Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የማርያም መንገድ››

‹‹የማርያም መንገድ››

ቀን:

‹‹የማርያም መንገድ››፣ ልጅነት ብርሃንነት እንዲሉ፣ አንድም በልጅነት ጨዋታ ጊዜ የማርያም መንገድ ስጡኝ ማለትን ለመጠየቅ፣ ለማስታወስ፣ በፒሊንግ ቴክኒክ ተሥሎና በቀይ፣ ጥቁርና ነጭ አሸብርቆ ለዕይታ የቀረበ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ነው፡፡

‹‹ቀይ፣ ጥቁር፣ ነጭ በክርስትናው እምነት በጥምቀት ጊዜ አንገት ላይ የሚታሰረው ማተብ የአብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስን ቀለማት ይወክላሉ፡፡ በጥቁር አንድም አብ ማንም አይቶት አያውቅም የሚለውን፣ በቀይ አንድም ወልድ ክርስቶስ ነው በደሙ አድኖናል እንዲባል፣ በነጭ አንድም መንፈስ ቅዱስ በነጭ ርግብ ይመሰላልና፣ በማርያም መንገድ የተሰየሙት ሥዕሎች እነዚህን ቀለማት ይዘዋል፤›› የሚለው ሠዓሊ ለይኩን ናሁሰናይ ነው፡፡

‹‹የማርያም መንገድ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ሠዓሊ ለይኩን ናሁሠናይ

ከሥዕሎቹ በጥቁርና ነጭ ዳማ መስለው የተሠሩም አሉ፡፡ ሠዓሊው እንደሚለው፣ የሕይወት ምሳሌ ከመጨለምና መንጋት፣ ከመኖርና መሞት፣ ከሰማያዊና ምድራዊ መወከሉን ለማሳየት የተሞከረበት ነው፡፡ አሁናዊ (ኮንተምፖራሪ) ሆኖ መሠራቱ ደግሞ ለማመስጠርም ነው፡፡

ሠዓሊ ለይኩን፣ ‹‹ብላክ ማዶና›› ወይም የማርያም መንገድ ብሎ ለሰየማቸው የሥዕል ሥራዎች መነሻውም የሉቃስ ሥዕል ነው፡፡

‹‹ብላክ ማዶና›› (ጥቁር ማርያም) መነሻው ጣሊያን የሚገኘው የወንጌላዊው ሉቃስ ሥዕል ነው፡፡ ሌላኛው የሉቃስ ሥዕል ደግሞ በጎጃም ደብረወርቅ ገዳም ይገኛለ፡፡

በዓውደ ርዕዩ ከቀረቡት ውስጥ አንዱ የሆነው የጎልጐታ ሥዕልም፣ ብላክ ማዶና (ጥቁሯ ማርያምን) ከወንጌላዊው ሉቃስ ተነስቶ እንደሠራ ሁሉ፣ ጎልጎታን ከገብረ ክርስቶስ ደስታ በመነሳት የሣለበትን ለማሳየት ነው፡፡

ወንጌላዊው ሉቃስ ብላክ ማዶና ብሎ የሠራት የቅድስት ማርያም ምስል ጥቁር ገጽ ያላት ሲሆን፣ ጥቁር ማርያምን በቅርፅም በሥዕልም የሚያሳዩ የማርያም ምሥሎችም በአውሮፓ ብቻ ከ400 እስከ 500 ይገኛሉ፡፡ በፈረንሣይ  200 ያህል ብላክ ማዶና ሥዕሎች እንደሚገኙ የሚገልጸው ሠዓሊ ለይኩን፣ የማርያም መንገድ ብሎ የሥዕል ሥራዎቹን ሲያቀርብም፣ እንደ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊነቱ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ምድብ እንድትገባ በማሰብ ነው፡፡

‹‹የማርያም መንገድ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በብላክ ማዶና ዓውደ ርዕይ ከቀረቡት ሥራዎች መካከል

‹‹የማርያም መንገድ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በብላክ ማዶና ማርያም ለምን ጥቁር ሆና ተሣለች ተብለው በተሠሩ ጥናቶች ግብፅና ኢትዮጵያ መጠቀሳቸውን የሚያስታውሰው ሠዓሊ ለይኩን፣ ይህ በሥዕል ሥራዎቹ ጥቁር ማርያምን እንዲያሳይ አነሳስቶታል፡፡

