Monday, December 11, 2023

የፍትሕ ሚኒስቴርን ወቅታዊ ቁመናና ዘርፉን ይለውጣል የተባለው አዲስ ፍኖተ ካርታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት በኢትዮጵያ ፍትሕና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢናገርም፣ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ቀላል አለመሆኑን፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ባለው የዓቃቤ ሕግ ዘርፍ የገለልተኝነት ጉዳይ ላይ በርካቶች ጥያቄ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡

የሕግና የፖለቲካ ምሁራን የፍትሕ ሚኒስቴር ተቋማዊ አወቃቀር በብዙ አገሮች ያልተለመደ መሆኑን፣ የገዥው መንግሥት ጉዳይ አስፈጻሚ የመሆን ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ በመጥቀስ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም እንዲሆን በተደጋጋሚ ሲያሳስቡም ይታወቃል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፍትሕ ሚኒስቴርን የ2016 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የገመገመ ሲሆን፣ በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅትንና የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ፎኖተ ካርታን የተመለከተ ሰነድ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሕዝቡ በፍትሕ ዘርፉ ላይ እሮሮና አቤቱታ እያሰማ መሆኑን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትም የሚነሱ አቤቱታዎች መኖራቸውና የፍትሕ አመራሮችና ባለሙያዎች በተወሳሰበ ችግር ውስጥ አመርቂ ሥራ አልሠራንም በማለት መልከ ብዙ ቅሬታ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች መካከል በመረጃ አያያዝ ረገድ የተመለከተው ይጠቀሳል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ ተፈጽሟል ከተባለው ወንጀል ውስጥ ምን ያህሉ በምርመራ ተጣርቶ እንደተለየ የሚያሳይ አመላካች መረጃ የለም ብለዋል፡፡ እንዲሁም ዘርፉ ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍልሰት እያጋጠመው መሆኑን ጠቅሰው፣ ፓርላማው ከፍተኛ የሆነ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር በሰባት የመንግሥት ተቋማት ግዙፍ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሎች ተመርምረው አስተያየት መስጠቱን የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ በዚህ ረገድ ፓርላማው የመንግሥት ተቋማትን በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ቢያደርግ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም የመንግሥትና የሕዝብን ‹‹ፍትሐ ብሔራዊ ጥቅም›› ለማስጠበቅ በ25 መዛግብት ላይ ክርክር እየተካሄደ መሆኑን፣ እነዚህ መዝገቦች ሰባት ቢሊዮን ብር የሚገመቱ አከራካሪ ጉዳዮች መያዛቸውን፣ በተመሳሳይ በግልግል ዳኝነት ከ350 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ክርክር እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ በወንጀል ምርመራ እንዲሁም በወንጀል ክስ ለማቃናት ከመሞከር ይልቅ የመንግሥት ፍትሐ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ውል የሚገባበት አካሄድ፣ ባለሀብቶች የሚስተናገዱበት አሠራር በጥንቃቄና በቅንጅት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ፓርላማው ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ መጠን ያላቸው የኢንቨስትመንት ክሶች ቢመጡና አንዴ ወደ መካሰስ ከተገባ በኋላ ወጪው በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር እንዳይሆን እሠጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም የውል አስተዳደሮችና የውል ክትትሎች ችግር ሲያጋጥም መፍትሔ የሚሰጥበትን መንገድ ሁሉም ተቋማት በቅንጅት እንዲሠሩ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ከበጀት ጋር የሚገጥማቸውን ችግር ሲያብራሩ ባለፉት ሦስት ወራት በማረሚያ ቤቶች ለ720,729 ታራሚዎች ምግብ ማቅረቡን ገልጸው፣ የበጀት ችግር ታራሚዎችን ለመቀለብና ለማረሚያ ቤት ፖሊስ ሊቀርቡ የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅሞች እንዳይሳኩ አድርጓል ብለዋል፡፡

