Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ንፋስን መከተል!

ሰላም! ሰላም! ኑሮው፣ ወሬው፣ ሥራው፣ ፓርላማው፣ ሹማምንቱ እንዴት ሰነበቱ? እናንተስ እንዴት ናችሁ? የዛሬ ስንት ዓመት ነበር በጣም የማፈቅራት ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ እንዲያው ኮራ ብላ እንደነበር አልረሳውም፡፡ ያኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ግማሹ በሴቶች በመሞላቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስደስቷት እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ ምነው ደህና ደህናውን ወግ ትተህ ወሬያችን መሀል ሚስትህን ሰነቀርካት እንደምትሉኝ ይሰማኛል። እኔማ የውድ ባለቤቴ ነገር አይሆንልኝም፡፡ ምነው በየኑሮ ፌርማታው ለወሬ የተመቻቸ ሠልፍ እያያችሁ የውዴን ነገር ችላ ትላላችሁ? ‹‹እስቲ እንደ ዘበት የታክሲን ሠልፍ ካነሳን አይቀር እንጀምረዋ፡፡ እንዴ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስሟ የሚጠራው በሠልፍ ነው ወይስ በብልፅግና? አልገባን አለ እኮ ጎበዝ፡፡ ለዳቦ ወረፋ፣ ለዘይት ወረፋ፣ ለነዳጅ ማደያ ወረፋ፣ ግብር ለመክፈል ወረፋ፣ ለኮንዶሚኒየም ዕጣ ለዓመታት ወረፋ…። አሁን ጭራሽ ልክ እንደ ሥራ ታክሲ ተጠቃሚውም በየቦታው ሠልፍ መያዝ የዕለት ዝርዝሩ ውስጥ ገባለት መሰል። ጠዋት ትነሱና የምትሠሩትን ስታሰላስሉ፣ እሺ አሁን ከዚህ ታክሲ ይዤ ከዚያ… በማለት ነበር በፊት የምትዘጋጁት። አሁን ‹ሠልፍ ይዤ› ሆኗል…›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። ስለዚህ በማንጠግቦሽ አትምጡብኝ፡፡ ዋ ብያለሁ!

ለነገሩ የወረፋ ሠልፍ በአጋጣሚ ተነሳ እንጂ ችግራችን እኮ የከራረመ ነው። ደግሞ እንደ አዛውንቱ ባሻዬ ላሉ አዛውንቶች ምንም እንኳ መቆሙ ቢያዝል፣ ከጎረምሳ ጋር ሳይጋፉ ይሳፈሩ ዘንድ ረድቷል የሚሉ ተንታኞችም አሉን። ‹እኔን ይተንትነኝ› አሉ ወይዘሮ ይርገዱ፡፡ ‹‹ሠልፍ በዘመነ ሶሻሊዝም ቀረ ሲባል እንዲህ ይባስበት? እስቲ ይሁና…›› ይላሉ ባሻዬ፡፡ እናማ ያው እንደምናየው በሠልፍ ላይ ሠልፍ በሸክም ላይ ሸክም ይደራረብብናል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር የሚገርመው ደግሞ ምንም ዓይነት መግለጫም ሆነ ለመፍትሔ የታሰበ ነገር እንዳለ አይነገረንም…›› ሲለኝ፣ ‹‹እህ? እየሰማሁ ነው…›› ስለው፣ ‹‹ይኼም የድርጅት ባህል ይሆን?›› ሲለኝ፣ ‹‹እንግዲህ ማን ያውቃል እሱንም ካልነገሩን…›› እለውና እንሳሳቃለን። የሳቃችን ምንጩ ግን በውል አይገባንም፣ የዘመኑ ባለሥልጣናት የመፍትሔውን ምንጭ ካላመነጩልን በስተቀር፡፡ ባለሥልጣንና ሀብታም ጓደኛ የሆነበት አገር ውስጥ እንደ እኔ ዓይነቱን ደላላ ማን ሰምቶት እያልኩ እቆጫለሁ፡፡ ይህንን የሰማ የጎረቤት ሱቅ ነጋዴ፣ ‹‹እነሱ አንድ ላይ ተባብረው እየደቆሱን ደላላ ከተጨመረበትማ አለቀልን…›› እያለ ሲስቅብኝ ነገሩ ወደ እኔ ኮተት ብሎ እየመጣ መሆኑ ገብቶኝ ጥዬው እብስ አልኩ፡፡ ሳይሻል አይቀርም!

