የአፍሪካ ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ማዕከል (Africa Center for Strategic Studies) ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሰፊ ዘገባ፣ አፍሪካ ውስጥ ፅኑ የምግብ እጥረት ካጋጠማቸው አሥር አገሮች አራቱ የሚገኙት በምሥራቅ አፍሪካ መሆኑንና እነሱም ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ መሆናቸው ገልጿል፡፡
መፍትሔ ያልተገኘላቸው ግጭቶች አሁንም ለምግብ እጥረት ዋነኛ ገፊ ምክንያት መሆናቸውን አስታውቆ፣ ለፅኑ የምግብ እጥረት ከተጋለጡ 149 ሚሊዮን አፍሪካውያን ውስጥ 82 በመቶ የሚሆኑት ግጭት ውስጥ ባሉ አገሮች እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡ በአፍሪካ 38 አገሮች በተወሰነ ደረጃ ፅኑ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ነገር ግን ሁለት-ሦስተኛ ያህሉ ፅኑ ችግር በአምስት ግጭት ውስጥ ባሉ አገሮች ማለትም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በናይጄሪያ፣ በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን መከማቸቱን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ 20.1 ሚሊዮን ወገኖች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን፣ 15.1 ሚሊዮን ያህሉ ደግሞ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በማዕከሉ ዘገባ ተካቷል፡፡