የማርያም መንገድ ብሎ በጥናቶች ላይ ተንተርሶ ሲሠራ፣ የማርያምን የግብፅ ስደት ለማሰብ፣ በልጅነት ጨዋታ ‹‹የማርያም መንገድ ስጡኝ፣ የመውጫ መንገድ ስጡኝ›› ከሚለው መልዕክትም ይመዘዛል፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን በሥዕል ሕይወት ውስጥም ልጅ መሆን ንጽሕናን ያሳያልና፣ ይህም ከሥራዎቹ ጋር ተዘምዶ አለው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልጆች የአርት ማስተር ናቸው፣ ልክ ናቸው፣ ንፁሕ ናቸው እንደሚባለው ሁሉ፣ ቀለምን ሲቀቡ ሆነ ሲናገሩ ልባቸው ክፍት መሆኑን፣ በልጅነት ዘመን በጨዋታ ላይ ‹‹የማርያም መንገድ ስጡኝ›› ሲባል መውጫ እንደሚመቻች፣ የሥዕል ሥራዎቹም ይህንን ለማሳየትና ለማጠየቅ እንደተሠሩ ሠዓሊ ለይኩን ተናግሯል፡፡

‹‹የማርያም መንገድ›› እንደ ሕፃናት፣ እንደ ንጽሕናቸውና እንደነሱ በቀላሉ ሐሳብን የሚገልጽ ነፃ ሥዕል በመሣል ሐሳብ የተገለጸበትም ነው፡፡

እንደ ሠዓሊ ለይኩን፣ የማርያም መንገድ የሥዕል ሥራዎች አንድ ዓላማም ሰንቀዋል፡፡ ብላክ ማዶና ወይም ጥቁሯ ማርያም በአውሮፓ የታወቀችውን ያህል ኢትዮጵያንም በዚህ ሥራ ማስተዋወቅ ነው፡፡

‹‹የማርያም መንገድ›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን የመጠየቅ፣ የማርያም መንገድ ስጡን ብሎ የመለመንም ሐሳብ በሥራዎቹ ለመግለጽ መሞከሩን ያስረዳል፡፡

የለይኩን ሥዕል ምንድነው? ሲባልም በ17ኛው ምዕት ዓመት ከነበረው አሣሣልም የተለየና ብላክ ማዶና የተሣለችበትን መንገድ ተከትሎ በአሁናዊ አሣሣል የቀረበ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከዚያ ተነስቶ የሠራበት ምክንያትም ለማመስጠርና በተረዳው መንገድ ለመግለጽ ነው፡፡ አቀባቡም፣ አሣሣሉም አሁናዊ ሲሆን፣ አውሮፓዊውም፣ አፍሪካዊውም እንዲረዳው ተደርጎ የተሣለ ነው፡፡

ጥቁር ማርያምና የማርያም መንገድ ከሠዓሊ ለይኩን ሥራዎች የተዛመዱበትና በፒሊንግ ቴክኒክ ማለትም በመቀነስ ወይም ቀይ ወረቀት ብቻ በመላጥ የተሠሩት ሥራዎች በስካይ ላይት ሆቴል ከመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እየታዩ ሲሆን፣ ጥቅምት 19 ቀን የዕይታ ጊዜያቸው ያበቃል፡፡

ሠዓሊ ለይኩን ናሁሰናይ በሥነ ጥበብ ሙያው በግልና በቡድን በመሥራት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ አካብቷል። በአሁኑ ወቅት ፕሮፌሽናል ስቱዲዮ አርቲስት ሲሆን፣ በሥነጥበብ ምርምርና ፎቶ ባለሙያነት ይሠራል። በሥነ ጥበብ ሙያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበባት ትምህርት ቤት በመምህርነት ተመርቋል፡፡ በቀድሞው የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በእንጨት ሥራ ዲዛይን (ውድከት ግራፊክስ) ተመርቋል።

በሥነ ጥበብ በቆየባቸው ዓመታት ሥራዎቹን በአገር ውስጥና ባህርማዶ በቡድንና በግል በተካሄዱ ዓውደ ርዕዮች ላይ አሳይቷል። ከእነዚህም መካከል Blachère Foundation በፈረንሳይ፣ Saon Zurcher Art Fair በኒውዮርክ፣ EDSA-EthioDanish Space Agency በአስኒ ጋለሪ አዲስ አበባ፣ በፈረንሳይ Contemporary African Art Fair፣ ፋውንዴሽን በኒውዮርክ የተዘጋጁት ይጠቀሳሉ።

በአዲስ ፋይን አርት Process and Progression እና በአስኒ ጋለሪ Flying Spoons በልዩ ቅርፃ ቅርፆች በአዲስ አበባ የግል ዓውደ ርዕይ ያቀረበ ሲሆን፣ በአራተኛው የባማኮ ፌስቲቫል ላይ የፎቶግራፍ ስብስቦችን አሳይቷል።

በአዲስ አበባ የፈረንሣይ ለጋሲዮን ነፃ አርት ቪሌጅ መሥራች አባልና ተሳታፊም ነበር። በፒያሳ ራስ መኰንን ድልድይ ከጉራማይሌና ክታብ ስቱዲዮዎች ጋር በመጎራበት በታዋቂ ሠዓሊዎች ሲካሄድ በነበረው የሥነ ጥበብ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። በተለይም በናስ ገዳም ስቱዲዮው ከ20 ዓመታት በላይ ለመሥራት መብቃቱን በገጸ ታሪኩ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...