ሴቶች በጦርነት ቀዳሚ ተጎጂዎች ቢሆኑም በሰላም የስምምነት ሒደቶች ወቅት ዕድል እንደማያገኙና ቅድሚያ እንደማይሰጣቸው የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር ቅንጅት አስታወቀ፡፡
የማኅበራት ቅንጅቱ ይህንን ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ሴቶች የሚገኙበት የሴቶችን ድምፅ ለማጉላት ያለመ ‹‹ቡና ለሰላም›› የማኅበረሰብ ውይይት ማጠቃለያ ውይይት ላይ ነው፡፡

መድኅን
ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በተከሰቱ ግጭቶችና ጦርነቶች ሴቶች ቀዳሚ ተጎጂ መሆናቸውን፣ ይሁንና በሚደረጉ የሰላም የስምምነት ሒደቶች ላይ በበቂ ሁኔታ እየተወከሉና ድምፃቸውን እየተሰማ አለመሆኑን የቅንጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሳባ ገብረ መድኅን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተደራጀው የኢትዮጵያ ‹‹ሴቶች ለሰላም ግንባታ›› አባላት በየወረዳው የተተገበሩ ‹‹ቡና ለሰላም›› የተሰኘ ፕሮጀክት ተቀርፆ ሲተገበር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ይህ ፕሮጅከት በዋናነት በስምንት ክልሎች፣ 16 ወረዳዎች የማኅበረሰብ ውይይት የተደረገ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሳባ፣ ሴቶች ስለሰላም ማውራት እንዲጀምሩ፣ ባሉበት አካባቢ የተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ባደረሱት ጉዳቶችና መፍትሔዎች ላይ በሰፊው እንዲወያዩ ዕድል መስጠቱን አስረድተዋል፡፡
በዋናነት በግጭትና በጦርነት ወቅት አንደኛ ተጎጂ ሴቶች በመሆናቸው መፍትሔ ላይም መጨረሻ መሆን እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት አካላት ሴቶች በየደረጃው በሰላም ውይይቶች እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ምቹ እንዲያደርጉና ዕድል እንዲሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ቡና ለሰላም›› ፕሮጀክት በተለያዩ ወረዳዎች የተሞከረ መሆኑን፣ ሴቶቹ አሁንም ጥያቄ የሚያቀርቡት የግጭትና የሰላም ዕጦት ሥጋት እንዳለባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቡና ለሰላም የሰላም ውይይቶች በተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ እናቶች መንግሥት በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን በሰላም እንዲፈታና በችግሩ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶች ትኩረት እንዲጣቸው ጠይቀዋል፡፡