Saturday, July 20, 2024

የአገር ህልውና የቆመባቸው ምሰሶዎች ልዩ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ!

የአንድ አገር መሠረታዊ የህልውና ምሰሶዎች ተብለው የሚታወቁት የሕዝቡ አንድነት፣ የጋራ ታሪኮች፣ ሰላምና ፀጥታ፣ የሕግ የበላይነት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮችና የመሳሰሉት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ ምሰሶዎች ላይ የሚታነፅ አገረ መንግሥት በምርጫ በሚለዋወጡ የመንግሥት አስተዳደሮች እየተጠናከረ፣ ህልውናውን አስጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመተላለፍ በቁሳዊም ሆነ በሰብዓዊ ሀብት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ በኢትዮጵያ ከእነ ችግሩም ቢሆን አገር የቆመችባቸው ምሰሶዎች አሉ፡፡ ምሰሶዎቹ የአገርን ህልውና ተሸክመው የሚጓዙበት ርቀት ለጊዜው የማይታወቅ ቢሆንም፣ አሁን ከሚስተዋለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ እነዚህን ፈተናዎች በጋራ በማስወገድ የአገርን ህልውና ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ታሪካዊ አደራ ነው፡፡ ይህንን አደራ በትጋትና በኃላፊነት ስሜት ለመወጣት ግን ለዓመታት የተበላሹ ግንኙነቶችን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታዊ አስተዳደሮች በተቀያየሩ ቁጥር የአኩራፊዎችና የብሶተኞች መበራከት፣ ለአገረ መንግሥት ግንባታው መሰናክል ከመፍጠሩም በላይ ለሕዝቡም ሆነ ለአገር ሰላምና ደኅንነት አደጋ እየደቀነ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት በስፋት ማብራሪያ እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ በሚገባ የመጠቀምም ሆነ በቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ተሳታፊ የመሆኗ ጉዳይ ከህልውናዋ ጋርም እየተቆራኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ ዕምቅ ሀብት ያላት አገር በቅርብ ርቀት ላይ ሆና ከባህር በር ባለቤትነት ተገልላ መኖር ስለሌለባት፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመደራደር የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አፅንኦት ተሰጥቶበት የሐሳብ ልውውጥ እየተደረገበት ነው፡፡ የሐሳብ ልውውጡ የተለያዩ አመለካከቶችን ይዞ የሚንሸራሸር መሆኑ ይበል መባል አለበት፡፡ መንግሥትም ቢሆን ይዞ የተነሳውን ዓላማ የሚሞግቱ በአመክንዮ ላይ የተመሠረቱ አመለካከቶችን በንቃት ቢያዳምጥ ይጠቀማል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እየሰጡ ያሉ ወገኖችም ከስሜታዊነትና ከአጉል ጉንጭ አልፋ ክርክሮች በመራቅ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ቢያስደምጡ ለአገር እንደሚጠቅሙ ይገንዘቡ፡፡ በድጋፍና በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉ ወገኖችም ሙግታቸው ከጊዜያዊና ከአላፊ ንትርክ ተላቆ፣ ለአገር ህልውና ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኩር፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ የምትታወቀው ወረራ ሲፈጸምባት እንጂ የሰው አገር ስትወር አይደለም፡፡ በየትኛውም ሥርዓተ መንግሥት ጊዜ ኢትዮጵያ ከወራሪዎች፣ ከተስፋፊዎችና ከቅኝ ገዥዎች ጋር ስትፋለም የኖረች አገር ናት፡፡ የሌላ አገር ዳር ድንበር ተዳፍራ የማታውቅ፣ በቅኝ ገዥዎች ጭቆና ሲማቅቁ ለኖሩ አፍሪካውያን ዋስ ጠበቃ የነበረች፣ ቅኝ ገዥዎችን ዓድዋ ላይ በከባድ ተጋድሎ ድል ነስታ ያሳፈረችና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ጭምር የኩራት ምንጭ የነበረች አገር ናት፡፡ ለእነዚህ ታላላቅ ክብሮች ያበቋት ጀግኖች ልጆቿ ከባድ የሚባሉ መስዋዕትነቶችን ሲከፍሉ የኖሩት፣ ልዩነቶቻቸውን በክብር ይዘው አንድነታቸውን በማጠናከራቸው ነው፡፡ ለእነሱ ከየትኛውም ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም በላይ በፍቅር የሚሞቱላት አገራቸው ትቀድም ነበር፡፡ በዓድዋም ሆነ በሌሎች ታላላቅ ዓውደ ግንባሮች በተደጋጋሚ የታየውም የአገር ፍቅርና ክብር ነበር፡፡ የዛሬው ትውልድ ከእዚህና መሰል አኩሪ የታሪክ ሰበዞች ትምህርት በመቅሰም፣ የእናት አገሩን ህልውና ለማስቀጠል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ማመንታት የለበትም፡፡ የአገር ህልውና ምሰሶዎች የሚጠነክሩትም በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ቅርብ ርቀት ላይ ሆና ወደብ አልባ ሆና መቆየቷ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ሲያስቆጭ የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ ከኤርትራ ነፃ መውጣት ማግሥት ወደብ አልባ ለምን ተደረገች ተብሎም፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞና ቁጣ ሲስተጋባ ይታወሳል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሰሚነት የነበራቸው የኢሕአዴግ ተቃዋሚ የነበሩ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች፣ በግል ሚዲያዎች ከመጠን በላይ በርካታ ሐሳቦች ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ በምርጫ 97 ክርክር ወቅት የኢሕአዴግ ዋነኛ ተቀናቃኝ የነበረው ቅንጅት አመራሮች፣ ኢሕአዴግን በቀጥታ ክርክር ከሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲወጣ ካደረጉባቸው አጀንዳዎች መካከል አንዱ የባህር በር ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የባህር በር ጉዳይ ድንገቴ ሆኖ ሲከሰት በጉዳዩ ላይ ከበቂ በላይ ዕውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን አሁንም በብዛት ስላሉ፣ በከፍተኛ ተሳትፎ ጠንካራ ንግግሮችና ክርክሮች እንዲካሄዱ ወደ አደባባይ መውጣት አለባቸው፡፡ የአገር ጉዳይ ለመንግሥት ወይም ለገዥው ፓርቲ ሰዎች ብቻ የሚተው ስላልሆነ፣ ውይይቱና ክርክሩ ደርቶ ጠቃሚ ነገሮች እንዲገኙ የበኩልን ድርሻ መወጣት ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ልምድ ውስጥ ከሚስተዋሉ ብልሹ ነገሮች መካከል አንደኛው፣ ሥልጣን የያዘው አካል ብቻ የሁሉም ነገሮች መነሻና መድረሻ መሆኑ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ላለመገንባቱ ትልቁ ምክንያት እንዲህ ያለው አጉል ባህሪ መንሰራፋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ ተጠብቆ አስተማማኝ ዕድገት ልታስመዘግብ የምትችለው፣ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ማንኛውም ፓርቲ ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ሲያከናውን ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ጥቂቶች እንዳሻቸው የሚፏልሉበት ሥርዓት ለውይይትም ሆነ ለድርድር በሩ ዝግ ስለሚሆን፣ እንኳንስ በአካባቢው ልዕለ ኃያል ሊያደርግ ስለሚችል አጀንዳ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም የጋራ አቋም አይኖርም፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ በባህር በር ጉዳይ ላይ በሚኖሩ የሚዲያም ሆነ የመድረክ ውይይቶች፣ ሐሳብ አለን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም ዓይነት አስተያየት ለማስተናገድ ልቡንም በሩንም መክፈት አለበት፡፡ ከአንድ አካባቢ የሚንቆረቆር ሐሳብ እንዳለ ተቀበሉ ከማለት ይልቅ፣ የተለያዩ አስተያየቶች እንዲደመጡ ዕድል መስጠት ለጎረቤት አገሮች ጭምር ዕፎይታ ይሰጣል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ካሉ አገሮች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የያዘች አገር ስትሆን፣ በአፍሪካም ከናይጄሪያ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን የሚገመተው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልማትም ሆነ ማደግ የሚችለው፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ጤናማ የሆነ የሰጥቶ መቀበል ግንኙነት ሲኖረው ነው፡፡ አንዳንድ አንደበታቸው ያልተገራ ግለሰቦች እንደሚሉት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ብላ የማንንም አገር ለመውረር ዕቅድ እንደሌላት በግልጽ መነገር ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ፍላጎቱ ወረራና ንጥቂያ እንዳልሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ሚዲያዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚነገሩ አሻሚ ቃላትና ሐረጎችም ጥንቃቄ ይደረግባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አስተማማኝ ሆኖ የሚቀጥለው ከጎረቤት አገሮች ጋር በመስማማት፣ የውስጥ አለመረጋጋትና ነውጥን በንግግርና በድርድር በመቋጨት፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስከበር፣ በዜጎች መካከል ለአድልዎና ለልዩነት በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ፣ የታሪክ ዝንፈቶችን በማስተካከልና ለሕግ የበላይነት ትልቅ ሥፍራ በመስጠት ነው፡፡ በእነዚህ የአገር ህልውና ምሰሶዎች ትኩረት እንዲሰጥ ልዩ ጥንቃቄ ይደረግ!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...