እና የእኛን እየሄዱ መቆም ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ለመረዳት ዋና ዋና የታክሲ መነሻ ሥፍራዎችን በመቃኘት ብቻ ማወቅ ይቻላል። የተለየ ምርምርና ጥናት ምሁራኖቻችን እስኪያደርጉ ድረስ መጠበቅ አያስፈልገንም። ‹‹ምርምርና ጥናት ማድረግ እኮ ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችል ነው ቢባል እንጂ፣ ይኼ ሁሉ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በጥቃቅንና በአነስተኛ ማኅበራት እየተደራጀ ያለ ቦታው አይገኝም ነበር…›› ሲለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ይኼ እንደ ግሪሳ ወፍ የሚረፈርፈው ፈተና ቀደም ብሎ ቢጀመር ስንቱን ጉድ እናየው ነበር…›› ብዬ እንዲጨርሰው አስገድደዋለሁ። ‹‹ከፈተናው በፊት አክሳሪው የትምህርት ሥርዓት የተቀረፀበት ጭንቅላት ላይ ቢሠራ ኖሮ፣ ዛሬ የምናየው መሳቀቅና በልጆቻችን ላይ እየደረሰ ያለው የሥነ ልቦና ጉዳት አይከሰትም ነበር…›› እያለኝ ሲናደድ እኔም ንዴቱ ተጋብቶብኝ ውስጤ በአንዴ እንደ እሳት ነደደ፡፡ የስንቱ ልፋትና ሕልም ሲጨናገፍ ታየኝ፡፡ ወይ ነዶ!

‹‹መሬት ወርዶ ችግር የማይፈታ ትምህርት ማስተማር ሙያ መስሏቸው አገር ሲያራኩቱ ኖረው እነሱም እንዳይሆኑ ሆኑ…›› ብሎ በንዴት የባሰ ሲበግን ይታየኝ ነበር፡፡ ‹‹ጃፓኖች አገራቸው ከአውሮፓ ለምን እጅግ ወደኋላ እንደቀረች ሲያውቁ፣ መጀመርያ ዘለው አካፋና ዶማ ሳይሆን የጨበጡት ብዕር ነው። ዘልቀው አውሮፓ ድረስ በመጓዝ ሙያና ጥበብ ተምረው በአገራቸው በመሥራት ከፍተኛ ውጤት ማስገኘት ቻሉ…›› እያለ ሲያወጋኝ አስብ የነበረው፣ ‹ስንቱን ተማር ብለን ልከን ስንቱ ይመለሳል› የሚለውን ነው። ወጪው ከገቢው የበለጠበት ዘመን፡፡ ምን ሩቅ አስኬደን? ቻይና ጃፓንን ገልብጣ አሜሪካን ደረስኩብሽ የምትለው በዕውቀት አይደል? ዕውቀትና እኛ እስከ መቼ ተኮራርፈን እንዘልቀው ይሆን፡፡ የሚገርማችሁ እኔና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በተለይ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተገኘው ውጤት ለአገር ዓይን ገላጭ ነው ብለናል፡፡ ምክንያቱም ለዓመታት የተከማቸ ችግር እንዲህ በሚገባ ተብጠርጥሮ ታይቶ ነው መፍትሔ ሊገኝለት የሚችለው እንላለን፡፡ መስዋዕትነት ቢያስከፍልም እውነቱን መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ እንዲያ መሰለኝ!

