Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኑሮ ፍዳ

የኑሮ ፍዳ

ቀን:

ከትልልቅ የጅምላ አከፋፋዮች እስከ ትንንሽ ቸርቻሪዎች ከሱፐርማርኬት እስከ ጉሊት ባሉ የገበያ ቦታዎች እግር እስኪቀጥን ቢዞር ነጋዴዎችን አንድ የሚያደርጋቸው ቢኖር ‹‹ጨመረ›› የሚለው ቃል ሳይሆን አይቀርም፡፡

ጧት የችርቻሮ ከሰል ገዝታ የተመለሰች እናት፣ የጣደችው ድስት ሳይወርድ አቋርጧት ድጋሚ ለመግዛት ስትሄድ በቀላሉ የአምስት ብር ጭማሪ ተደርጎበት ታገኛለች፤ ለምን ብላ ስትጠይቅ ‹‹ጨምሯል›› ስለተባለ ነው ልትባል ትችላለች፡፡ ምን ይደረጋል ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ሳይበላ አይዋል፣ አይታደር አድሮ ለመገኘት ጨመረ የተባለውን ጨምሮ መግዛት የውዴታ ግዴታ ነው፡፡

ምንም እንኳን አልጨምርም ብሎ ተከራክሮ ባያሸንፍም አንዳንድ ሰው ጭማሪ ላይ የጦፈ ክርክር የሚያደርገው ታክሲ ላይ ነበር፡፡ እሱም አሁን አሁን ቀርቶ ሰው ስለ ታሪፍ ሳይሆን የሚያስበው ታክሲ መጥቶ ከረዥሙ ሠልፍ እንዲገላግለው ብቻ ነው።

ከተሳፋሪዎች አንዱ ተሳስቶ መንገድ ትራንስፖርት ካወጣው ታሪፍ በላይ አልከፍልም ቢል የብዙ ሰው ግልምጫ ሊወርድበት ይችላል፡፡ ስለዚህ ያለው ብቸኛ አማራጭ የተጠየቀውን መክፈል ይሆናል፡፡

በሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዛሬ ላይ በገዙበት ዋጋ ነገ ለመድገም ማሰብ ዘበት እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአንድና የሁለት ብር ጭማሪ ተረት ሆኗል፡፡ ለአብነት ከሃያ ብር ሸቀጥ ላይ በቀላሉ ጭማሪ ተደረገ ከተባለ የአምስት ብር ጭማሪ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ያለውም በየደረጃው ‹‹ጨምሯል›› መባሉ አይቀሬና የተለመደ ሆኗል።

መልካምነትና የሰብዓዊነት መንፈስን የተላበሱ፣ የዛሬውን ውሽንፍር ሳይሆን ነገ የተሻለ ይሆናል ብለው የሚያስቡ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ሠላሳ ቀን ሲሞላ ሦስት መቶ ስድሳ ቀን የደረሰ የሚመስላቸው የቤት አከራዮችም አይጠፉ፡፡ በየወሩ የሚደረድሩት ሰበብ አያልቅባቸውም፣ ቤቱ ሊሸጥ ስለሆነ ሌላ ቤት ፈልጉ፣ ከውጭ አገር የሚመጣ ቤተሰብ ስላለ ሊገቡበት ነው፣ ፈርሶ ሊታደስ ስለሆነ ሌላ ቤት ፈልጉ፣ መንግሥት የጣራና ግድግዳ ክፍያ ዕዳ ጣለብን፣ የመብራትና የውኃ ክፍያ በዛብን… የሚሉት እሮሮዎች የቤት ኪራይ ጨምሩ ለማለት የሚደረጉ ዙሪያ ጥምጥሞች ናቸው፡፡

በእርግጥ ይህ ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም ትንሽ የሰብዓዊነት ጭላንጭል ሲኖር እንጂ አንድ የቤት አከራይ በፈጣጣው በየወሩ ልቦናው የፈቀደውን ያህል ገንዘብ ጨምሩ ቢል ወዴት አቤት ይባላል? ተገብቶ እስከተወጣ ድረስ መክፈል ይቀጥላል።

በቀጣዩ ዓመት በአንዳንድ ቦታዎች ድርቅ ሊከሰት ይችላል ብሎ ሚቲዎሮሎጂ ሲተነብይ የሰማ ነጋዴ፣ ወደ ገበያ ሊያወጣው የነበረውን ጤፍ ቆልፎ ሊያኖረው ይችላል፣ አልያም የተባለውን ታሳቢ አድርጎ መጨመሩ አይቀርም።

ማሽላው ከጉድጓድ፣ ጤፉ ከጎተራው ሳይሟጠጥ፣ እሸቱ ከጓሮው ሳይጠፋ ከጋጣው ተስቦ ወደ ገበያ የሚወጣ በግና ፍየል፣ ላሙና በሬው ሳይታጣ የኑሮ ውድነት ግን መጭ ብሎ እንደፈረስ ያለ ልጓም እየጋለበን ነው ሲሉ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ነዋሪዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

እንደዚህ የኑሮን ቀንበር የጫነብን የዕዳና የፍዳ ዘመን ያደረገብንስ ምን ይሆን ሲሉ ቢጠይቁም የሚያገኙት መልስ ‹‹ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ›› እየሆነ ቢያስቸግራቸውም ከመጠየቅ ግን እንዳልቦዘኑ ያወሳሉ ።

 ከጥያቄዎች ባሻገር ‹‹ረሃቤ ጥማቴ እርዛቴ ሦስቱ ይደበድቡኛል ባንድ እየዶለቱ›› የሚለውን ቆየት ያለ ስንኝ ደጋግመው የሚያንጉራጉሩ እናቶች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ይስተዋላል።

በአዲስ አበባ ያለው የኑሮ ወጀብ ከግራ ወደ ቀኝ፣ ከቀኝ ወደ ግራ እያላጋቸው ካሉ በርካታ ሰዎች መካከል ወ/ሮ ጥበበ ተዘራ አንዷ ናቸው፡፡

ወይዘሮዋ ያሳለፉትን የበፊት ዘመንና አሁን የደረሱበትን ወቅት እያጣቀሱ እያወዳደሩ አንዳንዴም በምናባቸው ያሳለፉትን ዓመታት ጎብኝተው እየተመለሱ ነው የሚያወሩት፡፡

‹‹እኔስ ኑሬዋለሁ ሲከፋኝ ሲደላኝ

ከእንግዲህ ተወልዶ ሰው ለሚሆን ይብላኝ›› የሚለውን

የባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንን ግጥም በውስጣቸው የሚሉ ይመስላሉ።

እርጅና መጣሁ መጣሁ እያላቸው እንደሆነ ፊታቸውንና መላ ሰውነታቸውን አይቶ መገመት አያቅትም፡፡ ከዚህም በላይ ኑሮ ከዕድሜያቸውና ከአቅማቸው በላይ ሆኖ እየደቆሳቸው እንደሆነ እሳቸው ሳይናገሩ ዓይነ ውኃቸው ይመሰክራል።

የረዥም ጊዜ የትዳር አጋራቸው በሞት ከተለያቸው አሥራ አምስት ዓመት ሆኖታል የሚሉት ወ/ሮ ጥበበ፣ ኑሮን ከአንድ ልጃቸው ጋር በመሆን እየገፉት ቆይተዋል።

የትዳር ጓዳቸው በደርግ ዘመነ መንግሥት ወታደር እንደነበርና በዚህም ለአገሩ ዳር ድንበር ሲዋደቅ፣ ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ዘብ ሲቆም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ ለተልዕኮ ሲንከራተት፣ የአንገታችን ማስገቢያ ጎጆም ሆነ ሊጦረን የሚችል ቋሚ ንብረት ሳያፈራ፣ ዕድሜ ዘመኑን ‹‹አገሬ›› እንዳለ ያማረውን ሳይበላ የከጀለውን ሳይለብስ እንዳለፈ ትዝታ በተሞላበት ፀፀት ያስታውሳሉ፡፡

ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር በቃላት ሊገለጽ የማይችል መስዕዋትነት የከፈለን የአገር ባለውለታ ኢሕአዴግ ‹‹የደርግ አሽከሮች›› በማለት መከራ አብዝቶባቸው እንደነበርና እሳቸውም አብረው መከራን እንደተቀበሉ ያነሳሉ።

ይሁን እንጂ ከአያሌ ዓመታት እንግልት በኋላ ሲያገለግልበት የነበረው የጡረታ ተቆራጭ እንዲጠበቅላቸው መደረጉን ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ባለቤታቸው ለመጠቀም ባይታደልም ለእርሳቸው ግን ጥሎላቸው የሄደው ብቸኛ ሀብት ይች ተቆራጭ ሆና ተመዝግባለች ይላሉ፡፡

ወርኃዊ የጡረታ ተቆራጯም የኑሮ ውድነቱ ሲጨምር እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ ሲደረግ አብራ ከፍ እያለች፣ የዛሬ አሥር ዓመት ከነበረችበት 60 ብር በመነሳት በአሁኑ ወቅት 700 ብር ደርሳለች ብለዋል።

‹‹በአሁኑ ወቅት ከምትደርሰኝ 700 ብር የመጀመሪያዋ 60 ብር ብዙ ነገር ትሸፍንልኝ ነበር፤›› የሚሉት ወ/ሮ ጥበበ፣ አሁንም ቢሆን በእርጅና ዘመናቸው እጃቸውን ወደ ቅርብ ዘመዶቻቸው መዘርጋታቸው አልቀረም፡፡ አንድ ልጃቸውም ቢሆን ለራሱ ‹‹በሁለት እግሩ መቆም አቅቶት እየተንገዳገደ ነው፣ እንኳንስ ሊረዳኝ ባገኘሁና ብረዳው ብዬ እመኛለሁ፤›› ይላሉ።

በወር 700 ብር መጥቶ የጎደለውን ባይሞላላቸው፣ የጎበጠውን ባያቃናላቸው    የሚፈልጉትን ቀርቶ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳይ ባያሳካላቸው፣ እንዲሁም እንደ እሳት ከሚጋረፈው ከሰው ፊት መቆምን ባያስቀርላቸውም፣ ነገር ግን ባለቤታቸው ለአገር ከፍለውት ያለፉትን ውለታ ለማስታወስ በየወሩ ሟች ባለቤታቸውን ለመዘከር እንደጠቀማቸው ይናገራሉ።

በማምሻ ዕድሜያቸውም ቢሆን ሰላምና ፍቅርን አጥብቀው የሚሹት እናት፣ በየዕለቱ በቴሌቪዥን መስኮት በሚመለከቱትና ከሚሰሙት ወሬ በመነሳት ከአሁኑ በበለጠ የነገው እንደሚያሳስባቸው ያነሳሉ፡፡

‹‹በየቦታው ልጆቻችን እርስ በርሳቸው እየተገዳደሉ እንደሆነ እያየሁ ነው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ጥበበ፣ በዚህም ልባቸው እንደተሰበረ ተናግረው ፈጣሪ በዓለም ዙሪያ ላሉ ፍጥረታት ሁሉ ሰላሙን ሁሉ እንዲያወርድላቸው መልካም ምኞታቸው ነው።

አርሶ አደሩ በወቅቱ አርሶና ዘርቶ እንዲሁም በወቅቱ ሰብስቦ ወደ ጎተራው ካላስገባ፣ ነገ ወደ ገበያ ይዞት የሚወጣው ቀርቶ ራሱ ለልመና መውጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ነጋዴውም ቢሆን ገበሬው ቋጥሮ ካልወጣ ሸምቶ ለከተሜው የሚያቀርበው ካላገኘ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ የነገው ዕጣ ፈንታ ከዛሬው የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያቅትም ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...