Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርትንሿ ምላጭ ዓለምን ትላጭ...

ትንሿ ምላጭ ዓለምን ትላጭ…

ቀን:

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

የእስራኤልና የሃማስ ጦርነት ቀስ እያለ ጎራ እየፈጠረ መሄዱ አይቀሬ ነው። ለምን ብትሉ “በመብረቃዊው” የሃማስ ጥቃት ከእስራኤል ይልቅ አሜሪካ በእጅጉ ደንግጣለች። እናም፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች በድሮ ዘመን ግንኙነት ሴራ እየሸረቡ ከሆነ ማንም ሊደርስባቸው አይችልም። እኛ በድሮ ዘመን ስለሌላ ሰው አስርገን ለማስገባትም ረፍዶብናል። ሰዓቱ ስላለፈ ይህንን ማድረግ አንችልም። አሁን ጥብቅ ቁጥጥርና ጥበቃ ብቻ ሳይሆን እነዚህን እናንተ ካልጠፋችሁ እኛ መኖር አንችልም የሚሉ አጥፍቶ ጠፊዎች፣ ቤታቸው ደረስ ሄደን የሚመኩበትን የጦር መሣሪያና የጦር ኃይል ሁሉ ማውደም አለብን…፤›› ብላ የደመደመች ይመስላል አዝማሚያዋ።

ይህ ሁኔታ ገና ያልፍልናል ለሚሉ ደሃ የአፍሪካ ዜጎች ይዞ የሚመጣው ዘርፈ ብዙ ችግር ይኖረል። በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮው ዘርፍ እንደሚታወቀው አፍሪካ ወርቅ ብትሆንም ትምህርት በሕዝቦቿ ውስጥ ባለመስረፁ ለራሷ ዜጎች “የመዳብ“ ያህል ጥቅም መስጠት ሳትችል ኖራለች። በድህነት ማጥ ተዘፍቃ ኖራም፣ እነሆ አዕምሮ ቢሶቹ ጀብደኞችና ኃያላኑ ባመጡት ጦስ ልትጠፋ ነው። ሆኖም ያለ ሥራዋ መጥፋት አልነበረባትም። ይሁን እንጂ የኑክሌር ጣጣ ከመጣ ያላለፈለት ሕዝቧ በሥልጣኔ ከመጠቀው ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ ሕዝብ ጋር ለዘለዓለም መጥፋቷ ግድ ይሆናል።

እስከ ዛሬ አፍሪካ ያላለፈላትና በድህነት ተኮራምዳ ከሁለት ሺሕ ዓመት በላይ የኖረችው ለምንድነው? የተለያዩ ትንተናዎችን የአውሮፓ ምሁራን ቢሰጡም አሳማኙ ትንተና ከሰባ ዓመት በፊት መሪዎቿን በተመለከተ በአንድ ጸሐፊ የተሰጠው አመክንዮ ሚዛን ይደፋል፣ እጠቅሳለሁ፡፡

“The Presidency [in Africa] is a family business and there is no future or monetary gain outside politics. Accumulating wealth and business opportunities are tied to controlling the state. So, is the economic fortunes of your allies, party officials and, crucially, the President’s family. Once you are out of off ice, you lose your ability to steer contracts or get a cut from profits.  (http://africasacountry.com/ March 11, 2016)” በዚህ ምክንያት ያላለፈላት የዛሬዋ አፍሪካ በኃያላኑ ጦስ እስከ ወርቅና ዕንቁዋ ለዘለዓለም ልታንቀላፋ ትችላለች።

በነገራችን ላይ አፍሪካ ውስጥ ሥልጣን የሚፈልግ ቡድን ወይም ፓርቲ በሙሉ ሥልጣንን እስከሚጨብጣት ድረስ፣ የሕዝብ አገልጋይና ለዜጎች ያልተሸራረፈ መብት ተሟጋችና ከሕግ በታች እንደሆነ በቃላትም በድርጊትም ያሳያል። ሺሕ ጊዜ በመማል ጭምር ከፍተኛ ቅስቀሳ በማድረግ ሺዎችን ከጎኑ ለአመፅ ያሠልፋል። ሥልጣን ቢጨብጥ ሕዝብን እንጂ ራሱን ለማበልፀግ እንደማይሻ ምሎ ይገዘታል።

በዚህ መኃላና ግዝቱም ዜጎች ተስፋ ይጥሉበትና ድጋፋቸውን ይሰጡታል። ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን የራሱን የጥቅም አጋሮች አደራጅቶ የአገር ሀብት ይዘርፍና በአጭር ዓመታት ውስጥ ድህነትን ይሰናበታታል።

ይህ ያልተገባ መንደላቀቅና መሞላቀቅ በሕዝብ ተቃውሞ የውኃ ሽታ እንዳይሆን “በዘረፋ ሸሪኮቹ አማካይነት“ ሥልጣኑን በገንዘቡ እየታገዘ በመሣሪያና በእስር ቤት እያስፈራራና ሕግን እየደፈጠጠ ያለ እንቅልፍ እንዲጠበቅ ያደርጋል።

