ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ጥበቃ ለማድረግ የወጡ የሕግ ድንጋጌዎች ቢኖሩም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተመዝግበውና ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ጋዜጠኞችና የኅትመት ውጤቶች በፀጥታ ኃይሎች ከሕግ አግባብ ውጪ መታገታቸው እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ የጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ተጠያቂነት ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ አስሮ የማቆየትና ለሥርጭት የተዘጋጀ የኅትመት ውጤትን የማገድ ድርጊቶች እንደተፈጸመ፣ በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የዕለት ተዕለት ሥራዎቻቸውን ለመሥራት መቸገራቸውን ከደረሱት ሪፖርቶች መገንዘቡን ጠቁሞ፣በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ‹ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሐሳቦች፣ አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሠራር ነፃነትና የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ እንዲደረገለት በተደነገገው መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ ሲል አሳስቧል፡፡
በኢትዮ ሐበሻ አሳታሚ ድርጅት በየሳምንቱ እየታተመ የሚሠራጨው ጊዮን መጽሔትና ዋና አዘጋጁ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው ከአንድ ሳምንት በኋላ ዋና አዘጋጁ ያለ ክስ መለቀቁን ለአብነት የጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ መጽሔቱ አንድ ወር ከ15 ቀን በላይ ቢሆነውም አለመለቀቁንና የትርታ ኤፍኤም 96.7 ሬዲዮ የፕሮግራም ዳይሬክተር ደግሞ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ከተወሰደ ከአንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ የታሰረ ሲሆን፣ ክስ እንዳልተመሠረተበትና ፍርድ ቤትም ሊቀርብ እንዳልቻለ ተናግሯል፡፡ በመናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238 አንቀጽ 85/7 ላይ በግልጽ እንደተደነገገው፣ በየጊዜው የሚወጣ ኅትመት ከመሠራጨቱ በፊት በፀጥታ አካላት የሚሰጥ የዕገድ ትዕዛዝ፣ የትዕዛዙ መነሻ የሆነውን አንቀጽ ወይም አንቀጾች፣ የኅትመቱን ቅፅ፣ ጽሑፉ የወጣበትን ዕትም መገለጽ አለበት፡፡ ዕገዳውም ለሥርጭት በተዘጋጁ ኅትመቶች ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፣ ሲል ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ጊዮን መጽሔት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ በአዋጁ መሠረት ተመርምሮ የጋረጠው አደጋ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ ሲሆን ለፍርድ ቤትም በ48 ሰዓት ውስጥ የቀረበ ክስ አለመኖሩንም አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካይነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ 1238/13 አንቀፅ 86 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ ቢደነገግም፣ የትርታ ኤፍኤም ራዲዮ ጋዜጠኛ ግን ከአዋጁ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለሳምንታት ያለ ክስ በእስር ላይ እንደሚገኝ በድጋሚ አስታውሷል።
የወንጀል ድርጊቶች ከመፈጸማቸው በፊት መከላከል፣ ተፈጽሞ ሲገኝም አፋጣኝና ፍትሐዊ ዕርምጃዎችን በሕግ አግባብ የመውሰድ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለባቸው የፀጥታ አካላት፣ ጋዜጠኞችን አስሮ መረጃ መሰብሰብና አስሮ ለቀናት ክስ አለመመሥረት እንዲሁም የኅትመት ውጤትን ከሥርጭት ማገድ፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱ ሥራቸውን በነፃነት እንዳያከናውኑ የሚያስተጓጉል ተግባር ነው፡፡ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙኃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት፣ በሕጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል ብሎ እንደሚያምን ምክር ቤቱ ተናገሯል፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ሥጋት አስታውቋል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትሕ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤቱን በእጅጉ እንዳሳሰበው ተናግሯል፡፡ ችግሩ እንዲፈታም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አክሏል፡፡
በመሆኑም መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙኃን ተቋማቱ ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥስቶችን በሕጉ አግባብ ብቻ እንዲመራ በማድረግ ሕገወጥ የወንጀል ድርጊቶችን በተቻለ ፍጥነት በማረም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሥነ ምግባር የታነጸ በኃላፊነት ስሜት ሕዝብን የሚያገለግል ሚዲያ በአገራችን እንዲጎለብት የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ በሕግ ተመዝግበው ፈቃድ የወሰዱ የሕዝብ፣ የንግድ፣ የማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃንን፣ የበይነ መረብ ሚዲያንና የጋዜጠኞች ሙያ ማኅበራትን በአባልነት በማቀፍ የእርስ በርስ የቁጥጥር ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