ሌላው በማረሚያ ቤቶች አንገብጋቢ የሆነ ችግር በማለት የገለጹት ሚኒስትሩ የታራሚዎች በጀት ሲሆን ለአንድ ታራሚ ለቁርስ፣ ለምሳና ለእራት የተመደበው በጀት በጣም አናሳ ነው ብለዋል፡፡ ይህ ችግር ሲያጋጥም ሁሉም ጉዳይ የሰብዓዊ መብት ሆኖ እየቀረበ በመሆኑ፣ የታራሚዎችን ጤንነትና ደኅንነት ለመጠበቅ ከሌላ በጀት በመመደብ የቅድሚያ ቅድሚያ ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የሰው ኃይል ፍልሰት በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ጠቅሰው፣ ለተቋሙ የሚቀጠሩ ሠራተኞች መጀመሪያ ለጥቂት ጊዜያት ልምድ ለማግኘት እንደሚቆዩ፣ በተቋሙ ያለው ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ የማያስቆይ በመሆኑ የተሻለ ሥራ ፍለጋ እየፈለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ልምድ ያለው የሰው ኃይል ፍልሰት አሳሳቢ መሆኑን ያስረዱት ጌዲዮን (ዶ/ር) ቁጥሩን ከመናገር ቢቆጠቡም፣ በተለይ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ወደ ባንኮች እየፈለሱ መሆናቸውንና ዓቃቢያነ ሕጎች የራሳቸውን ቢሮ ከፍተው ለመንቀሳቀስ ከተቋሙ በስፋት እየለቀቁ ናቸው ብለዋል፡፡

የወንጀል ሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕጉ ፀድቆ ወደ ሥራ አለመግባቱ በተቋማቸው ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የገለጹት ጌዲዮን (ዶ/ር)፣ ጊዜና ገንዘብ ሊቆጥቡ የሚችሉና የባለጉዳዮችን እንግልት ሊያስወግዱ የሚችሉ ዘመናዊ አማራጮችን ለመተግበር የሚያመቸው የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሲፀድቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ በአጠቃላይ የፍትሕ ዘርፉን በመሠረታዊነት ይለውጣል የተባለ ጠንካራ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን (ፍኖተ ካርታ) ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የፍትሕ ሚኒስቴር በአጠቃላይ ዘርፉን የሚገጥሙ ችግሮችን በመረዳት፣ የተለየ ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል ትልም በመያዝ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩ የማሻሻያ መርሆዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሕገ መንግሥቱን ባከበረና ዘላቂ የአገረ መንግሥት ግንባታና ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ በጎ ጉዳዮችን በማካተት ችግሮችን ለመቅረፍ የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ላይ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ይህንን ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት በ1950ዎቹ የተደረጉ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያዎችን፣ በ1966 ዓ.ም. ከአብዮቱ ጋር ኅብረተሰባዊነት ቅኝት ያላቸውን ሕጎች ለማውጣት የተደረገውን ጥረት፣ በድኅረ 1983 ዓ.ም. ለውጥ የፍትሕ ሥርዓቱን ያልተማከለና ፌዴራላዊ ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎችን፣ ሁሉን አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራምና በ2010 ዓ.ም. በሕግና ፍትሕ ማሻሻያ የተለወጡ ሕጎችን ጠንካራና ደካማ ጎናቸውን በጥናት መለየቱን አክለዋል፡፡

በፍትሕ ዘርፉ ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል ከተባለው ፍኖተ ካርታ ውስጥ አንዱ ‹‹የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት›› ማሳደግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በተደረጉ ጥናቶች በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓትና መንግሥታዊ የፍትሕ መዋቅር ያለው የፍትሕ ተደራሽነት ከ20 በመቶ በታች መሆኑን ጌዲዮን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አገሪቱ አሁን ባላት በጀትና የሰው ኃይል አደረጃጀት መደበኛውን መዋቅር አስፋፍቶ ተደራሽ መሆን አይቻልም የሚለው የማሻሻያው መነሻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዘመናዊ መደበኛ የፍትሕ ሥርዓት ከማኅበረሰቡ እሴትና አስተሳሰብ ጋር የተቀራረበ ባለመሆኑ፣ የፍትሕ ዘርፉን ቅቡልነትና ተዓማኒነትን የሚሸረሽር ስለሆነ መሠረቱን ማኅበረሰብ ያደረገ የፍትሕ ሥርዓት በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡

