Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ የውጭ ምንዛሪ ብድር ለማግኘት ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር እየተደራደርኩ ነው አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ባንክ በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ መቻሉንና ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት በውጭ ምንዛሪ ተጨማሪ ብድር ለማግኘት፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር እየተደራደረ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማሻገር ተችሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት ማሳየቱን፣ በሒሳብ ዓመቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ዕድገቱ ከቀዳሚው ዓመት 43 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባንኩን የተከታታይ ዓመት የውጭ ምንዛሪ ገቢውን የሚያመላክቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በዚህን ያህል ደረጃ ዕድገት ያልተመዘገበ መሆኑን ነው፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት የውጭ ምንዛሪ ገቢው 562.2 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ገቢ ባገኘበት ወቅት አስመዝግቦት የነበረው ዕድገት ምጣኔ አምስት በመቶ ብቻ እንደነበር መግለጹ አይዘነጋም፡፡

በ2013 የሒሳብ ዓመትም 602.8 ዶላር ገቢ ማግኘቱን፣ የዕድገት ምጣኔው 9.3 በመቶ ብቻ እንደነበር፣ በ2014 ሒሳብ ዓመት ደግሞ 708 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት በሒሳብ ዓመቱ ዕድገቱ 17.4 በመቶ ብቻ ስለነበረ በ2015 የሒሳብ ዓመት የተገባው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዕድገት ከፍተኛ ሊባል የሚችል መሆኑን አስታውቋል፡፡    

በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመኖሩና ለማግኘትም እጅግ ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ገቢውን በዚህን ያህል ደረጃ ማሳደግ መቻሉ ትልቅ አፈጻጸም ነው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማድረስ ከቻሉት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከአዋሽ ባንክ ቀጥሎ ዳሸን ባንክ ሦስተኛው ባንክ መሆን ያስቻለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ባንኩ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው በጠቅላላ ጉባዔው እንደተለገጸው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የሚባል የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተገኘው በባንኩ ደንበኞች አስተዋጽኦ ነው፡፡ በዋናነት ግን ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር የሚያከናውነውን ሥራ በማስፋቱ፣ አፈጻጸሙ ከፍተኛ እንዲሆን ማስቻሉን አቶ አስፋው ገልጸዋል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዳሸን ባንክ ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አቅራቢ ተቋማት ጋር በመደራደር በውጭ ምንዛሪ ብድር ለማግኘት የመጀመሪያ መሆን የቻለ መሆኑን፣ አሁንም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ብድር ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡  

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ከዚህ ቀደም ከሁለት ዓለም አቀፍ ገንዘብ አቅራቢ ተቋማት ጋር በመደራደር ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ያገኘው፣  ‹‹British International Investment›› እና ‹‹Dutch Entrepreneurial Development Bank›› ከተባሉ ብድር አቅራቢዎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁንም ይህንኑ ጥረት በመቀጠል ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተጨማሪ ብድር ለማግኘት እየተደራደረ መሆኑንና ውጤቱንም በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የሚገኝ ብድርን በተመለከተ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን እንዳሉት፣ ባንኩ እንዲህ ያለውን ዕድል ማግኘቱ በአገር ደረጃ ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ገብተው እንዲሠሩ መሠረት የጣለ ከመሆን ባለፈ፣ ባንኩን ከሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ አቅራቢ ተቋማት ጋር በቀላሉ እንዲሠራና ሌሎች ተጨማሪ በውጭ ምንዛሪ የሚቀርቡ የፋይናንስ አማራጮችን እንዲያገኝ የሚረዳው ነው፡፡  

የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ በተለይ በግብርና ምርት ላይ በተሰማሩና ወደ ውጭ ምርታቸውን ለሚልኩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች በብድር መልክ እንዲቀርብ በማድረግ፣ የወጪ ንግዱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያግዝ ይሆናል ተብሏል፡፡ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ተበዳሪ የወሰደው ብድር ከእነ ወለዱ በውጭ ምንዛሪ የሚከፈል እንደሚሆንም አቶ አስፋው አስድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች