በፈረንሣይ ፓሪስ የሚከናወነው የኦሎምፒክ ጨዋታ ለመካፈል የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የናይጄሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ይገጥማሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2024 በፈረንሣይ ፓሪስ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ የሴቶች ማጣሪያ ጨዋታ ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል፡፡ በመጀመርያ ማጣሪያ ጨዋታ ቻድን ገጥመው፣ በድምር ውጤት 10 ለ 0 መርታት የቻሉት ሉሲዎቹ፣ በሁለተኛ ዙር ጨዋታ ከናይጄሪያ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡
በሁለተኛ ዙር የጨዋታ መርሐ ግብር ከናይጄሪያ ጋር የተመደቡት ሉሲዎቹ፣ ልምምዳቸውን መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው 35 ሜዳ ሲያከናውኑ ከርመዋል፡፡
በዚህም መሠረት የሁለተኛ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን በአበበ ቢቂላ የሚያደርጉት ሉሲዎቹ፣ ሁለተኛውን የምድባቸው የማጣሪያ ጨዋታ ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በናይጄሪያ ያከናውናሉ፡፡
በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ ጨዋታ 16 አገሮች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ስምንት ቡድኖች ብቻ ወደ ቀጣዩ ወይም ወደ ሦስተኛ ዙር ይገባሉ፡፡
የሦስተኛው ዙር የደርሶ መልስ ጨዋታን ማሸነፍ የቻሉ አራት ብሔራዊ ቡድኖች በ2024 ኦሊምፒክ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
በኦሊምፒክ የሴቶች እግር ኳስ ጨዋታ ሦስት ጊዜ ማለፍ የቻሉት የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹን ይፈትናሉ የሚል ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በኦሊምፒክ ተሳትፎ አድርገው የማያውቁት ሉሲዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጉትን ጨዋታ ውጤት አስጠብቀው እንደሚወጡ ይገመታል፡፡
እ.ኤ.አ. 1996 ከአትላንታ ኦሊምፒክ ጀምሮ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ መከናወን የጀመረ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ካሜሮን፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዛምቢያና ዚምባብዌ በተከታታይ መሳተፍ ችለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን መሳተፍ ከጀመረበት ጊዜ አንሰቶ አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር፣ አንድ ነሐስ በድምሩ ሦስት ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡
ካሜሮን አንድ የወርቅና አንድ የነሐስ በድምሩ ሁለት ሜሊያዎች በመሰብሰብ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ መቀመጥ የቻለች አገር ናት፡፡ ጋና በአንድ ነሐስ ሜዳሊያ ሦስተኛዋ አፍካዊት አገር ሆናለች፡፡