‹‹አንበርብር የአሁኑ የትምህርት ጥራት ውድቀት አብዛኛው ገብቶ ይወጣ ዘንድ እንጂ፣ አውቆ እንዲወጣ እያደረገው ስላልሆነ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡ ሙያና ቴክኒክ ሲስፋፋ አገር ታድጋለች፡፡ ወደፊት በራሳችን ባለሙያዎች በመንገድ ግንባታ፣ በባቡር መስመር ዝርጋታና በትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ምሥረታ በዓለም አቀፍ ደረጃ መፎካከር የሚችሉ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችለንን የከፍተኛ ትምህርት አካሄድ ካልተከተልን ዋጋ የለንም። አሁን እንደሚታየው በተግባር የማይፈተሽ የንድፈ ሐሳብ ጥራት የሌለው ትምህርት ችግር መፍጠር እንጂ ዕድገት አያመጣም…›› እያለ ብዙ ያጫውተኛል። በደላላ ጭንቅላቴ ስንቱ ተይዞልኝ ስንቱ እንደሚሳተኝ እናንተው ገምቱ፡፡ ያም ሆነ ይህ ድህነት እንደ ተራራ ለተቆለለበት አገር ማስተንፈሻ ያስፈልጋል፡፡ የሚበላ ሳይኖር ስለሌላ ጉዳይ ማውጋት የትም አያደርስም ባይ ነኝ፡፡ ውድ ሹማምንቶቻችን በተለይ እስኪ እዚህ ላይ በርቱልን፡፡ ለራስ ትንሽ መቆንጠር ባይቀር እንኳ አገርን ችላ ማለት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሕግ ባይጠይቅ መጪው ትውልድ ይፋረዳል!

አጀብ ነው የዘንድሮ ነገር። ዝም ብለው ሲታዘቧት ሕይወት ብዙ እያስለቀሰች ብዙ ታስቃለች። ለማንኛውም ቀደም ብዬ የዚህን የታክሲ ሠልፍ ነገር ማንሳቴ ሰሞኑን አንድ ‹ቢዝነሴን› አስረፍዶ ስላከሸፈብኝ ነው። ጉዳዬ ተበላሽቶ ተበሳጭቼ ወደ ቤቴ ሳዘግም አንድ ካፌ ጎራ ብል ከውስጥ የቴሌቪዥን ድምፁ ጎልቶ ተከፍቶ የፓርላማ ውይይት ያሳያል። ታዲያ ይኼኔ ምን እንደሚሰማችሁ ታውቁታላችሁ። በቆምኩበት ‹ሰዎቹ ካልሠሩበትና ውጤት ካላገኙበት ምን ዋጋ አለው?› እያልኩ ስወራጭ አጠገቤ ማኪያቶውን ይዞ የተቀመጠ ሰው፣ ‹‹ሳይታቀድና ሳይመከርበት የሚሆን ምን አለ ብለህ ነው?›› ብሎኝ ፈገግ አለ። እንድቀመጥ ጋብዞኝ ጨዋታችንን ቀጠልን። ስለበርካታ ችግሮቻችን ከልክ ማለፍና ዝም የተባሉ የሚመስሉበትን ሁኔታ ያብራራልኝ ጀመር። ‹‹አዎ ችግሮችማ አሉ። ወጥተን መግባት እስክንጠላ ድረስ አላፈናፍነን ብለዋል። ትራንስፖርቱ፣ የገንዘቡ ረድኤት አልባነት፣ የቢሮክራሲው ትብታብ፣ የብሔር ፍጭቱ፣ ደረት ማሳበጡ፣ በጉራ መቆለሉ፣ ምኑ ቅጡ፡፡ ግን አየህ በሒደት ላይ ነን። አገራችን በብዙ መስክ እንደ አዲስ በመሠራትና በመገንባት ላይ ናት…›› እያለኝ እኔም ከታክሲ በተረፈችዋ ገንዘብ ማኪያቶዬን እየጠጣሁ አዳመጥኩት። ‹‹ግን እስከዚያ ምን እንሁን? በዚህ መራር ጊዜ እኮ መንግሥት የሕዝቡን ኑሮ ማረጋጋት አለበት፡፡ ይህ ትውልድ በትክክለኛው ጎዳና ላይ እየተራመደ ለአገሩ ጠቃሚ ሚና እንዲኖረው ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይ አዲሱ ትውልድ በፍትሐዊነትና በእኩልነት ተኮትኩቶ እንዲያድግ መንግሥት አደራ አለበት…›› ስለው ሐሳቤን የተጋራ መሰለኝ፡፡ እኔም ከአቅም በላይ እንዲጫወት ስላልፈለግኩ ‹‹ሒሳብ›› ስል አስተናጋጁ ፈጥኖ ‹‹60 ብር…›› አይለኝ መሰላችሁ? ዘንድሮ እኮ ከማን አንሼው በዛ፡፡ ዝም ብሎ ዋጋ መቆለል ምን የሚሉት አጉራ ዘለልነት ነው፡፡ ‹‹ተመሥገን በል ቦሌ 140 ብር ድረስ ትጠየቃለህ…›› የሚል ድምፅ ሰማሁ፡፡ ምክንያት አልባ ጭማሪዎችና ትንተናዎች ሰለቹን እኮ!