በማሻሻያው ውስጥ የቀረበው ሌላው ጉዳይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው ግጭት የመፍቻና ፍትሕ የማምጫ ልማዳዊ ሥርዓት፣ ከዘመናዊና ከመደበኛው የፍትሕ መዋቅር ጋር እርስ በርስ የሚተዋወቅና የሚናበብ መሆን ስላለበት ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕጎች በ1950 እና በ1960ዎቹ ሲወጡ ያረቀቋቸው የውጭ ዜጎች መሆናቸውን፣ ባለሙያዎቹ ኢትዮጵያ ሳይመጡ የኢትዮጵያ የሚባለውን ነገር ኋላቀርና ዘመኑ ያለፈበት በሚል ባለማካተት ሙሉ በሙሉ አዲስ ዓይነት ሕግ ማውጣታቸውን አውስተዋል፡፡ ስለሆነም ይህ አካሄድ ላለፉት 60 ዓመታት በመሞከሩና የሚያዋጣ ባለመሆኑ ለውጥ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፍትሕ ዘርፉ ከሥነ ምግባርና ከብቃት ጋር የተገናኙ ችግሮች በመደበኛው አሰራር ብቻ ሊቀረፉ ስለማይችሉ፣ ጥንቅቅ ያለ (vetting) አሠራር በመተግበር አመራሩንም ሆነ ባለሙያውን ከብቃትና ከሥነ ምግባር አንፃር ማጥራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ረገድ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የፍትሕ ተቋማት ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ያልገቡና በወረቀት ላይ የተመረኮዙ በመሆናቸው፣ የመረጃ አጠቃቀምና ውጤታማ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ በፍትሕ ዘርፍ ማምጣት የዚህ ፍኖተ ካርታ ሌላኛው ትልም ስለመሆኑ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በዝግጅት ላይ ያለው ፍኖተ ካርታ አንዱ አካል የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ሕግን ማዘመንና መለወጥ ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያገለገለ በመሆኑ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ረቂቅ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ፀድቆ ወደ ሥራ መግባት አለበት ብለዋል፡፡

ሁሉም ጉዳይ በአንድ ሐዲድ ላይ መሄድ የለበትም ያሉት ሚኒስትሩ፣ ፍኖተ ካርታው የአስተዳደር ፍትሕን በአዲስ ዕይታ ለማየት የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚ,ህ መሠረት እስካሁን በኢትዮጵያ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር በሚል ከሚታወቀው የፍትሕ ጉዳይ በተጨማሪ የአስተዳደር ፍትሕ ራሱን የቻለ የፍትሕ ዘርፍ ሆኖ ተጠናክሮ እንዲወጣ የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው የሕግ ድጋፍና ንቃተ ሕግን ያጠናክራል የተባለበት ሲሆን፣ አሁን አለ በሚባለው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ ጉዳይ ገጥሟቸው የጠበቃ ወይም የሕግ አገልግሎት የሚያገኙ ሰዎች ከአንድ በመቶ የማይበልጡ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ ፍትሕን ማረጋገጥ ስለማይቻል፣ ማሻሻያው የተለዩ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የፍትሕ ዘርፍ ተቋማትን አደረጃጀት ማስተካከልና ዘርፉን ሳቢና ተዓማኒነት የተቸረው ማድረግን ያለመ ማሻሻያ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ አሁን ባለው ሁኔታ በፍትሕ ተቋማት ላይ ሰው እጁን አፍታቶ በራሱ ጠበቃ የሚሆንበት፣ በማረሚያ ፖሊስ ከተለማመደ በኋላ ወደ ባንክ ጥበቃ የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ፍኖተ ካርታው በቀጣይ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ይዞ ለማቆየት እንደሚያስችል ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ጫናዎች የሚደርስባቸውና ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚያገለግሉ ባለሙያዎች የኑሮአቸውና የሥራቸው ሁኔታ መሻሻል ያለበት በመሆኑ፣ ይህን ለመለወጥ ከአደረጃጀት ጀምሮ መከናወን ያለባቸው ተግባራት በፍኖተ ካርታው መካተቱን አስረድተዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ዓምደ ገብርኤል አድማሱ እንደሚሉት፣ በ1950ዎቹ እንግሊዛውያንና ፈረንሣውያን አዘጋጅተው ያመጡት የሕግ ሥርዓት በመሆኑና ባህላዊ ሕጉን ባለማካተቱ፣ አሁን እንዲካተት መደረጉ በብዙ ገጽታው በፍትሕ ዘርፉ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡

በመሆኑም በዚህ በታሰበው ማሻሻያ በየክልሉና በየብሔረሰቡ የሚታዩ ባህላዊ የሽምግልናና የድርድር ዘዴዎች ቢታዩ፣ በወንጀል ዘርፉ ፖሊስ ከሚመረምረው ባሻገር በአካባቢው ሰዎች በባህላዊ መንገድ አጣርተው አውጫጪኝ ቢደረግና በሕዝቡ ውስጥ መከባበርንና እውነት ፈልጎ ማግኘት ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ የሚያመጣ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ባህላዊ ሥርዓት በአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ባለመካተቱ ጉድለት መፍጠሩን፣ በማሻሻያው ባህላዊው በሕግ ውስጥ ተጠቅሶ በአንቀጽ ሲቀመጥ የመከበር ዕድሉ ሰፊ ይሆናል ብለዋል፡፡

በሌላ መንገድ ለፍርድ ቤት፣ ለጠበቃና ለዳኝነት ክፍያና የመመላለሻ ጊዜና ከዘለቄታዊ ፍትሕ አንፃር ባህላዊ አሠራር ቢካተት ትልቅ ትርጉምና ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -