Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከወለድ ነፃ አገልግሎት ያስጀመረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወለድ ነፃ ቦንድ ለማቅረብም ዝግጅት ላይ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ብቸኛው የአገሪቱ የፖሊሲ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመጀመርያውን ከወለድ ነፃ ቦንድ ሥራ ላይ ለማዋል መዘጋጀቱንና ለከፍተኛ ፕሮጀክቶች ፋይናንስ ማቅረብ የሚያስችል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ደግሞ በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ‹‹ዲቢኢ ተዐውን›› የሚል ስያሜ የሰጠውን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ሐሙስ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም. መጀመሩን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ባንኩ ያስጀመረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሸሪዓን ሕግን ተከትሎ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንቶች ፋይናንስ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ 

ባንኩ ካስጀመረው የወለድ ነፃ አገልግሎት በተጨማሪ፣ ‹‹ሱኩክ›› የተሰኘ ለአገሪቱ አዲስ የመጀመርያ የሆነ ከወለድ ነፃ ቦንድ በማቅረብ፣ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ሀብት ለማሰባሰብ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለአገሪቱ ዕድገትና ፍትሐዊ ሀብት ሥርጨት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት የሚታመን ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሚጠበቀው ደረጃ ሳያድግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡    

በዚህም ምክንያት ሰፊ ሽፋን ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ፍላጎቱና እንደሚከተለው እምነት የሚፈለገውን የኢንቨስትመንት ፋይናንስ አገልግሎት ሳያገኝ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን አሁን መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ 

ለማሳያ የጠቀሱትም ከ18 ባንኮች በተገኘው መረጃ መሠረት፣ 200 ቢሊዮን ብር የሚገመት ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሊሰባሰብ መቻሉን ነው፡፡ ይህንን ዕድል በመጠቀምም እሳቸው የሚመሩት ልማት ባንክ ዘርፉን የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችል አሠራር ዘርግቶ ወደ ትግበራ መግባቱን አመልክተዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚያስጀምረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢንዱስትሪው ውስጥ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት በእጅጉ የሚያግዝ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ በባንኩ ዕቅድ መሠረት  ከወለድ ነፃ ፋይናንስ የሚቀርብባቸው ዘርፎችን የለየ ሲሆን በዋናነት በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በማዕድን ልማት፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርትና በአስጎብኚ አገልግሎት ለሚሠማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የባንክ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ 

ለኢንቨስትመንቱ የሚያስፈልገውን ሀብት ከማሰባሰብ አንፃርም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ባገኘባቸው ሁለት የፋይናንስ ምንጮች የሚተገብራቸው መሆኑንም በዚሁ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል፡፡ 

በተፈቀዱለት ሁለቱ የሀብት ማሰባሰቢያ ምንጮቹ ‹‹ሱኩክ›› እና ‹‹ሙደረባ›› የሚባሉ ሲሆን፣ በእነዚህ የሰበሰበውን ሀብት ኢንቨስትመንት ላይ ለማዋል ደግሞ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የኢጀራ ወይም የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ለብዙ ፕሮጀክቶች ደግሞ ሙራባሃ በተሰኘው የወለድ ነፃ አገልግሎት የፕሮጀክት ፋይናንስ ለማቅረብ እንደሚያስችለው ጠቅሰዋል፡፡ 

እነዚህን አገልግሎቶች መጠቀም በጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ በሸሪዓው የተፈቀዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ወሳኝ ልማቶችን ለማስፋፋትና ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ባንኩ የፕሮጀክት ፋይናንሲንግ በስፋት ለማቅረብ ከተያዘው የበጀት ዓመት ጀምሮ ከአቻ የውጭ የልማት ባንኮች ልምድ በመውሰድና በቂ ጥናት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የወለድ ነፃ አገልግሎቱ በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በተጨማሪ በመላ አገሪቱ በሚገኙ 100 ቅርንጫፎች የሚሰጥ ሲሆን፣ ለዚህም ራሱን የቻለ መዋቅር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ተናኘ ወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የፋይናንስ አካታችነትንና ፍትሐዊነትን ዕውን ለማድረግ ሲዘጋጅባቸው ከነበሩ አገልግሎቶች መካከል አንዱና ዋነኛው በዕለቱ በይፋ የሚጀመረው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ባንኩ ይህንን አገልግሎት ተጠቃሚ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ የአሠራር ፖሊሲዎችንና መመርያዎችን ማፅደቁንም ገልጸዋል፡፡ 

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በርካቶችን ወደ ኢንቨስትመንት የመሳብ ዕምቅ አቅም ያለው በመሆኑ፣ ከዚያም ባሻገር የፋይናንስ ተደራሽነትንና ፍትሐዊነትን በመወጣት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡  

ከዚህ በመነሳት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን አንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎቱን ለማስፋት ሁሉም ወገን ሊጥር እንደሚገባውም በመጥቀስ፣ አገልግሎቱ በደንብ እንዲስፋፋ ለማድረግ ግን ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን መከወን የሚጠይቅ ስለመሆኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  

