Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና ልዩ ትኩረት በአፋር ሦስት ማዕዘናዊ አቀማመጥ (ክፍል...

የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና ልዩ ትኩረት በአፋር ሦስት ማዕዘናዊ አቀማመጥ (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በተሾመ  ብርሃኑ ከማል

ውድ አንባቢያን በክፍል አንድ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ሲባል ምን ማለት እንደሆነና ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ካሉት አገሮች ቀዳሚ ተጠቃሚ መሆኗን ከጥንታዊ ታሪኳ ተነስተን በትንሹም ቢሆን አቅርቤያለሁ፡፡ በዚህ ዕትም ደግሞ በቅድሚያ ከቀይ ባህር ጂኦ ፖሊቲክስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ እንዲሁም የመን እጅግ አሳሳቢ በሆነ ችግር ላይ መገኘታቸው ለሁላችንም ገና በሚገባ ግልጽ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የተሞከረ ሲሆን፣ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮች ግልጽ ይሆኑልን ዘንድ በኤርትራ ሪፈረንደም ምክንያት ኢትዮጵያ እንዴት ወደቧን አጣች የሚለውን ለግንዛቤ ያህል እንመለከታለን፡፡

አደገኛው የቀይ ባህር ጆኦ ፖለቲክስ

ከቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኬንያ፣ እንዲሁም የመን እጅግ አሳሳቢ በሆነ ችግር ላይ መገኘታቸው ለሁላችንም ገና በሚገባ ግልጽ የሆነ አይመስልም፡፡ ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው ኢኮኖሚ ምክንያት የቀይ ባህር የንግድ መስመርን ለመቆጣጠር የሚሹት ከበርቴ አገሮች በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ በወታደራዊ ኃይል የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ የተፋጠጡበት ሥፍራ በመሆኑ የእነዚህ አገሮች ሕዝብ የደኅንነት ሥጋትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄድ ላይ እንደሚገኝ ብዙዎቻችን ትኩረት አልሰጠነውም፡፡

ዛሬ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን በወዳጅነት የቀረቡ፣ ቀርበውም በልዩ ልዩ መተያያ፣ መማለጃ፣ ስጦታ፣ ቸርነት የተሞላበት ልገሳ፣ ብድርና የብድር ልገሳ ስለተረፋቸውና ስለተትረፈረፋቸው የሚሰጥ እንዳልሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ የአገሪቱ ሕግ አውጭዎች፣ አስፈጻሚዎችና ተርጓሚዎች አንዱ ኢትዮጵያዊ በአገሩ በማንኛውም ሥፍራ የመቀመጥና የመሥራት መብቱ ተነጥቆ ሲገደል፣ ሲፈናቀልና የመከራ ገፈት ቀማሽ ሲሆን ‹‹ለምን?›› ብለው አለመጠየቃቸው ሚስጥር በአንዱ ወይም በሌላው ከቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ‹‹እርስ በርስ መጨፋጨፋችን ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር በሚሹ ኃይሎች (አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ፣ ኢራን፣ ግብፅ) የተሸረበ ሴራ ሊሆን ይችላልና ልብ እንግዛ፡፡

ያለ ምንም ጥርጥር የቀይ ባህር የንግድ መስመርን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በጦር ኃይል ለመቆጣጠር ከ120 ሚሊዮን በላይ ያላት ኢትዮጵያ ጠንካራ ሆና መገኘት ዓላማቸውን እንደሚያደናቅፍባቸው ሁሉም ኃያላን መንግሥታት አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች እንደ ፔንዱለም ከግራ ወደ ቀኝ የሚወዛወዙበት ሳይሆን፣ ሰላማዊ ግንባታ የሚካሄድበትን መላ አበጅተው ሕዝባቸውን ከጥፋት ለማዳን መንቀሳቀስ ያለባቸው ዘመን ነው፡፡ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ሰለባ የሆኑ የእኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ አክቲቪስቶች፣ አገር ወዳድ ነን ባዮች ይህንን ሀቅ በግልጽ ሊረዱ ይገባል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ1880ዎቹ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫት እንደተከፋፈሉ፣ በ2020ዎቹ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጠብ በመጫር አገራቸውን እያዳከሙ መሆናቸውን መረዳት አለብን፡፡ ካልተረዳንና ሁላችንም ራስ ወዳድ፣ ሥልጣን ወዳድ፣ ገንዘብ ወዳድ ከሆንን ሶማሊያ የፈረንሣይ ሶማሌላንድ፣ የእንግሊዝ ሶማሌላንድ፣ የኢጣሊያ ሶማሌላንድ እንደተባለች ኢትዮጵያ ሳዑዲላንድ፣ ኢትዮጵያ ኢምሬትላንድ፣ ኢትዮጵያ አሜሪካላንድ፣ ኢትየጵያ ፍሬንችላንድ፣ ኢትዮጵያ ቻይናላንድ መባላችን አይቀርም፡፡ ዛሬም ብዙ ጁሴፔ ሳፔቶች፣ ብዙ አባ ማስያሶች፣ ብዙ የጂኦግራፊክ ማኅበረሰቦች በጉያችን እንደሚገኙ እንድናሰላስል አደራ እላለሁ፡፡

ኢትዮጵያ ወደብ ያጣችበት የኤርትራ ሪፈረንደም አጭር ታሪክ

እንደሚታወቀው የኤርትራ ሕዝብ ነፃነት ግምባር (ከኢሕአዴግ በተደረገለት ወታደራዊ ዕርዳታ ጭምር) በሚያዚያ ወር 1983 ዓ.ም. የደርግን ሠራዊት ድል በማድረግ ኤርትራን ተቆጣጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት የኤርትራ ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥት መሪዎች የመጡትም በታዛቢነት ነበር፡፡ በኤርትራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት መዋቅር ስለፈረሰ፣ በዚያው የነበሩ ኢትዮጵያውያን የመንግሥት ሠራተኞች ለርክክብ ካልሆነ በስተቀር የሚሠሩት ሥራ አልነበረም፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን የኤርትራ ሪፈረንደምን የማካሄድ ኃላፊነቱ የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ማድረግ የምትችለው እንደ ማንኛውም ታዛቢ አገር ሬፈረንደሙ በትክክል ተካሂዷል ወይስ አልተካሄደም ብላ መታዘብ፣ ትዝብቷንም ለኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማቅረብ ነው፡፡

ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ከመፅደቁ በፊት ነፃነቷን ያሳወቀችው ኤርትራ፣ በሽግግር መንግሥቱ በታቀደው መሠረት ሪፈረንደሙ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ማካሄዷን ለማሳየት የሚያስችል ሁኔታ አመቻቸች፡፡ በዚህም መሠረት በሚያዚያ ወር 1984 ዓ.ም. የሪፈረንደም አዋጅ ቁጥር 225/1984 አወጀች፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ ሪፈረንደሙ እንዴት እንደሚካሄድ ዝርዝር መግለጫ የወጣ ሲሆን፣ ይህንንም ሥራ ተከታትሎ የሚያስፈጽምና የሚከታተል የኤርትራ የሪፈረንደም ኮሚሽን ተቋቋመ፡፡ ከሪፈረንደሙ ኮሚሽን ሥልጣንና ተግባር መካከል አንደኛ ሪፈረንደሙ ነፃና ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ሁለተኛ ለሪፈረንደሙ ድምፃቸውን ሊሰጡ የሚገባቸው ኤርትራውያን እነ ማን እንደሆኑ ለይቶ ማወቅና መመዝገብ፣ ሦስተኛ ሪፈረንደሙ የሚካሄድበትን አመቺ ሁኔታ መፍጠርና ድምፅ የሚሰጡ ኤርትራውያን ስለድምፅ አሰጣጡ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ለሪፈረንደሙ ድምፃቸውን መስጠት የሚገባቸው ሲባልም ዕድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም ኤርትራውያን ነን ብለው የኤርትራ ዜግነትን በሚመለከት በታወጀው አዋጅ ቁጥር 21/1984 መሠረት ያሳወቁና በኤርትራ ደኅንነት ጉዳይ መምርያ ተመዝግበው መታወቂያ የያዙ መሆን ነበረባቸው፡፡ በመታወቂያው ላይም ሙሉ ስም፣ የተመዘገበበት ቁጥር፣ የተመዘገበበት ወረዳ፣ የመዝጋቢው ፊርማ ተሟልቶ መገኘት አለበት፡፡ በዚህም መሠረት ከ1.1 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የኤርትራን ዕድል በድምፅ ለመወሰን ተመዘገበ፡፡ ተመዝጋቢዎቹ በአገር ሲተነተኑም 60 ሺሕ ያህሉ በኢትዮጵያ፣ 156 ሺሕ ያህሉ በሱዳን፣ 84 ሺሕ ያህሉ በሌላው ዓለም በተለይም በዓረብ አገሮች፣ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኤርትራውያን ነበሩ፡፡

