠረታዊውን ችግር ወደ ጎን ገፍቶ ተማሪዎችን በፈተና ማስጨነቅ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡

የፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ ያሉ ተዋንያን አሁንም የብሶት ፖለቲካ ነው እያራመዱ ያሉት፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር ያላቸው ግንኙነት ከወትሮው እምብዛም ካለመሻሻሉም በላይ፣ ለሕጋዊና ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የማይመች ምኅዳር ውስጥ እየዳከሩ መሆናቸውን ነው በስፋት የሚያስተጋቡት፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሥርተው አብረው ለመሥራት ቢሞክሩም፣ ከምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡት መግለጫዎች መግባባትን አያሳዩም፡፡ በዚህም ምክንያት የፖለቲካው መንደር ከበፊቱ ምንም ዓይነት መሻሻል ሳያሳይ የተለመደውን ቅራኔ ነው የሚያስቃኘው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀጥታም ሆነ በገደምዳሜ ገዥውን ፓርቲ በተለያዩ ጉዳዮች ሲወቅሱና ሲከሱ ነው የሚደመጠው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥት ሀብትና ንብረት በመጠቀም ለምርጫ ውድድር ራሱን ማዘጋጀቱን፣ የፓርቲ አባላቱን ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች በተለየ ሁኔታ ለይቶ በመንግሥት በጀት ማሠልጠኑ ከፍተኛ የሕግ ጥሰት በመሆኑ በኦዲት አጣርቶ እንዲያረጋግጥ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሌሎች በርከት ያሉ ተያያዥ ጥያቄዎች እየቀረቡ ችላ ማለት ከቀውስ በስተቀር የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ የሚያስችል ሐሳብ ተለኩሶ የተለያዩ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ተነስቶ የመነጋገር አስፈላጊነት ሲታሰብ፣ ለይስሙላ ያህል ከሚቀርቡ አልፎ ሂያጅ አስተያየቶች ይልቅ በዕውቀትና በልምድ ባለቤቶች የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ እንጂ ይህንና መሰል የዲፕሎማሲና የጂኦ ፖለቲክስ ጉዳዮች ሲነሱ፣ በመስኩ የዳበረ ልምድና ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያዎች የሚመሩ ቲንክ ታንኮች ነበሩ ውይይቶችን በሰፊው መምራት ያለባቸው፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ቲንክ ታንኮች ጥርት ያሉ አጀንዳዎችን እያዘጋጁ፣ በቂ ምክክሮችና ክርክሮች እንዲካሄዱ በማድረግ የማያዳግሙ ምክረ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ ከቲንክ ታንኮች በተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና የተለያዩ ኢንስቲትዩቶች ምሁራንና ልሂቃንን በመጋበዝ ጠቃሚ ሰነዶችን ያበረክታሉ፡፡ መንግሥትም ሆነ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በመስኩ አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያንና ከተቻለም የውጭ ሰዎችን በመጋበዝ፣ በጥናት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ላይ ለመድረስ ይትጋ፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ግንኙነት የሚኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

የችግሮች ብዛት ቢዘረዘር ማለቂያ የለውም፡፡ የሌብነቱና የዝርፊያው መጧጧፍ፣ ብሔርተኝነት ላይ ተሰንቅሮ አገራዊ ራዕይ ማጣት መበራከት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት መበራከት፣ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የብልሹ አሠራሮች ቅጥ ማጣት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የባለሀብቶች በጥቅም የተሳሰረ አደገኛ ጉድኝት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ የዜጎችን ዕንባ መፍሰስ አለማቆም፣ የሕገወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መንሰራፋት፣ ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም ተንቀሳቅሶ ጉዳይን ማከናወን አለመቻል፣ በጠራራ ፀሐይ ዜጎችን እያገቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቁ ወረበሎች ከልካይ ማጣትና በርካታ ችግሮች የመንግሥት ያለህ የሚያሰኙ የዘመናችን አደገኛ ክስተቶች ናቸው፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ደግሞ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከላይ እስከ ታች መዋቅር ድረስ ያሉ የገዥው ፓርቲም ሆነ የመንግሥት አመራሮች ኃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት ጉዳይ መመርመር አለበት፡፡ እነሱ ኃላፊነታቸውን በሕግ እንደተደነገገው በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ማከናወን ካልቻሉ የሕግ የበላይነት ዋስትና አይኖረውም፡፡ ለዚህም ነው ለአገር ሰላምና ደኅንነት ሲባል ችግር አባባሽ ድርጊቶች ይወገዱ የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...

የስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከተካተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ ይሰጥ!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብዓዊ...

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...