ከዚህ አንፃር በተለይ የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ አካላት ከባንኩ ጋር እንዲሠሩ ጥሪ ቅርበዋል፡፡ በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹አንጋፋና ብቸኛው የፖሊሲ ባንካችን በሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መጀመሩን ትልቅ ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትንና አካታችነትን ለአንድ አገር ሕዝቦች ፍትሐዊ ዕድገት ጠንካራ መሠረት የሚጥል እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስቴር ደኤታው፣ ‹‹መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በፋይናንስ ዘርፉ ላይ በወሰዳቸው ጠንካራ ዕርምጃዎች አበረታች ውጤቶች ሊመዘገቡ ችለዋል፤›› ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል በዋናነት ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ራሱን ችሎ እንዲሰጥ ለማስቻል የተካሄዱት የአዋጅ ማሻሻያ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

በፋይናንስ አካታችነት ላይ የተሠሩ እነዚህ የሪፎርም ሥራዎች በዓለም አቀፍ ማኅረበሰብ ዕውቅና እንዲኖራቸው ሆኗል ያሉት ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጋር የተገኘውን ዕውቅና ነው፡፡ ይህንንም ‹‹ባፈለው ዓመት አገራችን ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒትራችን በኩል የ2022 የዓለም አቀፍ የእስላም ፋይናንሲንግ ሽልማት ማግኘቷ ተጠቃሽ ነው፤›› በማለት በዘርፉ እየተገኘ ነው ያሉትን ውጤት አመላክተዋል፡፡ 

መንግሥት የፋይናንስ አካታችነትን ዕውን ለማድረግ ካለው ፅኑ ፍላጎት አንፃር እየሠራባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዋነኛው ይህ አገልግሎት ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ የሚሰጥ ሲሆን፣ አገልግሎት ከቴክኖሎጂ ጋር ተጣጥሞ ሲሠራበት ደግሞ ከፋይናንስ አካታችነት ባለፈ ለአገር ኢኮኖሚ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለየት ብሎ ከሚታይባቸው ባህሪያቱ አንዱ ከወለድ ነፃ ቦንድ ‹‹ሱኩክ›› በመዘጋጀት ሀብት የማያሰባስብ መሆኑ እስካሁን ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥን በተለየ ሁኔታ ይዞ መምጣቱን አመልክቷል፡፡ እንዲህ ያለው አገልግሎት ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሀብት ለማሰባሰብ ከማስቻሉም በላይ፣ በተለይ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ከወለድ ነፃ ያሰባሰቡትን ተቀማጭ ገንዘብ ቦንድ እንዲገዙበት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹትም፣ በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ በቁጠባ የተሰባሰቡት ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ለብድርና ለፋይናንስ ያልዋለ በመሆኑ፣ ባንኩ የሚያዘጋጀው ቦንድ ይህንን የታቀደ ገንዘብ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲውል የሚያስችል መሆኑን ነው፡፡ ሱኩክ የሚል መጠሪያ ያለው የሸሪዓ መርሆዎችን የተከተለው ይህ ቦንድ፣ የተለያዩ አሠራሮች ያሉት በመሆኑ ይህንን አሠራር በመተግበር ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ደረጃን ከፍ ማድረግ የሚችል ስለመሆኑም ከተሰጠው ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ሱኩክ በተፈቀዱ ንብረቶች ላይ ባለቤቶች የሚኖራቸው ያልተከፋፈለ እኩል የባለቤትነት ወይም ኢንቨስትመንት የያዘና እኩል ዋጋ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ወይም መዋዕለ ንዋይ ስለመሆኑ ሱኩክን በተመለከተ የተዘጋጀ የባንኩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ሱኩክ ከቦንድ ጋር ተመሳሳይ የሆነና ከእስልምና ሕግጋት ጋር የሚጣጣም የፋይናንስ ሰነድ መዋዕለ ንዋይ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ኢዮብ (ዶ/ር)፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጠቀሜታ በብዙ መንገዶች የሚገለጽ ስለመሆኑ የጠቀሱ ሲሆን፣ ይህ ዕድል ሳያገኝ ቆይቶ የነበረውን የኅበረተሰብ ክፍል ወደ ኢንቨስትመንት የሚያመጣ በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው የፋይናንስ አገልግሎት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችና ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ አራት ባንኮች በጥቅል ካሰባሰቡት ገንዘብ ውስጥ ፋይናንስ ያደረጉ (ያበደሩት) ገንዘብ ከ40 በመቶ የማይበልጥ መሆኑ ይነገራል፡፡ አሁን ልማት ባንክ ይዞት የቀረበው አዲስ አገልግሎት የተከማቸ ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብን ወደ ኢንቨስትመንት ለመለወጥ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ካሰባሰበው አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች