Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአክሲዮን ማኅበራት አደራጆች የሚሰበስቡት የማደራጃ ወጪ ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ ሊደረግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአክሲዮን ማኅበራትን የሚያደራጁ ግለሰቦች (Promoters) አክሲዮኖችን ከሚገዙ ሰዎች የሚሰበስቡት የማደራጃ ወጪ፣ ከሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከአራት በመቶ መብለጥ እንደሌለበት ሊደነገግ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ውይይት ክፍት የተደረገው የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጮች የሚተዳደሩበት ረቂቅ መመርያ፣ ባለአክሲዮኖች ከአንድ ኩባንያ አክሲዮን ሲገዙ አብረው የሚከፍሉት የማደራጃ ወጪን አራት በመቶ ጣሪያ በማድረግ ደንግጓል፡፡

በረቂቅ መመርያው መሠረት አደራጆች በአክሲዮን ሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ወደ አደራ ሒሳብ (Escrow Account) ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚሰበስቡትን አራት በመቶ የማደራጃ ወጪም ኩባንያውን ለማቋቋም ለሚውሉ ወጪዎች ብቻ መጠቀም እንዳለባቸውም መመርያው ያዛል፡፡

የአክሲዮን ማኅበራት አደረጃጀት እ.ኤ.አ. በ2021 በወጣው የንግድ ሕግ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፣ የንግድ ሕጉም ለአደራጆች ጥቅም በሚል ከሦስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ የሚከፈል ከትርፉ ከ20 በመቶ የማያልፈውን መውሰድ እንደሚችሉ ይፈቅዳል፡፡

ባንኮችን ጨምሮ አክሲዮን ማኅበራት ሲደራጁ በተለምዶ አሠራር ከአምስት እስከ አሥር በመቶ ክፍያዎችን በአክሲዮን ግዥዎች ላይ በመጨመር ለማደራጃ ወጪ ይወሰድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ረቂቅ መመርያ ይህንን ወጪ አሳንሶ፣ አደራጆቹ ለአማካሪዎቻቸው ወጪያቸውንና ሒሳባቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

በሥራ ላይ ያሉም ሆነ አዳዲስ አክሲዮን ማኅበራት አክሲዮኖችን ከመሸጣቸው በፊትና ድርጅቶች ለሕዝብ የብድር ሰነዶችን ከመሸጣቸው በፊት በባለሥልጣኑ መመዝገብ ያለባቸው ሲሆን፣ ባለሥልጣኑም የሰነድ ሙዓለ ንዋዮች ሽያጭ የሚተዳደርበትን መመርያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት እየሠራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች በመመርያው ላይ የሕዝብ ውይይት ያስጀመሩ ሲሆን፣ ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተወሰኑ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋርም ውይይት አካሂደዋል፡፡ የሕዝብ ውይይቱን ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ካደረጉና በፍትሕ ሚኒስቴር መመርያው ቁጥር ከተሰጠው በኋላ፣ በሁለት ወራት ገደማ ውስጥ ሥራ ላይ እንደሚውል አስረድተዋል፡፡

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን ለሽያጭ የሚያቀርብ አካል ባለሥልጣኑ በሚያዘጋጀው ቅፅ አማካይነት፣ የተመረመረ የምዝገባ መግለጫና በኦዲት የተረጋገጠ የሒሳብ መዝገብን ጨምሮ ሌሎችም ሰነዶችን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

ኩባንያዎች ደንበኛ ሳቢ መግለጫ (Prospectus)፣ ማለትም ለሽያጭ ስለሚያቀርቧቸው አክሲዮኖችና የዕዳ ሰነዶች ዝርዝር ዓላማና ባህሪ የያዘ ሰነድ ለባለሥልጣኑ በማቅረብ ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡ ሙዓለ ንዋዮችን የሚገዙ ባለሀብቶችም ግዥውን ከማከናወናቸው በፊት ስለኩባንያውና ለሽያጭ ስለቀረበው ሙዓለ ንዋይ ጠቅላላ መረጃ ከሰነዱ በመመልከት ሊወስኑ እንደሚገባ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ለሽያጭ ከሚያቀርባቸው የብድር ሰነዶች፣ ለሃምሳ ያህል ሰዎች ከሚሸጡ አክሲዮኖች፣ እንዲሁም አጠቃላይ ካፒታሉ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ድረስ ለሆነ ድርጅት ከሚሰበስቡ አክሲዮኖች ውጪ የሚደረግ ማንኛውም የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ ከመደረጉ በፊት በባለሥልጣኑ ምዝገባ ተደርጎበት ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች