ለኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የጠለፋ መድን ሽፋን የሚሰጡ የውጭ ኩባንያዎች ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የኢንሹራስ ሽፋን ዓይነቶች ላይ የጠለፋ ዋስትና ላለመስጠት ገደብ መጣላቸው ተሰማ፡፡
ከአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የፀጥታ ችግር ባላቸው አካባቢዎች በተለይም ደግሞ ለፖለቲካዊ ግጭት (Political Violence) የመድን ሽፋን ለሰጡ የአገር ውስጥ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለሰጡት ሽፋን የጠለፋ ዋስትና አገልግሎት እንደማያገኙ አስታውቀዋቸዋል፡፡ በቅርቡም በአማራ ክልል በተፈጠረው አለመረጋጋት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለፖለቲካዊ ግጭት የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጡ ከሆነ የጠለፋ መድን ዋስትና እንደማይሰጣቸው አሳስቧቸዋል፡፡ በተመሳሳይ በትግራይ ክልልም ለ‹‹ፖለቲካል ቫዮለንስ›› የኢንሹራንስ ሽፋን ቢሰጡ የጠለፋ መድን ሽፋኑን እንደማያገኙ ገደብ ማስቀመጣቸውን ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሽፋን በመስጠት የሚታወቀው የአፍሪካ ሪ የተባለው የጠለፋ ዋስትና አግልግሎት አቅራቢ መሆኑን የሚጠቁመው ይኼው መረጃ፣ በቅርቡ በአማራ ክልል ተፈጻሚ እንዲሆን የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአካባቢው ‹‹የፖለቲካል ቫዮለንስ›› የመድን ሽፋን እንዳይሰጥ የጣለውን ገደብ ለሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሳውቋል፡፡
በዚህም ምክንያት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀደም ብሎ በትግራይ፣ አሁን ደግም በአማራ ክልል ለፖለቲካ ቫዮለንስ የመድን ሽፋን ከመስጠት እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል፡፡ የሚሰጡም ካሉም በራሳቸው ኃላፊነት የሚሰጡት እንደሚሆን ያነጋገርናቸው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኃላፊዎች ገልጸው፣ በራሳቸው ኃላፊነት የሚሰጡ ቢኖሩ የሚሸከሙት ከፍተኛ ኃላፊነት ስለሚሆን ያለ ጠለፋ መድን ሽፋኑን ይሰጣሉ ተብሎ እንደማይታመንም አክለዋል፡፡
በተመሳሳይ በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት ሳቢያ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ተመሳሳይ ገደብ መጣላቸውንና ይህንንም ገደብ ሳያነሱ እስካሁን መቆየታቸው ጦርነቱ አካባቢ ለሚጫን ዕቃ የማሪን ኢንሹራንስ እንዳይሰጡ እያደረጋቸው ነው፡፡
በዚህ ጦርነት ሳቢያ ጦርነቱ አካባቢ ይሰጡ የነበረውን የጠለፋ መድን ማቆማቸውን በማስታወቃቸው፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ከጦርነቱ አካባቢ የሚነሱ ጭነቶች የማሪንና የባህር ላይ ኢንሹራንስ ሽፋን ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የኢትዮጵያን አብዛኛውን የጠለፋ መድን ሽፋን የሚሰጠው አፍሪካ ጦርነት ካለባቸው አካባቢዎች ለሚነሱ ግጭነቶች የጠለፈ መድን ሽፋን የማይሰጣቸው መሆኑን አሳውቋቸዋል፡፡ በመሆኑም ብዙዎቹ የኢንሹራንሰ ኩባንያዎች ከዩክሬንና ከሩሲያ ለሚነሱ ግጭቶች የጠለፋ መድን ሽፋን ስለማያገኙ የማሪን ኢንሹራንስ እየሰጡ ባለመሆኑም እንዲህ ካሉ የኢንሹራንስ ሽፋኖች ያገኙ የነበረውን ገቢ በእጅጉ እየጎዳው ነው፡፡
ከእነዚህ ሌላ በሌሎቹ የመድን ሽፋን ዓይነቶች ላይም የጠለፋ መድን ሰጪዎቹ ገደብ እየጣሉ መሆኑን ያስታወሱት የኢንሹራንስ ባለሙያዎቹ፣ የእነዚህ ገደቦች መደራረብ የዓረቦን ገበያቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ ስለመምጣቱ አልሸሸጉም፡፡ ሌላው ሥጋታቸው በቅርቡ በተጠቀሰው የእስራኤልና ሐመስ ጦርነት በዚያ አካባቢ በሚያልፉ ጭነቶች ላይ ተመሳሳይ ዕርምጃ ከወሰዱ ሁኔታውን አሳሳቢ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
በእስራኤልና ሐማስ ጦር ምክንያት የጠለፋ መድን ሰጪዎቹ ገደብ የሚጥሉ ከሆነ፣ ነገሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ብዙ የጭነት ጭቃዎች በቀይ ባህር የሚመጡ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ከባድ ይሆናል፡፡ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት እምብዛም ጫና ያላሳደረው ብዙ ዕቃዎች ከዚያ አካባቢ ያለመሆናቸው ነው፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ አብዛኛው ጭነቶች የሚያልፉት በቀይ ባህር በመሆኑና በደቡበ አፍሪካ በኩል የሚመጡት ጭነቶች ጥቂት ስለሆኑ አሁንም ጦርነቱን አሳብበው የጠለፋ መድን ሰጪዎቹ ገደብ የሚጥሉ ከሆነ የማሪን የኢንሹራስ ሽፋን መስጠት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ በአሁኑ ወቅት የማሪን ኢንሹራንስ ሽፋን የተቀዛቀዘው በተጣሉ ገደቦች ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ቅናሽ ከማሳየታቸው ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ፣ እኚሁ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
አብዛኛው የአገሪቱ የኢንሹራንስ ሽፋን ከጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር የሚሠራ ከሆኑ አንፃር እነርሱ በተለይ ከፀጥታ ችግር ጋር የሚጥሉት የአንዳንድ የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነቶች ሽፋን እንዳያገኙ እንደሚያደርግ ያረጋግጣሉ፡፡
የጠለፋ መድን ሽፋን ኩባንያዎቹ ለሚሰጡት የጠለፋ መድን ሽፋን አገልግሎት የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከዓመታዊ የዓረቦን ገቢያቸው እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ለጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች የሚያውሉ ስለመሆኑ ሲገለጽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