ፓርቲው ፍፁም ቤተሰባዊና በኃጢያት የተነካካ እንዲሆን በማድረግም፣ የፓርቲውን አባላት “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ” ይላቸዋል። ከቀድሞ መንግሥት ውድቀት ተማሩ በማለት እንደ ጀርመናዊው ፈላስፋ ኒቼ ሞራልን በባለፀጎችና በድሆች ደረጃ በማስቀመጥ፣ የገዥ ሞራል እንዲኖራቸው ለደቀ መዝሙራቱ ያለ ማቋረጥ ምክር ይሰጣል። ‹‹ሞራልና ሥነ ምግባርን እርሱት፣ እሱ የጅሎች ፍልስፍና ነው፤›› ይላቸዋል።

እንደምታውቁት ሞራል ወይም መልካም ሥነ ምግባር ለአርስቶትል፣ ለካንትና ለኒቼ የተለያየ ትርጉም አለው። ስለሞራል ወይም “ኤቲክስ” ካንት፣ አርስቶትልና ኒቼ የተለያየ ምልከታ አላቸው። ካንት ሰው ደስታው በሥቃይ ውስጥ እንዲበዛ መጣርና ሰውን ደስተኛ የሚሆንበትን ከባቢ መፍጠር ነው ሞራል፤” ይለናል። አርስቶትል ደግሞ ‹‹ሞራል ወይም ኤቲክስ ለአንተ ሊደረግልህ የምትፈልገውን ለሌሎችም ማድረግ ነው፤›› ብሎ ይሞግታል።

ኒቼ ደግሞ ‹‹ሞራል የሞኞች ተግባር ነው። የተሸናፊዎችም መፈክር ነው። እናም ሞራል እያልክ ራስህን አታሞኝ፤›› ይላል። እንግዲህ ተርታው ሕዝብ ሁሌም ከሞራል አንፃር ተጎጂ ነው። ሥነ ምግባር ወይም ሞራል በሚባል ነገር ተተብትቦ ስለሚያዝ ሁሌም ተገፊ ይሆናል እንጂ ገፊ አይሆንም  ባይ ነው ኒቼ።

እንግዲህ የአርስቶትልን ዓይነት ሞራልን ዓለም መመርያው እስካላደረገ ድረስ የአፍሪካም ሆነ የእስራኤልና የፍልስጤም፣ እንዲሁም የዩክሬኖች ሥቃይ አያባራም። የዓለም ሰው ነቅቶ ወይም በትምህርት አዕምሮው በስሎ ሁሉም ሰው አጭር ሕይወቱን የሚያጣፍጥበት የተሻለ የፖለቲካና የማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብር በዓለም እንዲፈጠር እስካላደረገ ድረስ፣ ሰው መሞቱ ላይቀር እርስ በርሱ በድንቁርና እየተጨፋጨፈ መኖሩ እንደሚቀጥል አትጠራጠሩ።

መደምደሚያ

እነሆ ትምህርት በቅጡ በዓለም ሕዝብ አዕምሮ ባለመስረፁ የተነሳና በእርስ በርስ ጦርነት ሰበብ፣ ታላቋና ወርቋ አፍሪካ ለዜጎቿ ችግርና ችጋር ሆናለች። ዓለምም በትንሿ ክብሪት የተለኮሰ እሳት እየተፋፋመ ገሚስ አካሏን ወላፈኑ እየለበለባት ነው።  በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሰው ዘር በዘመናዊ መሣሪያ እየደበነ ኡ…ኡ… እያለ ነው። በትንሿ ምላጭ ዓለም እንዳትላጭና ፍጥረት ሁሉ ታሪክ እንዳይሆን ልበ ብርሃኖች የወንድሜና የእህቴ ሥቃይ፣ የሰው ሥቃይ የእኔም ነው በማለት ባለሥልጣናትን በብርቱ ሊቃወሙና ወደ ትክክለኛው የሰላም መንገድ ሊያመጧቸው ይገባል።

“አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ

ነገራችን ሁሉ ይሆናል የእምቧይ ካብ… የእምቧይ ካብ…” (አገሬ የሚለውን ዓለም በሚለው ተኩልኝ) እንዳሉት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ዛሬ ቆም ብሎ የዓለም ኃያል ነኝ ባይ ሁሉ ካላሰበ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት መነሳቱ አይቀሬ ይሆናል። ይህ ጦርነት ከተነሳ ደግሞ በምድራችን ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሁሉ እንደሚጠፉና የሰው ታሪክ ነጋሪ እንኳን እንደሚያጣ ከወዲሁ መገንዘብ መልካም ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው mekonnenshawelsun@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...