የቻይና መንግሥት የኢትዮጵያን ሙሉ የቆዳ ስፋት የሚሸፍን የሳተላይት መረጃ በነፃ ለማቅረብ ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን 80 በመቶ የቆዳ ስፋት የሚሸፍን የሳተላይት መረጃ ማቅረቧን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ሥራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባቀረበበት ወቅት እንደገለጸው፣ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ወዲህ በተፈጠረው ትብብር አማካይነት የኢትዮጵያን ሙሉ የቆዳ ስፋት የሚሸፍን የሳተላይት መረጃ በየዓመቱ በነፃ ለማቅረብ ስምምነት ተደርሷል። በዚሁ መሠረትም በበጀቱ ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት የኢትዮጵያን 80 በመቶ የቆዳ ስፋት የሚሸፍን ሁለት ሜትር ‹‹ሪዞሊውሽን›› (የምስል ጥራት) ያለው የሳተላይት መረጃ በነፃ መገኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የኢትዮጵያን ሙሉ የቆዳ ስፋት የሚሸፍን የሳተላይት መረጃ በየዓመቱ ለማግኘት ከቻይና መንግሥት ጋር በተገባው ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ መረጃውን ሌላ ወገን መሸጥ አትችልም ያለው ሚኒስቴሩ፣ በዚህም ስምምነት የሚገኘው የሳተላይት መረጃ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የገበያ ዋጋ 2.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር በመተባበር ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ጠፈር የላከቻቸው ሁለት የመረጃ ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው መረጃ አሰባስበው መላክ ማቆማቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በመሆኑም እነዚህን ሳተላይቶቹን ለማስወገድ ዝግጅት መጀመሩን የገለጸው ሚኒስቴሩ፣ ሳተላይቶቹን የማስወገድ ሥራ በህዋ ላይ የሚገኙ ሌሎች ሳተላይቶችን በማያውክና ጉዳት በማያስከትል መንገድ ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር እንደሚፈጸም አስረድቷል።
በተጨማሪም አዲስ የመሬት ምልከታ ሳተላይት ለማልማትና ለማምጠቅ በ2015 ዓ.ም. ጨረታ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በቂ ተጫራች ባለመገኘቱ መሰረዙን የጠቆመው ሚኒስቴሩ፣ በቀጣዮቹ ወራት ጨረታውን በድጋሚ ለማውጣት ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።