ከካፌው ወጥቼ በእግሬ ስራመድ ይኼንኑ ጉዳይ በውስጤ አብሰለስል ነበር። ‹ዛሬ መኖራችን ሳይረጋገጥ በነገ ተስፋና ምኞት መኖር እንደማይቻል ሁሉም ያውቀዋል። ዛሬ የሚታዩ መሠረታዊ ችግሮች ካልተቀረፉ የነገው ታላቅ የልማት ድግስ አይናፍቀንም የሚል ቢኖርስ? ፈጽሞ ማሟረቴ አይደለም። ግን ራሳችን እያታለልን ማሰብ የሚገባንንና መጠያየቅ ያለብንን ነገር አድበስብሰን ማለፍ እስከ መቼ?’ እያልኩ እጓዝላችኋለሁ። ፓርላማው የጋራ ድምፃችን መሆን ካልቻለ ወገንተኝነት ወንዝ አያሻግርም፡፡ ዘመናችንና እኛ እንመጣጠን ዘንድ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ ‹‹ዘንድሮ ረክሰው ከሚገኙት ነገሮች አንደኛው ተስፋ ነው…›› ያለኝን ሰው ጭምር ለማስታወስ እየሞከርኩ ማዝገሜን ቀጠልኩ። ቀስ እያለ እኮ የማስታወስ ችሎታዬ እያጠራጠረኝ መጣ ጎበዝ፡፡ ‹እንዴ ሳይኖሩ ማርጀት እንዲህ ቀላል ነው?› እላለሁ ብቻዬን ስሆን። ታዲያ ማንጠግቦሽም ጎበጥ ከማለት ወጥታ ቀና ማለት መጀመሯን ሳስተውል ብዙ ደጋግ የፍቅር ቀናት ትውስ ይሉኛል። ‹‹ለትውስታ የሚሆን ነገር አይጥፋ እንጂ ለሌላው ይደረስበታል…›› ትለኝ ነበር ያኔ ፍቅር በጀመርን ሰሞን። አይገርምም? ማንጠግቦሽ ለካ በፊት ነበር ነገር የገባት፡፡ እኔም ሁኔታችንን ስታዘብ እንጂ ስሠራ አለመዋሌ ከንክኖኝ ወደ ቤቴ ተጓዝኩ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አግኝቶኝ ውሎዬን ሳጫውተው ቆየሁ። እንጫወተው እንጂ!

እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የአገር ጉዳይ፣ የሕዝብ ጉዳይ፣ የሰላም ጉዳይ፣ የዴሞክራሲ ጉዳይ፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ፣ ወዘተ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን እየተሰማኝ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናስበው በዓለም ፊት ኩሩ መሆናችንን ነው፡፡ ታላቁን የዓድዋ ጦርነት ድል ስናስብ በዓለም ላይ ለቅኝ ግዛት አለመንበርከካችንን እንመካበታለን፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርዓያ ያደረገን ይኼ ድንቅ ድል የኩራታችን ምንጭ ቢሆንም፣ ሁሌም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደሚያስተምረኝ የመረረው ድህነታችንና ውስጣዊ አለመግባባታችን ያበሳጨኛል፡፡ የአፍሪካ መሰባሰቢያና ዕምብርት ሆነን እኛ እርስ በርስ እንናጀሳለን፡፡ በአገር ጉዳይ አንድ መሆን ሲገባን ለቡድን ጉዳዮች እያደላን እንነቃቀፋለን፣ እርስ በርስ እንሳደዳለን፡፡ በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በፍትሕ መጓደል እንካሰሳለን፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? ይባስ ብለንስ የአፍሪካና የዓለም ታላላቅ ድርጅቶች መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ባለቤትነት ላይ ስንተናነቅ እየተናቅን መሆኑ ለምን አይገባንም፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ከኒውዮርክ፣ ከጄኔቭና ከብራሰልስ ተርታ ተሠልፋ የዲፕሎማቲክ ከተማ የሆነችው ከተማችን እኮ የእኛ ብቻ አይደለችም፡፡ የዓለም ሀብት እንደሆነች አንዘንጋ፡፡ አሁን እኔ ደላላው አንበርብር ምነተስኖት ይኼንን ለእናንተ ማስረዳት ነበረብኝ፡፡ ኧረ ተው እባካችሁ!

የኦሊምፒክ ውድድር ሲኖርብን ሰንደቅ ዓላማችንን ይዘን አንድ ላይ እንዘምራለን፡፡ ነገር ግን ይህችን ሰንደቅ ዓላማ ማዕከል አድርገን ከእነ ልዩነቶቻችን ለአገራችን ለምን እኩል አናስብም? በአገር ጉዳይ አንዱ እየተገፋ ሌላው ባለቤት ለምን ይሆናል? የባሻዬ ልጅ ሁሌም የሚነግረኝ ቁምነገር አለ፡፡ ‹‹የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ለአገርህ ምን እንደምታደርግላት እንጂ አገርህ ምን እንደምታደርግልህ አትጠይቅ…›› ያሉትን ስንቶቻችን እናስበዋለን? ያው ፓርላማ ሲጀመር ሹመት ይኖራል የሚል ወሬ ላይ ነው የከረምነውና እስኪ አንድ ነገር ላውጋችሁና ልሰናበት፡፡ ይኼንን ነገር የነገረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ‹‹ናፖሊዮን ፈጽሞ የማይወደውን አንድ ዝነኛ ጄኔራል ሊሾመው ፈልጎ እንዲህ ብሎት ነበር…›› አለኝ፡፡ እንዲህ ያለ ታሪክ ደስ ስለሚለኝ፣ ‹‹ምን አለው?›› አልኩት በከፍተኛ ጉጉት፡፡ ‹‹ጄኔራል ሆይ ፈረንሣይ ውስጥ ከምጠላቸው ሰዎች መካከል ዋናው አንተ ነህ፡፡ ነገር ግን ለአገርህ ፈረንሣይ በጣም አስፈላጊው ሰው መሆንህን ስለማምን፣ እየመረረኝም ቢሆን ጦሯን እንድትመራላት ልሾምህ እፈልጋለሁ ሲለው፣ ጄኔራሉም ናፖሊዮን ሆይ እኔም በጣም እጠላሃለሁ፣ ውድ አገሬ ፈረንሣይ ከፈለገችኝ ግን ሹመቱን በደስታ እቀበላለሁ…›› በማለት መለሰለት ብሎ ይኼንን መሳጭ ታሪክ ሲነግረኝ እንዲህ ዓይነቱን መልካም ነገር ለውድ አገሬ ተመኘሁ፡፡ እባካችሁ ለአገራችን መልካሙን ሁሉ እንመኝ፣ አገራችንን እንውደድ፣ ዓለም የምሬት ምንጭ በሆነችበት በዚህ ጊዜ አገራችንን ጣፋጭ እናድርጋት፣ ምሬቱ ተወግዶ በደስታ ኖረን ለመጪው ትውልድ እናስረክባት፡፡ አለበለዚያ ግን ንፋስ እየተከተልን ከንቱ አናድርጋት፡፡ ንፋስን መከተል ከንቱ ነውና፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት