የዓለማችንን ሕዝብ ዓይንና ጆሮ የያዘ ቀዳሚ ሰሞናዊ ጉዳይ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከስድስት መቶ ቀናት በላይ የዓለማችን ‹‹ትልልቅ›› የሚባሉ መገናኛ ብዙኃን መሪ ዜናቸው አድርገው የቆዩትን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት አቀዝቅዘው ለእስራኤልና ሐማስ ጦርነት ቦታውን ሰጥተዋል፡፡ ይህ ጦርነት ዓለምን ከዳር እስከ ዳር ያነጋገረ፣ መጨረሻውም የተናፈቀ ሆኖ፣ ነጋ ጠባ የዚህ ትኩስ ጦርነት ወሬ በየመገናኛ ብዙኃኑ በሰበር ዜናነት እየተለቀቀ ነው፡፡
አገራችንም የዓለም አንዷ አካል ናትና የእስራኤል ጋዛ ጦርነትን የየዕለት ክዋኔ ዜጎቿ እየተከታተሉት ነው፡፡ የአገራችን ሚዲያዎችም በየራሳቸው መንገድ በየዕለቱ የሚዘግቧቸውን እየሰማን፣ እያየንና እያነበብን ነው፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ የጦፈ የዓለማችን ቀዳሚ ዜና መሀል፣ በኢትዮጵያ የተሰማው አንድ ዜና ግን ዓለም እያወራበት ያለውን ጉዳይ ተሻምቶታል፡፡ ይህ ዓለም የሚነጋግርበትን ትልቅ የጦርነት ዜና በኢትዮጵያውያን ዘንድ ደረጃውን ያስቀለበሰው ዜና ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹የቀይ ባህር ጉዳይ እኛም ያገባናል፤›› ብለው ብቅ ማለታቸው ነው፡፡ ለዓመታት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ታፍኖ የቆየውን የወደብ ባለቤትነት ጉዳይ፣ ልንነጋገርበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ማስታወሳቸው ነው፡፡ የወደብ አስፈላጊነትንና በታሪክም ኢትዮጵያ ከወደብ ተጠቃሚነቷ አንፃር የነበራትን መብት በማጣቀስ ጭምር ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡበት ይህ ጉዳይ፣ በየትኛውም መንገድ ቢታይ ለኢትዮጵያውያን ከእስራኤልና ሐማስ ጦርነት በላይ ቢሆን ሊገርም አይችልም፡፡
‹‹በሰላማዊ መንገድ ከቀይ ባህር ዳርቻ ኢትዮጵያ የምታስተዳድረው የገቢና የወጪ ንግድ ማቀላጠፊያ ሥፍራ ሊኖራት ይገባል፤›› የሚለውን ምልከታ በቅን ልቦና ለተረዳው፣ አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ሲያስነሳም በጉዳዩ ላይ እንምከር ብለዋል፡፡ መቼም ለእኛ ከዚህ በላይ የዜና ርዕስ የለምና ሁሉም ወገን ራሱ መንገድ ሰፊ ትንታኔ የሚሰጥበት የመሆኑ ሚስጥርም ወደብ ጉዳይ በእርግጥም አንገብጋቢ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ አጀንዳ ምናልባትም በተከታታይ ብዙ የሚባልበት እንደሚሆንም ይታመናል፡፡
በዓለም ላይ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ወደብ የሌላት ትልቋ አገር ኢትዮጵያ እንደመሆኗ ወደብ ይኑረን ማለት ይገባል፡፡ ከሕግም ሆነ በአጠቃላይ የወደብ ተጠቃሚነት የሚያስችላት ብዙ ዕድሎች እንደነበሩም ከማንም የሚሰወር አይደለም፡፡ ይህንን ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምበት ሳንችል መቆየታችንም፣ እየከፈልነው ያለው እጅግ ከፍተኛ ዋጋ አስቆጭቶ የወደብ ጉዳይ በዚህ ዘመን አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ አግባብ ነው፡፡ ማንም እንደማይክደውም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና በቆየችበት ጊዜያት ምን ያህል ወጪ እንዳወጣች አገልግሎቱን ለማግኘት ዜጎቿ የከፈሉትና እየከፈሉ ያሉት ዋጋ የሚገባቸው አልነበረም፡፡
የወደብ ባለቤነት ጉዳይ ከአገር ህልውና ጋር ጭምር የተያያዘ ነው፡፡ ሌላ ሌላውን ጉዳይ ትተን የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ የምትጠይቀው የወደብ አገልግሎት ክፍያ ባይኖር ወይም ባነሰ ዋጋ አገልግሎቱ ቢገኝ፣ ምናልባትም የኢትዮጵያ አሁን ያላት ኢኮኖሚያዊ አቋም በእጅጉ በተቀየረ ነበር፡፡
ዛሬ በዋጋ ንረት የሚሰቃየው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ የምሬቱ ምንጭ ወደብ አልባ ሆነን መቆየታችን ስለመሆኑ በቁጥር ሊገለጽ የሚችል ብዙ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ በተለይ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ ግዥ የምትፈጽም አገር፣ በእያንዳንዱ ምርት ላይ የሚከተለው የወደብና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዋጋ፣ ለዋጋ ንረት ምክንያት ስለመሆኑ መሰመር አለበት፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ለወደብ የሚከፈለው ክፍያ ቁጥር አንድ የአገሪቱ ወጪ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የወደብና የሎጂስቲክስ አገልግሎት መቀነስ የዋጋ ንረት እንዲረግብና ኢኮኖሚው እንዲፍታታ እንደሚያስችል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡
ስለዚህ ለወደብ አገልግሎት የምንገፈግፈውን የአገር ሀብት ለመቀነስ፣ ከተቻለም ለማስቀረት ‹‹ወደብ ያስፈልገናል›› የሚለውን አጀንዳን ይዞ መነሳት ምንም ክፋት የለውም፡፡ ትክክል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን አጀንዳ ያነሱት በአገር ውስጥ በርካታ ሊፈቱ የሚገባቸው ጉዳዮች ባሉበት ወቅት ስለመሆኑ አይታበልም፡፡ ብዙ ሊመለሱ የሚገባቸው የሕዝብ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ያሉባቸው ወገኖች መኖራቸውም አይካድም፡፡
ከሰሞኑ ሲንሸራሸሩ ከነበሩ አንዳንድ ትንተናዎች መረዳት የሚቻለው፣ ‹‹በዚህ ወቅት አጀንዳው ለምን ተነሳ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን የያዙ ናቸው፡፡ ‹‹ስንት ችግር ባለበት አገር ይህንን የተዳፈነ እሳት መቀስቀስ አያስፈልግም›› በማለት በድፍረት ሲናገሩ የተደመጡም አሉ፡፡ በአገራችን መንግሥት ሊመልሳቸው የሚቻሉ ብዙ ጥያቄዎች ያሉበት ቢሆንም፣ እንዲህ ያሉ ሁሉንም ወገን ሊያስማሙ የሚገቡ ነገንም ታሳቢ ያደረጉ አጀንዳዎችን ግን በጥርጣሬና በተቃውሞ ስሜት ከማጣጣል፣ ‹‹እንዴት ሊሳካ ይገባል?›› የሚለውንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
እንደተባለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለባቸውን ተጠያቂነት ለማስቀልበስ ከሆነም ይህንኑ ጉዳይ እንዲያብራሩ ቀጣይ ዕቅዱንም በተመለከተ በግልጽ አሠራር እንዲኖር መሞገት እንጂ፣ የኢትዮጵያ ወደብ እንዲኖራት እንሞክር፣ ሲባል መቃወም አግባብ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሌላው ቢቀር የወደብ ወጪያችን እንቀንስ ሲባል፣ ጉዳዩ የአገር ህልውና መሆኑን ስቶ በተፃራሪነት መቆም እየፈተነን ያለውን ድህነት ታቅፈን እንቆይ፣ ተወዳዳሪነት በጠነከረበትና መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ጣራ እየነኩ ባስቸገሩነት ዓለም ላይ የሚቀርቡ አማራጮችን መቃወም ነገን ያለማሰብ ጭምር ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ብዙ የማንስማማባቸው ጉዳዮች ቢኖሩም፣ አገርን ሊጠቅም የሚችል እንዲህ ያሉ ወሳኝ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጉዳዮችን በሰከነ አዕምሮ ማሠላሰልና እንዴት ማሳካት እንደሚቻል ማሰብን ማስቀደሙ ጥቅሙ ይበዛል፡፡ ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በመነሳቱ ብቻ ‹‹ይህማ ነገር አለው›› ብሎ፣ መነሳት ትክልል አይደለም፡፡
ደግሞም ‹‹እንወያይበት›› ነው የተባለው፡፡ ‹‹በጦርነት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ የወደብ ባለቤት እንሁን ለዚህ እንምከር፣ አማራጮችን እንይ፤›› ሲባል ዘሎ ለተቃውሞ መነሳት ግራ ያጋባል፡፡ ቢያንስ እንደ ዜጋ ሁላችንንም የሚጠቅም ጉዳይ ላይ እንዴት መስማማት ያቅተናል?
‹‹ጦርነት ውስጥ ሆነን፣ ዘረኝነት በገነሠበት አገር ይህ እንዴት ይሆናል?›› ከማለት፣ በእርግጥም ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው መነጋገር ክፋት የለውም፡፡ ምናልባትም እኮ ይህ አጀንዳ በጋራ አሰባስቦን፣ ሌሎች ችግሮችንም ለመፍታት ዕድል የሚሰጥ ሊሆን ይችላል፡፡ አጀንዳው ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጻሚያ እንዳይውልም ማድረግ ይቻላል፡፡ አንደኛው ችግራችን ሳይቀረፍ ሌሎች አገራዊ ጠቀሜታቸው የጎሉ አጀንዳዎች መነሳት የለባቸውም የሚለው አስተሳሰብም በምንም ሁኔታ ሊደገፍ አይችልም፡፡ ችግር አለብኝ ያለ ነጋዴ ይህ ችግር ካልተፈታ አልነግድም አይልም፡፡ ጦርነት አለ ተብሎ ሥራ አይቆምም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ካልተሻሻለ አላርስም፣ አላስተምርም፣ አልነግድም፣ አልሸምትም አይባልም፡፡ ብዙ ችግሮችን ይዘን ነው ስንጓዝ የቆየነው፡፡
የህዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለው አገሪቱ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ባሉባት ወቅት ነው፡፡ ሕዝብ የሆዱን በሆዱ ይዞ አገራዊ ጠቃሚነቱን አስቦ፣ ግድቡን ማስገንባት ችሏል፡፡ በወቅቱ ‹‹በአገር ውስጥ ያለው ችግር ሳይፈታ ወደ እዚህ ግንባታ መግባት የለበትም›› ብሎ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ህዳሴ ግድብ ባልነበረ ነበር፡፡
ስለዚህ ችግሮች እንዲፈቱ እየተሟገትን ለዘላቂያዊና አገራዊ ጥቅም የሚበጀንን ደግሞ በስምምነት ማራመድ ያስፈልገናል፡፡ የሚያስማማ አጀንዳ የሚኖረን የውጭ ጠላት ሲመጣ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ፊት ለፊት ያሉ ተግዳሮቶች የበዙ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን አንገብጋቢ ጥያቄ ሊመልስ፣ ሐሳብ ሲቀርብ ሐሳቡን ከአገር ጥቅም ጋር አለማያያዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ሕዝብ እየበዛ ኑሮ እየከበደው ሲሄድ ብዙ አማራጮችን መፈለግ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ ዕርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ሰሞነኛው ‹‹የወደብ ያስፈልገናል›› አማራጮችን ማየት ግድ እያለ ነው ሲባል ጉዳዩን የብልፅግና አድርጎ መመልከትም አይገባም፡፡ ብልፅግና ባይኖርም አገር ለማስተዳደር ዕድል የሚያገኝ ፓርቲም ቢሆን፣ የአገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይህንኑ አጀንዳ ማቀንቀን ግድ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡
ስለዚህ ቢያንስ በቀላሉ ሊያስማሙን የሚችሉ ጉዳዮችን ላይ መነጋገር፣ ከዚያም ተፈጻሚ እንዲሆን የራስን አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳት ለሌሎች ችግሮቻችን የመፍትሔ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚሰጡ መረጃዎች ከስሜታዊነት የነፃ ሆኖ፣ በባለሙያዎች የተደገፈ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መረጃዎቹ እየተሰጡ ሕዝብ እንዲመክርባቸው በማድረግ አጀንዳውን ሕዝብና አገር የሚጠቀምበት እናድርገው፡፡