ይህ ቅድመ ሁኔታ ከተመቻቸ በኋላ የኤርትራ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ስለሪፈረንደሙ ሒደት ቅስቀሳ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ካርዱም ሁለት ምርጫዎች የሚሰጥ ሲሆን አንደኛው ካርድ ባለሰማያዊ ቀለሙ፣ ሁለተኛው ማለትም ባለቀይ ቀለሙ ነበሩ፡፡ ባለሰማያዊ ቀለሙ ‹‹ነፃነት›› የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ማለትም ቀዩ ደግሞ ‹‹አይደለም›› የሚል ነበር፡፡ የድምፅ መስጫ ካርዱ ‹‹ነፃነት›› እና ‹‹አይደለም›› የሚል ቢሆንም የኤርትራ ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ግን ‹‹ነፃነት›› ማለት ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት ሲሆን፣ ‹‹አይደለም›› ማለት ግን ‹‹ባርነትን መምረጥ›› ማለት ነው በማለት መቀስቀስ ጀመሩ፡፡ ጉዳዩ በነፃነት እንዲያልቅ ስለተፈለገም ይህንን የድምፅ አሰጣጥ የሚቃወም ዕድል አልተሰጠም፡፡

 የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1951 ዓ.ም. ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትዋሀድ የፈቀደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎችም የሚሰጡት አስተያየት አልነበረም፡፡ ይልቁንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የበላይ ተቆጣጣሪነት ሁለተኛው ሪፈረንደም ሚያዚያ 16 ቀን 1984 ዓ.ም. ተካሄደ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ታዛቢዎችም በየሄዱበት የምርጫ ጣቢያ በሳጥኖቹ ላይ ‹‹ነፃነት እፈልጋለሁ›› እና ‹‹ነፃነት አልፈልግም›› የሚሉ ተጽፎባቸው ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር መቆየት እንፈልጋለን፣ በፌዴሬሽን ወይም በኮንፌዴሬሽን እንተሳሰራለን… የሚል ምርጫ አልነበረም፡፡ በዚህም መሠረት ምርጫው ተካሂዶ በ99.80 በመቶ ድምፅ ኤርትራ በኢትዮጵያ በተጠቀሰው መንገድ መለያየቷን አረጋገጠች፡፡ ይህንንም የሪፈረንደም ድምፅ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታዛቢዎችም ምርጫው ነፃና ትክክለኛ፣ እንዲሁም አንዳችም እንከን ያልነበረው መሆኑን ሪፖርታቸውን ለዋና ጸሐፊው አቀረቡ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ተወካዮችም ምርጫው ትክክልና እንከን እንዳልነበረው ሪፖርታቸውን አቀረቡ፡፡

ለኤርትራ ነፃነት ዕውቅና መስጠትና የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን

ሚያዚያ 21 ቀን 1985 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥቱ አምስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ፣ ተደረገ፡፡ የኤርትራን ሪፈረንደም እንዲታዘብ የተላከው የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት የልዑካን ቡድን ሪፖርት ከደርግ መንግሥት በኋላ የሽግግር መንግሥቱን ያቋቋሙት የፖለቲካ ድርጅቶች ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ባደረጉት አገር አቀፍ ጉባዔ፣ ለሽግግር ዘመን መርሆ የሆነውን ቻርተር መክረውና ተቀብለው ማፅደቃቸውና ማወጃቸው ይታወሳል፡፡

በቻርተሩ አንቀጽ ሁለት ላይ የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መረጋገጡንና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ “ሐ” ላይ ደግሞ የሚመለከተው ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ከላይ የተጠቀሱት መብቶች ታገዱ፣ ተረገጡ፣ ወይም ተሸራረፉ ብሎ ባመነበት ጊዜ የራሱን ዕድል በራሱ እስከ ነፃነት ድረስ የመወሰን መብቱን ተግባራዊ የማድረግ መብት እንዳለው ተደንግጓል፡፡

የኤርትራን ጥያቄ በተመለከተም በዚሁ መንፈስ መፈታት እንዳለበት፣ ከሁለት ዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ባሉበት ሕዝበ ውሳኔ እንደሚደረግና የሕዝበ ወሳኔው ውጤት እንደሚከበር በተወሰነው መሠረት መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥትም የዚህን መሠረታዊ ጉዳይ አፈጻጸም በቅርበት የመከታተል ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ 13 አባላት ያሉበትን አንድ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከሚያዚያ 13 ቀን 1985 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኤርትራ ተልኳል፡፡ የልዑካን ቡድኑም መሠረታዊ ዓላማዎች ሕዝበ ውሳኔው ነፃ፣ ትክክለኛ፣ ያለ አድልኦና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት የተደረገ መሆኑን መታዘብና አስተያየቱን ለወከለው መንግሥት ማቅረብ ነበር፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጉባዔና ከኢትዮጵያ ካቶሊክ ጽሕፈት ቤት የተውጣጣ ነበር፡፡ በብሔራዊ ስብጥሩም የተለያየ መሆኑ ለታዛቢነት ተልዕኮአችን የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ለታዛቢ ቡድኑ የተደረገ አቀባበል

አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራ ጊዜያዊ መንግሥት ዋና ጸሐፊ ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) የማስታወቂያ ሚኒስትር ለሚመራውና የኤርትራን ሪፈረንደም ለመታዘብ ለተላከው የልዑካን ቡድን ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡ ከአቀባበሉ ሥነ ሥርዓት በኋላ የልዑካን ቡድኑ አስፈላጊ ፎርማሊቲዎችን ከማከናወኑ በፊት የምሳ ግብዣ የተደረገለት ሲሆን፣ ቀጥሎም ስለሪፈረንደሙ ታዛቢዎች መስተንግዶ በአስተናጋጆች ተገቢ መግለጫ ተደርጎለታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ የሥራ ቅድመ ዝግጅት

የኢትዮጵያ የታዛቢ ልዑካን ቡድን አስመራ ከደረሰ በኋላ በዕለቱ በነጋሶ (ዶ/ር) ሰብሳቢነት ወደፊት ስለሚያካሂዳቸው ሥራዎች ተነጋግሯል፡፡ በስብሰባው ነጋሶ (ዶ/ር) ለ30 ዓመታት የተካሄደው ጦርነት በሁሉም ወገን ያስከተለው ጥፋት በቀላሉ የማይረሳና ስለአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት የዳረገ መሆኑን አመልክተው፣ የኢትዮጵያ ገዥዎች በሕዝቦች ብሔራዊ ጥያቄ ላይ የተከተሉት መድልኦና ከፋፋይ ፖሊሲ አላስፈላጊ የእርስ በርስ መጠራጠርና ጠላትነትን ፈጥሮ መቆየቱንም አስታውሰው፣ ሪፈረንደሙ በቀድሞ ገዥዎች ተፈጥረው የነበሩትን መሠረታዊ ችግሮች እንዲፈታና የኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ፍላጎት እንዲገለጽ ይጠበቃል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ዋና ዓላማ ሕዝበ ውሳኔው ነፃ፣ ትክክለኛና አድልኦና ተፅዕኖ ያልተደረገበትና ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት የተፈጸመ መሆኑንና አለመሆኑን መከታተልና ማረጋገጥ እንደሆነና እያንዳንዱ አባል በብቃትና በንቃት ሁኔታውን ተከታትሎ ሪፖርት እንዲያቀርብ የተደረገ መሆኑን አውስተው፣ ለላካቸው መንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛውን የሪፈረንደሙን ገጽታ የሚያሳይ ሪፖርት የማቅረብ ኃላፊነት ለልዑካን ቡድኑ ተሰጥቶ እንደነበረ አበክረው ገልጸዋል፡፡

