Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኢትዮጵያውያን የኮሪያ ፖፕ ተወዛዋዦች

ኢትዮጵያውያን የኮሪያ ፖፕ ተወዛዋዦች

ቀን:

በዳንኤል ንጉሤ

የደቡብ ኮርያ ኤምባሲ በጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ምርጥ የኬ-ፖፕ (የኮሪያ ፖፕ) ሥልት ችሎታ ያላቸውን ወጣት ኢትዮጵያውያን ዕውቅና ለመስጠትና ለመሸለም ያለመ ዝግጅት በራዲሰን ብሉ አዘጋጅቶ ነበር።

የዚህ ዝግጅት ዓላማ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ኬ-ፖፕ እየተባለ የሚጠራውን የኮሪያ ፖፕ ሥልት የሚጫወቱ  የኢትዮጵያ ተወዛዋዦችና የሙዚቃ ኮከቦችን ማክበርና መሸለም ነበር።

በየዓመቱ የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ የኬ ፖፕ ሥልትን ለሚጫወቱ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መድረክ ያዘጋጃል። የውድድሩ አሸናፊዎችም በአፍሪካ መድረክ የመወዳደር ዕድሉን ያገኛሉ፡፡ በቀጣይም  ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ በመግባት ተወዳድረው አሸናፊ ከሆኑ  በደቡብ ኮሪያ ኬ-ፖፕ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመገናኘት አብረው የመሥራት ዕድል ይፈጠርላቸዋል።

በዝግጅቱ ጎልተው ከታዩ ትርዒቶች ውስጥ የኬ-ፖፕ የውዝዋዜ ሥልትን ካቀረቡት ወጣቶች መካከል ሁለት ተወዛዋዦች የሚገኙበት ‹‹አዶት›› የዳንስ ቡድን አንዱ ሲሆን፣ በውድድሩ ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል።

የ‹‹አዶት ዳንስ›› ቡድን አባላት የሆኑት እሱባለው ጋሻውና ሡራፌል ዘውገ ባደረጉት ማራኪ እንቅስቃሴና ቅንጅት ታዳሚውን አስደምመዋል።

የ21 ዓመቱ ወጣት እሱባለው ሙሉ ጊዜውን በውዝዋዜ ሥራ ለመቀጠል ሲል በሮያል ኮሌጅ ሲከታተል የነበረውን የኮሌጅ ትምህርቱ እንዲዘገይ አድርጓል።

‹‹የዳንስ ፍቅሬ  ያደገው ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ ነበር፡፡ አብሮኝ የሚደንሰው ሡራፌል ከደብረ ብርሃን አዲስ አበባ ከእህቱ ጋር ለመኖር በመምጣቱ  ተዋወቅን፡፡ ሡራፌልም በደብረ ብርሃን ባህላዊ ውዝዋዜ ጀምሮ ነበርና ከእኔ ጋር ለመደነስ ፍላጎቱን ሲገልጽ በደስታ ተቀበልኩት፤›› በማለት እሱባለው ያስረዳል።

የ21 ዓመቱ ሡራፌል ዘውገም የእሱባለውን ሐሳብ ይጋራል። ‹‹ከአስደናቂው የኬ ፖፕ ሙዚቃና ቪዲዮዎች ጋር ያስተዋወቀን የኬ ፖፕ አድናቂ ጓደኛችን ካሌብ በኃይሉ ነው፤›› ሲል ሡራፌል ያስረዳል። ‹‹ቤተል በሚገኘው ወጣት ማዕከል ውስጥ ሥልጠና እንድንጀምር ገፋፍቶን ለሥልቱ ፍቅር እንዲኖረን አደረገን፤›› በማለትም ያስታውሳል።

ጉዟቸው የጀመረው በቤቴል የወጣቶች ማዕከል ሲሆን፣ ከውዝዋዜ ቡድኖች ጋር ተቀላቅለው ለስድስት ዓመታት ችሎታቸውን አጎልብተዋል።  ዛሬ ተወዛዋዥ ብቻ ሳይሆኑ፣  አሠልጣኝም ሆነው ዕውቀታቸውን  ለታዳጊ ተወዛዋዦች በልግስና በማካፈል ላይ ናቸው።  አዶት ወደ ኬ-ፖፕ ውዝዋዜ ከመግባቱ በፊት በዋነኛነት ያተኮረው በሂፕ-ሆፕ ጭፈራ ላይ ነበር።

ደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ በሚያዘጋጀው የኬ ፖፕ ውድድር የመሳተፍ ዕድሉን ያገኙት በጓደኛቸው  በኩል ሲሆን፣  ስለውድድሩ በተነገራቸው ሰዓት ሳያቅማሙ ዕድሉን ተጠቅመው በኤምባሲው ሊመዘገቡ ችለዋል።

በ2014 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ተወዳድረው ችሎታቸውን በማሳየት  የሦስተኛ ደረጃን ቦታ በማግኘታቸው፣  በሒልተን አዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ ኮሪያ ወዳጅነት 60ኛ ዓመት  በዓል በሕዝብ ፊት ውዝዋዜውን የማሳየት ዕድል አግኝተዋል።

በሒልተኑም ዝግጅት ባሳዩት አስደናቂ ትርዒት ከኢትዮ-ኮሪያ ዘማች ማኅበር ለዘማች ቤተሰቦች ልጆች የዳንስ ትምህርት እንዲሰጥ ለአዶት ግብዣ ቀርቦለታል።

እሱባለው ልዩ ተሞክሮውን በማስታወስ ‹‹ያሳየነው የዳንስ ብቃት ዕድል ፈጥሮልናል፡፡ ዳንሱንም ለዘማች ቤተሰቦች ልጆች እንድናስተምር በአክብሮት ተጋብዘናል፡፡  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየእሑዱ እናስተምራለን፤›› ብሏል፡፡

የእሱባለውና ሡራፌል ቤተሰቦች በትምህርት ልቀው እንዲገኙ ቢፈልጉም፣ እነሱ ለውዝዋዜ ያላቸውን ፍቅር አጥብቀው በመያዝ፣ ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቀዋል፡፡ ምንም እንኳን አንደኛ ባለመውጣታቸው በቀጣይ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የውድድር ዕድሎች ባይሳተፉም፣ ህልማቸውን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሠሩ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እሱባለው ‹‹በድል አድራጊነት እስከምንወጣና አገራችንን በዓለም አቀፍ መድረክ በኩራት እስክንወከል ድረስ እንታገላለን፤›› በማለት ተናግሯል። የኬ-ፖፕ ባህልን ለማሳደግና በመላው ኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ያለመ ‹‹ድሪመርስ›› የሚባል የኬ-ፖፕ  ትምህርት ቤት ለመመሥረት ዕቅድ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የውጭ አገር የውዝዋዜ ሥልቶችና ትምህርት ቤቶች ተወዳጅነትን እያተረፉ ቢሆንም፣ አገር በቀል የውዝዋዜ ወጎችን መጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ይከራከራሉ።

የፈንዲቃ ባህል ማዕከል ባለቤትና የኢትዮጵያ የባህል ተወዛዋዥ መላኩ በላይ፣ ‹‹በአሁኑ ጊዜ እነዚህን ዓይነት ትምህርት ቤቶች መክፈት ቅድሚያ ሊሰጠው አይገባም፤›› ብሎ ያምናል። ‹‹የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ የብሔራዊ ማንነታችን ዋነኛ አካል ነው፤›› ሲልም ያክላል።

የኢትዮጵያን የባህል ውዝዋዜ ዕድገት ልናከብረውና ልንንከባከበው ይገባል የሚለው አቶ መላኩ፣ የሌሎች አገሮችን ውዝዋዜ ዘይቤ በመከተል ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ የራስን ባህላዊ ቅርስ ለማክበርና ለማስተዋወቅ አዳዲስ መንገዶችን መመርመር እንደሚያስፈልግ፣  ይህን ማድረግም መጪው ትውልድ የኢትዮጵያን ውዝዋዜና ውበታዊ ፋይዳ ተቀብሎ እንዲያደንቅ እንደሚያግዝ ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...