እቴ…
ይስጥሽ ከቁመቴ ከላዬ ቀንሶ
ያስረዝምሽ አንቺን እኔን አሳንሶ
ከሰጎን እረዝመሽ ስትቆሚ ከጎኔ
ቁመቴን መጽውቼሽ ጫጩት ላክል እኔ፤
ይስጥሽ ከጸጉሬ ከአናቴ ላይ ዘግኖ
ይገጠብ ራሴ ያንቺ ተጎንጉኖ
አወይ ጸጉሯ ብለው ኮረዶች ሲያወሩ
ድጥ ራስ ነህ ብሎ ይዝለፈኝ ሰፈሩ፤
እቴ…
ይስጥሽ ከወዜ ላይ ጨልፎ ከፊቴ
ይቅዳልሽ ከደሜ ጠልቆ ከጅማቴ
ከአይን ያውጣሽ እያለ ሲመርቅ አድናቂ
እስቲ እግዜር ይማርህ ይበለኝ ጠያቂ።
እቴ…
እጄን ብትፈልጊ
እግሬን ብትፈልጊ
አንገቴን ደረቴን
ተሰጥኦ ሐሳቤን
ያደምቀኛል ብለሽ ያሰብሽውን ሁላ
እግዜር ከኔ ወስዶ ከሰጠሽ በኋላ
ያስቀርልኝ አይኔን
አንቺን ማየት ብቻ ያኖረኛል እኔን።
(በዕውቀቱ ስዩም)