 ነጋሶ (ዶ/ር) በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በሪፈረንደሙ ላይ ያለው አቋም ምን እንደሚመስል ለሚያገኟቸው ሁሉ የመግለጽ ኃላፊነት ያልነበራቸው መሆኑንና የሪፈረንደሙ አጠቃላይ ሒደት ትክክለኛ መሆኑንና አለመሆኑን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በየፊናቸው መግለጫ መስጠት እንደሌለባቸው፣ የልዑካን ቡድኑ ሪፖርቱን ለወከለው መንግሥት ብቻ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት አምኖበት መንቀሳቀሱን አስገንዝበው የልዑካን ቡድኑ የራሱን ጸሐፊ መምረጥና በቡድኖች ተከፋፍሎ በተለያዩ አውራጃዎች እየዞረ መታዘብ ይጠበቅበት እንደነበረ አውስተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከልዑካኑ አባላትም የቀረቡ ሐሳቦች በሪፈረንደሙ ሒደት ውስጥ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮችና ዘዴዎችን የሚመለከት ነበር፡፡ በዚሁም መሠረት ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች የድምፅ አሰጣጡ ነፃ፣ ትክክለኛና ተፅዕኖ የሌለበትና በተለይም ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በተገኙበት የሚካሄድ መሆኑን ማረጋገጥና ለልዑካኑ አባላት በቂ ግንዛቤ ሊያስጨብጧቸው የሚችሉ ጥያቄዎችን ለድምፅ ሰጪዎች እያቀረቡ መወያየት የሚችሉ መሆኑን፣ በዚህም ላይ ምንም ገደብ መኖር እንደሌለበት አባላቱ ተወያይተው ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ቡድኖቹ ወደ ተመደቡበት ከመሰማራታቸው በፊት ሚያዚያ 14 ቀን 1985 ዓ.ም. በአስመራ ከተማ ለሪፈረንደሙ የተደረጉትን ቅድመ ዝግጅቶች እየተከታተሉ እንዲውሉ፣ ከሪፈረንደሙ ዕለት ከጠዋት 12 ሰዓት ጀምሮ ወደ ተመደቡባቸው አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ሚያዚያ 16 ቀን 1985 ዓ.ም ማታ አስመራ ገብተው እንዲያድሩና ስለሥራው ሪፖርት እንዲያደርጉ ሆኖ፣ ሁሉም ቡድኖች ከሚመለከታቸው ክልል ውጪም በተቻለ መጠን መሸፈን እንደሚኖርባቸው ውይይት ከተደረገ በኋላ ስብሰባው ተፈጽሟል፡፡

ከድምፅ መስጫው ቀን አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሚያዚያ 14 ቀን 1985 ዓ.ም ወደ ከረን የተመደበው ቡድንም ጉዞውን ጀመረ፡፡ ከልዑካን ቡድን አባላትም ውስጥ ዘግይተው ከነበሩት ውስጥ ሁለቱ በዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ አስመራ ገቡ፡፡ ዘግይተው ለመጡትም ማብራሪያና ምደባ ለማካሄድ የልዑካን ቡድን አባላቱ በኒያላ ሆቴል ሚያዚያ 14 ቀን 1985 ዓ.ም. ማታ ተሰብስበው አቶ ገላጋይ ትርፌንና ወ/ሪት መኪያ መሐመድን ከልዑካን ቡድኑ አባላት ጋር ለማስተዋወቅና በየትኛው አካባቢ እንደሚሰማሩ ለማስወሰን መሆኑን ሰብሳቢው ገልጸው፣ በጉዳዩ ላይ በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ ትራንስፖርት ከተገኘና ችግር ካላጋጠመ ወደ አሰብ እንደሚሄዱ ተገልጾላቸው፣ እስከዚያው አቶ ገላጋይ ትርፌ ከአስመራው ቡድን ጋር ወ/ሪት መኪያ መሐመድ ከአካለ ጉዛይና ሰራዬ ቡድን ጋር እንዲሠሩና ወደ ምፅዋ ለመሄድ የጠየቁት ወደ ምፅዋ እንዲሄዱ ተደርጎ፣ ዘግይተው ለመጡት አባላት እስካሁን ስለተደረጉ ውይይቶችና ስለሪፈረንደሙ አጭር ማብራሪያ ተደርጎ ስብሰባው ተፈጽሟል፡፡

ሚያዚያ 15 ቀን 1985 ዓ.ም. ጠዋት 12 ሰዓት ላይ አስመራ የነበሩት የተቀሩት ቡድኖች ወደምድብ ጣቢያዎቻቸው ተሰማርተዋል፡፡ የአሰብ ቡድን ተብሎ ታስቦ የነበረው በትራንስፖርት ዕጦት ምክንያት ቀርቶ አባላቱም በጊዜያዊነት ተመድበው በነበሩበት ቡድኖች ውስጥ እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡

የቡድኑ ግንዛቤና አስተያየት

በሪፈረንደሙ የሥራ አፈጻጸም ሒደት ውስጥ በድምፅ አሰጣጡ የሴቶች ተሳትፎ ንቁና ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ መሆኑን፣ ከነዋሪው ሕዝብ መካከል የተመረጡ ሥነ ሥርዓት አስከባሪዎችና መዝጋቢዎች መራጩን ሕዝብ በሥነ ሥርዓት ሲያስተናግዱ፣ እንዲሁም የተለያየ እምነት ተከታዮችና የኮሚሽኑ ተወካይ በታዛቢነት በየድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መገኘታቸውን፣ የድምፅ አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት ሥርዓትን የተከተለና መራጩ ሕዝብ ተራውን በትዕግሥት ጠብቆ ድምፅ ሲሰጥ መቆየቱን፣ በየምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ለመራጩ ከፀሐይ መጠለያ የሚያገለግሉ ድንኳኖችና መቀመጫዎች መዘጋጀታቸውን፣ ቡድኑ በአስመራ ከተማ በተጓዘባቸው የድምፅ ቆጠራ ጣቢያዎች ታዛቢዎች በተገኙባቸው ሳጥኖች ተከፍተው መቆጠሩንና ከተቆጠረም በኋላ መታሸጋቸውን ተመልክቷል፡፡ ቆጠራውም በተክክል መካሄዱን ማስተዋሉን ጠቅሶ በአጠቃላይ ቡድኑ በታዛቢነት በተገኘባቸው ሁሉ የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መገኘታቸውን፣ የድምፅ አሰጣጡም ሒደት የተከናወነው ያላንዳች ተፅዕኖና ከኋላው ምንም ዓይነት ድብቅ ወይም ሥውር አሠራር ሳይኖረው የተፈጸመ በመሆኑ ምርጫው ነፃ፣ ትክክለኛና አድልኦ የሌለበት መሆኑን ባቀረበው ሪፖርት ተገልጿል፡፡

ማጠቃለያና አስተያየት

በዚህ ሪፖርት ውስጥ እንደተካተተው የኢትዮጵያ ልዑካን ዓላማ ምን እንደሆነ ተገናኝቶ ሐሳብ በመለዋወጥ፣ ለሥራው አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማውጣት፣ የልዑካን አባላት ራሳቸውን በአራት ቡድኖች በመክፈል በከረንና አካባቢው፣ በምፅዋና አካባቢው፣ በአካለ ጉዛይና ሰራዬ አውራጃዎች፣ በአስመራ ከተማና በአካባቢዋ በሚገኙት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት ታዝበዋል፡፡ የታዘቡትንም በጽሑፍ ሪፖርት በማቅረብና የግል አስተያየታቸውንም በማከል ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት አድርገዋል፡፡ ቡድኖቹ ወደ ተለያዩ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር የኤርትራ ሪፈረንደም ኮሚሽንን ዝግጅት ተመልክተው ረክተውበታል፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ መከፈታቸውን፣ ድምፅ ሰጪውን የሚያስተናግዱ ሠራተኞች ተሟልተው መገኘታቸውን፣ ምዝገባው የምርጫ ካርዱ ዕደላ በሥርዓት መካሄዳቸውን፣ ከነዋሪው መካከል የተከሉ አረጋውያን ድምፅ የሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ተቀምጠው መታዘባቸውንና ሌሎችም ዝግጅቶች እጅግ የተሳኩ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

ሕዝበ ውሳኔው በሽግግሩ መንግሥቱ ተቀባይነት ስለማግኘቱ

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1985 ዓ.ም. ከቀኑ ከ8፡00 እስከ 12፡00 ሰዓት ባካሄደው አምስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ስለኤርትራ ሪፈረንደም ውጤት ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ በከፍተኛ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት የሪፈረንደሙ ውጤት ከፍተኛ ተቀብሎ ከማፅደቁ በፊት ከኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የተላከውን ማስታወሻ፣ ከማስታወሻውም ጋር ወደ ኤርትራ ተጉዞ የነበረው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ያቀረበውን ባለ 23 ገጽ ሪፖርት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ታዛቢ አካላት የሪፈረንደሙ ሒደት በትክክል በነፃና ተፅዕኖ በሌለበት ሁኔታ መከናወኑን የሚያረጋግጠውን የጽሑፍ ማስረጃ ተመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ ምክር ቤቱ የሕዝቡን ውሳኔ እንቀበለው ወይስ አንቀበለው የሚል ሐሳብ አንስቶ ሲወያይም በጉዳዩ ላይ ሦስት ዓበይት ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ ከእነዚህም የመጀመሪያው በአገው ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ድርጅት የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ተልዕኮውን ፈጽሞ በሌላ ቋሚ መንግሥት የሚተካ እንደ መሆኑ መጠን፣ ስለኤርትራ ነፃ መሆን ወይም አለመሆን ለመወሰን ስለማይችል ጉዳይ የሽግግሩን መንግሥት ለሚተካው መንግሥት በይደር ማቆየት እንደሚገባው ገልጿል፡፡ የጉራጌ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አንድ አባልም ምንም እንኳ ሪፈረንደሙ በአንድ አማራጭ ከማለቅ ይልቅ ሕዝቡ በፌዴሬሽን፣ በኮንፌዴረሽን ወይም በአንድነት መኖርን ይመርጥ እንደሆነ አማራጭ ሊቀርብለት ይገባ እንደነበር ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሦስተኛው ድርጅት የሪፈረንደሙ ውጤት በተመለከተ የቀረበውን ሪፖርት ተመልክቶ ከመወሰን ይልቅ፣ የሽግግሩ መንግሥት የሚመራበትን ቻርተርና አቋም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመርያ፣ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር ተጣቅሶ ለመጪው ትውልድ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲቀርብ ውሳኔው ለሌላ ጊዜ እንዲቆይ አቋሙን ገልጿል፡፡

በሪፈረንደሙ ውጤት የኤርትራ ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥር ነፃነትን በመደገፍ የወሰነውን ውሳኔ እናከብራለን የሚለውን ከሁለት ድምፅ ተዓቅቦ በስተቀር በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡ በአጠቃላይም በኤርትራ የተካሄደውን ሪፈረንደም ነፃና ዴሞክራሲያዊ ነበር በማለት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ያስቀመጡትን ትዝብትና ግምገማ ተቀብለናል፡፡ በዚሁ በሪፈረንደም ውጤት መሠረት የኤርትራ ሕዝብ የወሰነውን ውሳኔ እንደምናከብርም አረጋግጠናል፡፡ ከዚህ በመነሳት የሚመለከታቸው አካላት በየደረጃው መወሰድ ያለባቸውን ውሳኔዎች ሊወስዱ ይችላሉ፡፡

(ክፍል ሦስት ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...