Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሁሉ ስፖርት ጋር ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረመ

ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሁሉ ስፖርት ጋር ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ተፈራረመ

ቀን:

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ከሁሉ ስፖርት ኦንላይን ሶሉዩሽን ጋር መፈራረሙን አስታወቀ፡፡

ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሁለቱ ተቋማት፣ ለሁለት ዓመት የሚያቆያቸውን የ11 ሚሊዮን ብር የአጋርነት ስምምነት ይፋ አድርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት ሁሉ ስፖርት ከዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጀምሮ የመጫወቻ ኳስ ስያሜን የሚወስድ ሲሆን፣ የውድድር ዓመቱን ሙሉ የመጫወቻ ኳስ ያቀርባል ተብሏል፡፡ ከዚህም በሻገር ተቋሙ የአክሲዮን ማኅበሩን የተለያዩ ዩኒፎርሞች የሚያቀርብ ሲሆን፣ የተለያዩ መርሐ ግብሮችን በጋራ ሆኖ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት ዓመት በሚቆየው የውል ስምምነት ስድስት ሚሊዮን ብር ለውድድር ቁሳቁስ ወጪ የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው አምስት ሚሊዮን ብር የስምምነት ክፍያ ይውላል ተብሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁሉ ስፖርት ሶሉዩሽን የውድድር ዓመቱን 240 ጨዋታ የመጫወቻ ኳስ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡

በስምምነቱ መሠረት በወድድሩ ወቅት ኳስ ከማቅረብ ባሻገር የሕክምና ባለሙያ ትጥቅ፣ የፎቶግራፈር ትጥቅ፣ እንዲሁም ለኳስ አቀባዮች ትጥቅና ቁሳቁስ ይቀርባል፡፡

ድርጅቱ የፊፋን ደረጃን ያሟላና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥራቱ የተረጋገጠ የመጫወቻ ኳስ እንደሚያቀርብ፣ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፋ አብራርተዋል፡፡፡

ከዚህም ባሻገር ሁሉ ስፖርት ኦንላይን ሶሉዩሽን የቴክኖሎጂ ድጋፍ የማድረግ ዕቅድ እንዳለው፣ የሁሉ ስፖርት ሁለገብ ሶሉዩሽን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይትባረክ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከመልቲቾይስ አፍሪካ ጋር የሊጉ ጨዋታ ቀጥታ ሥርጭት እንዲኖረው ውል ያሰረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ስያሜን ለቤትኪንግ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ሆኖም በአፍሪካ እንዲሁም በተለያዩ አገሮች በስፖርት ውርርድ የሚታወቀው ‹‹ቤትኪንግ›› ውሉን አቋርጦ ከአጋር መውጣቱ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዘም ሁሉ ስፖርት፣ በስፖርት ውርርድ ንግድ ውስጥ ያለ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ ቀደሞ ውሉን በጊዜ ያቋረጠው ተቋም እያለ ከሊግ ካምፓኒው ጋር ውል ማሰሩ አዋጭ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ተነስቶ ነበር፡፡  

ሆኖም ቤትኪንግ በአክሲዮን ማኅበሩ ተቀባይነት ኖሮት ሲሠራ ቢቆይም፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ደኅንነትን በጠበቀ ሁኔታ ባለመሥራቱ፣ ውሉን አቋርጦ መውጣቱን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ሁሉ ስፖርት በውርርድ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚሠራ ተቋም በመሆኑና ፕሪሚየር ሊጉን የሚከታተሉ ታዳጊዎች ላይ የሚኖረው ጉዳት ከግምት ውስጥ መግባቱ ተነስቷል፡፡

እንደ አክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ከሆነ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ከተመሳሳይ ድርጅቶች ጋር ከመዋዋሉ አስቀድሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳውን በተመለከተ፣ ከብሔራዊ ሎቶሪ ጋር ከተወያየ በኋላ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ አቶ ክፍሌ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ አዲስ ስያሜ ይዞ እንደሚከናወን የተጠቆመ ሲሆን፣ በአገሪቱ ከሚገኝ ትልቅ የፋይናንስ ተቋም ጋር የስያሜ ስምምነት እንደሚያደርግ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

ይህም ተቋም በቀጣይ ከሊጉ ጋር በሚያደርገው ስምምነት መሠረት መጠሪያው ሆኖ  እስከ ስምምነቱ ማብቂያ ዕለት ድረስ አብሮ ይዘልቃል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየተከናወነ የሚገኘው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የቀጥታ ሥርጭት ተቋርጧል፡፡

የሥርጭቱ መቋረጥ ጋር በተያያዘ አክሲዮን ማኅበሩ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሱፐር ስፖርት ጋር ሆኖ የፕሮዳክሽን ሥራ ሲሠራ የቆየው ‹‹ላይቭ አይ›› የተሰኘ መቀመጫውን ኬንያ ካደረገ ተቋም ጋር ውል በማቋረጡ ምክንያት ሥርጭቱ ሊቆም መቻሉ ተገልጿል፡፡

የውድድሩን የመጀመርያ ሳምንቶች ከአገር በቀል ተቋማት ጋር በመመካከር የቀጥታ ሽፋኑን ለማስቀጠል ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ የአገር በቀል ተቋማቱ ቀጥታ የማስተላለፊያ መሣሪያ የጥራት ጉድለት መኖሩና ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቃቸውን ተከትሎ ሊቋረጥ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዘም ሱፐር ስፖርት ሙሉ በሙሉ አዲስ የፕሮዳክሽን ቡድንና መሣሪያ በማሟላት በቀጣይነት ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ የሊጉን ቀጣይ ሥርጭት ዳግም እንደሚጀምር ተጠቁሟል፡፡

ይህም ዘንድሮ ከሚከናወኑት 240 ጨዋታዎች፣ 180ዎቹ በሱፐር ስፖርት በቀጥታ እንደሚተላለፉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...