Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሳምንት ከአሥር ሺሕ ያላነሱ የቀንድ ከብቶች በሕገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው እንደሚወጡ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በሁሉም የድንበር መውጫ በሮች በሳምንት ከአሥር ሺሕ በላይ የቀንድ ከብቶች በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጡ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

የባለሥልጣኑ የእንስሳት ኳራንታይን ሬጉላቶሪ ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ኃይሉ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አንዳንድ ነጋዴዎች የተሻለ ገቢ ለማግኘት ሲሉ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚያስመጧቸው የቀንድ ከብቶች ብዛት እንደወቅቱ ቢለያይም ነገር ግን ቁጥሩ እየጨመረ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፌዴራል ፖሊስና ከጉሙሩክ ኮሚሽን ጋር በመሆን በሕገወጥ መንገድ የአገር ሀብት እንዳይወጣ ቁጥጥር ቢደረግም፣ አሁንም ችግሩ መኖሩን ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

በድንበር ላይ በሚደረገው ከፍተኛ ቁጥጥር ከሦስት ወራት ወዲህ በሕገወጥ መንገድ የሚወጡ የቀንድ ከብቶች ቁጥር መቀነሱን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሳምንት ከአሥር ሺሕ ያላነሱ የቀንድ ከብቶች በተለያዩ የአገሪቱ መውጫ ድንበሮች በሕገወጥ መንገድ እንደሚወጡ ገልጸው፣ ለምሳሌ አንድ በግ በሕጋዊ መንገድ በ60 ዶላር ቢሸጥ፣ የ10‚000 በጎች ዋጋ በ60 ዶላር ሲሰላ አገር የምታጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የቀንድ ከብቶች ሕገወጥ ንግድን ብዙዎቹ ነጋዴዎች የሚመርጡት የእንስሳት ማቆያ ክፍያንና የሚወስደውን ጊዜ ሰበብ እንደሚያደርጉ ሲነገር ቢደመጥም፣ ነገር ግን የአገር ውስጥ የገበያ ዋጋ ዝቅ ማለቱ የችግሩ ተጠቃሽ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥት የእንስሳት ማቆያ ወይም ኳራንታይን እንደሌለ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ በግል ማቆያዎች በጊዜያዊነት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በመንግሥት እየተሠሩ ያሉ የእንስሳት (የቁም እንስሳት) ማቆያዎች በተለያዩ የአገሪቱ መውጫ በሮች ቢኖሩም፣ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ አክለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውንና በቅርቡ ችግሩን ለመቅረፍ የግንባታ ሒደታቸው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በመንግሥት የተሠሩ የእንስሳት ማቆያዎች አገልግሎት የሚሰጡት ለ20‚000 ያህል እንስሳት እስከ 2‚000 ብር በማስከፈል እንዲያቆዩ ሲደረግ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአፋር የሚገኘውን የሚሌ ኳራንታይንን በምሳሌነት ሲያስረዱ፣ መንግሥት ያስተዳድረው እንጂ አገልግቱን የሚሰጠው የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሀብት በመሆኑ፣ ለበግና ፍየል ስድስት ዶላር፣ ለበሬ አሥራ አንድ ዶላር፣ ለግመል ደግሞ አሥራ አምስት ዶላር (በአንድ እንስሳት) ላኪዎች እንደሚከፍሉ አስረድተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የሚወጡ የቁም እንስሳት በቀጥታ ለውጭ ገበያ እንደማይቀርቡ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ብቻ በቀጥታ የቁም እንስሳት የምትገዛ ብቸኛዋ አገር መሆኗን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ኦማን፣ የመንና ሌሎች አገሮች በቀጥታ የቀንድ ከብት እንደማይገዙ ገልጸው፣ እንስሳቱ ጂቡቲ ጊዜያዊ ማቆያ ደርሰው በሌላ አገር ስያሜ እንደሚሸጡ አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑ ከአሥር ቀናት በኋላ የመካከለኛው ምሥራቅ አገር የሆነች ከኦማን ጋር በቀጥታ የቁም እንስሳት ለመግዛት ስምምነት ለማድረግ ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን፣ በሌላ አገር ስምም ቢሆን 60 በመቶ እንስሳት ስትቀበል ወይም ስትገዛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ለላኪዎች በቀጥታ ለአገሮች መሸጥ አዋጭ መሆኑን፣ ቀጥተኛ ሳይሆን ሲቀር ሚሌ ኳራታይን ለአንድ በግ ስድስት ዶላር ከከፈሉ በኋላ በድጋሚ ጂቡቲ ላይም 16 ዶላር እንደሚከፍሉ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ቀጥታ ከሄደላቸው የነጋዴዎች ወጪ የሚሆነው ስድስት ዶላር ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ከሚያወጡት ወጪ አኳያ አዋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች