Monday, December 11, 2023

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል ያስነሳው ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጀመረው አዲሱ የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በተማሪዎችና በወላጆች ላይ ድንጋጤ ከመፍጠር አልፎ፣ ጉዳዩን በበላይነት በሚመራው በትምህርት ሚኒስቴርና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መካከል ሰሞኑን አለመግባባት ተፈጥሯል፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል ያስነሳው ውዝግብ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ
ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)

በኢትዮጵያ ባለፉት አሠርት ዓመታት በተለይም በኢሕአዴግ ዘመን በትምህርት ተደራሽነት ላይ የተከናወነው ሥራ በብዙዎች ዘንድ ቅቡልነት ማግኘቱ የሚነገር ቢሆንም፣ የጥራቱ ጉዳይ ግን ለብዙዎች ሕይወት መበላሸትና አጠያያቂ ከመሆኑም በላይ አገር የምትፈልገውን የተማረ የሰው ኃይል እንዳታገኝ የተደረገ ሴራ ነው በማለት የሚሞግቱ አሉ፡፡

ብልፅግና ፓርቲ በምርጫ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ መንግሥት ከመሠረተ በኋላ የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት የተፎካካሪ ፓርቲው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ በኢሕአዴግ ዘመን የነበረውን የትምህርት ጥራት ስብራት ለማስተካከልና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚመሩት ተቋም በርካታ ማሻሻያ እያካሄደ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከሚያካሂዳቸው ማሻሻያዎች መካከል በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ የተደረገው ለውጥ ነው፡፡ ከቀደሙት ጊዜያት በተለየ ለሁለተኛ ጊዜ መሰጠት በጀመረው አዲሱ የአፈታተን ዘዴ፣ በርካታ ተማሪዎች ሚኒስቴሩ ያስቀመጠውን የማለፊያ ውጤት ማምጣት አለመቻላቸው ይፋ የተደረገው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡

ሚኒስቴሩ በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ካስፈተናቸው ከ845 ሺሕ በላይ ተማሪዎች መካከል 50 በመቶና ከዚያ በላይ ማምጣት የቻሉት 27,267 ተማሪዎች ወይም ከአጠቃላይ 3.2 በመቶ ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ የተማሪዎቹን ውጤት ይፋ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ በበርካቶች ዘንድ የተደበላለቁ ስሜቶች እየተንፀባረቁ ነው፡፡

ከሰሞኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2016 የበጀት ዓመት ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ገምግሟል፡፡

በግምገማው ወቅት በአመዛኙ በ2015 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በተለይ የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል በቋሚ ኮሚቴውና በሚኒስቴሩ መካከል አለመግባባትን ፈጥሯል፡፡

የተማሪዎቹ ውጤት ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች እየተሰጡ ካሉ አስተያየቶች መካከል የተሰጠው ፈተናው ከተማሩት ትምህርት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑንና አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ በሌለበት የተፈተኑ ተማሪዎች መኖራቸውን፣ መጻሕፍትን የመሳሰሉ ግብዓቶች በሌሉበት መፈተናቸውና መሰል ማነቆዎችን በመጥቀስ ተማሪዎች ወደቁ ተብሎ መነገሩ ተገቢ አይደለም የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ይህን አስተያየት ሊያረጋግጥና እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችለው የትምህርት ሚኒስቴር ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው በአጠቃላይ ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት ከነበረባቸው ተማሪዎች መካከል 26.8 በመቶ የሚሆኑት በጦርነት፣ በድርቅ፣ በጎርፍና መሰል አደጋዎች ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት አልመጡም የሚለው ሪፖርት ነው፡፡

በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ የትምህርት መሠረተ ልማቶች ከአጠቃላይ ተቋማት መካከል 12.4 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ በየትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን ብቃታቸው ተመዝኖ ተረጋግጦ እንደማያውቅ ያስታወቀው የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2016 ዓ.ም. ቢያንስ አሥር በመቶ የሚሆኑትን መምህራን ብቃታቸውን እመዝናለሁ ብሏል፡፡ ለቋሚ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ለመካከለኛ የትምህርት ደረጃ ማለትም ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል የትምህርት ደረጃ ብቁ የሆኑ መምህራን 29.8 በመቶ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የካሪኩለም ለውጥ በማድረግ በውጭ አገር አዲስ መጻሕፍት አሳትሞ ወደ አገር እያስገባ መሆኑን ቢያስታውቅም፣ ተማሪዎች ግን አልደረሳቸውም ነው የተባለው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ እንደገለጹት አሁን ከውጭ ታትመው ወደ አገር እየገቡ ካሉ የመማሪያ መጻሕፍት መካከል 249 ኮንቴይነሮች ጂቡቲ ወደብ ደርሰዋል፡፡ ጂቡቲ ወደብ የደረሱ መጻሕፍት በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለክልሎች መሠራጨት እንደሚጀምሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረተ ከውጭ ታትመው የገቡት መጻሕፍት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የሚሠራጩ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በሥርጭቱ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ለአራት ተማሪ ይደርሳል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ሴሚስተር አንድ መጽሐፍ ለሁለት ተማሪ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡

በመጻሕፍት አቅርቦት እጥረትና በፀጥታ ችግር ውስጥ ሆነው ፈተና የወሰዱት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃው የጠበቀ ፈተና መውሰዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እሸቱ (ዶ/ር) ለቋሚ ኮሚቴ አባላት ሲያብራሩ፣ ‹‹አንዳንድ ሰዎች ሚዲያ ላይ ደፈር ብለው በመውጣት በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ፈተናው ምን ያህል ደረጃውን ጠብቋል በማለት ማብራሪያ ሲሰጡ ይደመጣሉ፤›› ብለዋል፡፡ በተቋማቸው ወደ 200 የሚጠጉ የትምህርት ባለሙያዎች ለወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ የፈተና መሥፈርቶች መሠረት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የፈተና ስታንዳርድና የፖሊሲ አቅጣጫ መሠረት ከሥርዓተ ትምህርት ጋር በመናበብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ይህን ቢልም ከኅብረተሰቡም ሆነ ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው ጥያቄ ግን፣ ተማሪዎቹን በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት ፈተንኩ ሲል በስታንዳርዱ መሠረት አስተምሮ የሚጠበቅባቸውን ውጤት እንዲያመጡና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለምን አልሠራም የሚል ነው፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም ለተፈጠረው የውጤት ማሽቆልቆል ጥናት እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

ጥቅምት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በነበረው የቋሚ ኮሚቴ ስብብባ ውጤቱ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ተብሎ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ባውቅ ምን አስደበቀኝ ይላሉ የአራዳ ልጆች፡፡ የ12ኛ ክፍል ውጤት እንዲህ መሆኑ ሁላችንም አስገርሞናል፡፡ ምንም እንኳ መጠበቅ የነበረብን ጉዳይ ቢሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም በፊት የፈተና ውጤት በክልልና በትምህርት ቤት ደረጃ በተደራጀ መንገድ የሚሰረቅ መሆኑን አስረድተው፣ ‹‹ነገር ግን የፈተናውን አሰጣጥ መቀየር ብቻ ይህን ካሳየን ከዚያ በፊት ተማሪዎች ሲያስመዘግቡት የነበረው ውጤት የተማሪዎችን ትክክለኛ አቅም የሚያመላክት አልነበረም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ፈተና የተማሪዎችን አቅም አሳይቶናል፣ የምንደበቅበት ቦታ የለም፣ ሰርቀን የምንናሳይበት ቦታ የለም፡፡ ራቁታችንን ምን እንደምንመስል አሳይቶናል፡፡ ያ ያሳየን የትምህርት ሥርዓቱ ሥር የሰደደ መሠረታዊ ችግር እንዳለበት ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የፈተናውን ውጤት የመደናገጥ፣ የማዘንና ለአገር የመጨነቅ ስሜት ውስጥ እንደከተታቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ከዚህ ችግር በፍጥነት ለመውጣትና ለመቀየር እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት የመምህራንና የመጻሕፍት አቅርቦት ችግር፣ የተሟላ መሠረተ ልማት አለመኖር መቅረፍ፣ መምህራንና ዳይሬክተሮች ከፖለቲካ ሥራ እንዲወጡና ሚናቸውን ማስተማር ብቻ መሆኑን የማሳወቅ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ለውጤቱ መውረድ ተጠያቂው ማነው ተብሎ ከምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በእናንተ የምክር ቤት አባላት አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ምን ሲያደርግ እንደነበር መጠየቅ አለበት፤›› ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) የትምህርት ሚኒስቴር፣ የሚዲያው፣ የወላጆችና የሁሉም ኃላፊነት አለበት የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) 97 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች 50 በመቶና ከዚያ በላይ ማምጣት አለመቻላቸው እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም ብለው፣ ሚኒስቴሩ ዕቅዱን መልሶ እንዲያይና ከዚህ ችግር ለመውጣት በሚያስችል መንገድ በድጋሚ እንዲከልስ ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ትኩረት ይሻሉ ያሉዋቸውን ጉዳዮች ሲያስረዱ፣ ‹‹በአንድ በኩል የትምህርት ሥርዓቱን ተቀይሯል፣ ነገር ግን ተማሪዎች ማግኘት ያለባቸን አስፈላጊውን ግብዓትና የትምህርት መሣሪያ ሳያገኙ ተፈትነው በተለይም በ2014 ዓ.ም. እና በ2015 ዓ.ም. ውጤት መውረድ አፈጻጸሙን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹97 በመቶ ተፈታኞች ውጤት አለማምጣታቸው እኛ በዚህ መድረክ ላይ እንዲሁ በቀላሉ እንደሚሰጠው ምክንያት አይደለም፣ አንድምታው ቀላል አይመስለኝም፤›› ያሉት ነገሪ (ዶ/ር)፣ ‹‹ተጠያቂ የሚሆነው ማነው ሲባል ሁሉም ነው በሚል ከሚኒስቴሩ የቀረበው ምላሽ፣ ማንን ልንጠይቅ ነው ሁሉንም በሚል በጅምላ የተጠቀሰው?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አስፈጻሚዎች የተደራጁት በተልዕኳቸው ልክ መሆኑ ሁሉም የሚባል ነገር እንዳይመጣ ታሳቢ በማድረግ በመሆኑ፣ ሁሉም ተጠያቂ ነው የሚለው ጉዳይ ግልጽነት ይጎድለዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ኃላፊነት መጠን የእኔ ውድቀት ነው ብሎ ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ውጤት የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ምን ዓይነት ክትትል ተደረገባቸው? ተማሪዎች ወድቀው ለወደቁበት ምክንያት ካልቀረበ ምንም እንዳልተፈጠረ ሥራውን ሊቀጥል ነው ማለት ነው?›› ሲሉም አክለው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡  

‹‹እኛ በተረዳነው መጠን ኩረጃን ስላስቀረን ነው ተማሪ የወደቀው የሚለው ነገር ሁሉንም ላያሳምን ይችላል፡፡ በተወሰነ ደረጃ እውነት ነው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እስኪ ለምንድነው እንዲህ የሆነው ብላችሁ ጠይቁ፤›› በማለት ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በመሆኑም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ በግልጽ ሲጠይቅ እንዲሁ የራሳችን አስተያየት በመስጠት ለማለፍ ሳይሆን፣ የተጣራ መረጃ የሚገኝበትን ጥናትና ምርምር ማድረግ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

 ጥናት አድርጉ የሚለውን ለትምህርት ሚኒስቴር መምከር አስፈላጊ አለመሆኑን፣ በገለልተኛ ምሁራን መሠረታዊ ችግሮቹ በአግባቡ ካልተጠኑ መፍትሔ ለመፈለግም እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡ ነገሪ (ዶ/ር) የትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ ዕቅዱ አጥኚ ቡድን አካቶ ችግሩን እንዲያጠናውና በውጭ የሚባለውን ነገር የሚያጣራ ዳሰሳ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቋሚ ኮሚቴው ገለልተኛ አጥኚ ቡድን አቋቁሞ ጥናት ያካሂድበት ወይ ተብሎ ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን ጥያቄ፣ ፓርላማው ራሱ እንደ አንድ ገለልተኛ አካል አጥኚ ቡድን አቋቁሞ ለምን አያስጠናም ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ሞግተዋል፡፡

ፓርላማው ጉዳዩ ያን ያህል ጠቃሚ ነው ብሎ ካሰበና ሚኒስቴሩ ከሰጠው ምክንያት ውጪ ሌሎች ምክንያቶች ይኖራሉ ብሎ ከገመተ፣ ቋሚ ኮሚቴው ቢያስብበት በማለትም ተናግረዋል፡፡

ይሁን አንጂ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከሚኒስትሩ የቀረበውን ፓርላማው ያጥናው የሚል ጥሪ፣ ‹‹ከአሠራር አኳያ ተገቢ አይደለም፣ እኛ አይደለንም የምንሠራው፣ ገለልተኛ ስንል ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በትምህርት ዘርፉ ከሚኒስቴሩ ውጪ ባሉ ባለሙያዎች በመታገዝ ጥናት ቢያስደርግ ለራሱ ግብዓት ያገኝበታል፤›› ብለዋል፡፡

ነገሪ (ዶ/ር) አክለውም፣ ‹‹ለውጤት ማሽቆልቆል ትምህርት ሚኒስቴር አጠናሁ የሚለውን በዝርዝር አላየነውም፡፡ የፈተና ውጤቱ በቅርብ ነው የወጣው፡፡ መቼ ጥናቱን አካሄዳችሁ?›› በማለት ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ባለፈው ዓመት አካሂዳችሁ ከሆነ አናውቅም፡፡ ካለፈው ዓመት በተሻለ በዚህ ዓመት ብዛት ያላቸው ተፈታኞች እንደሚያልፉ ዕቅድ ተይዞ፣ ዘንድሮ የበለጠ ሲወድቁ ሚኒስቴሩ የተፈጠረው ችግር ምንድነው ብሎ መገምገም አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም ዋናውን ምክንያት በማጥናት የመፍትሔ አማራጮችን በመያዝ መወሰድ ያለበት አስፈላጊ ዕርምጃ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -