Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራዎቹና ሌሎች አገልግሎቶቹ ዘመን ባንክን ለማስተዋወቅ ተስማማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ የማስታወቂያ ፓኬጆች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመን ባንክን ለማስተዋወቅ በዓይነቱ ልዩ ነው የተባለ ስምምነት ተፈረመ፡፡ 

ዘመን ባንክና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል የተደረገው ይህ ለየት ያለነው የተባለው የማስተዋወቂያ ስምምነት ለአንድ ዓመት የሚቆይ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንዲህ ያለውን የማስተዋዋቅ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለው ስምምነት የመጀመርያ ስለመሆኑም ባለፈው ሐሙስ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል፡፡ 

በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት አየር መንገዱ በሁሉም የበረራ አገልግሎቶቹ ዘመን ባንክን የሚያስተዋውቅ ሲሆን፣ በበረራዎቹ መዳረሻ አገሮች በሚገኙ ቢሮዎች ጭምር ዘመን ባንክ ለማስተዋወቅ ስምምነት ፈርሟል።

አየር መንገዱ በበረራ ወቅት ለመንገደኞቹ በሚያዘጋጃቸው የመዝናኛ ፕሮግራሞች፣ በሰላምታ መጽሔትና በመሳሰሉት ላይ ዘመን ባንክን የሚያስተዋውቁ መረጃዎች እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ 

በአየር መንገዱ ተርሚናልና መሰል ቦታዎች ላይም የዘመን ባንክ ማስታወቂያ ለአንድ ዓመት የሚያስተዋውቅ መሆኑን የሁለቱ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የአየር መንገዱ በተለያዩ መንገዶች በሚያዘጋጃቸው የበረራ ቲኬቶች ላይም የዘመን ማስታወቂያን እንደሚያካትት ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ዘበነ እንደገለጹት ‹‹ይህ ስምምነት ወደ አገራችን የሚመጡ ኢንቨስተሮች የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አገጣሚ ስለሚኖር በዚሁ እንዲያውቁት ማድረግ ጭምር የባንካችን ገጽታ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ያበረክትልናል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት የአየር መንገዱ ኮሜርሻል ኦፊሰር አቶ ለማ ያደታ በበኩላቸው የባንኩን አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ለማስተዋወቅ ይህ ስምምነት የሚያግዘው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡና የሚተላለፉ ኢንቨስተሮች ይህንን ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም የገለጹት አቶ ለማ፣ ‹‹የባንኩን ተደራሽነት ለማስፋት ዕድል ተጠቅመንበት ዘመን ባንክን እንደ አንድ ድርጅት ኢትዮጵያን ደግሞ እንደ አገር እናስተዋውቃለን፤›› ብለዋል፡፡ ስምምነቱ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስት ወይም ለተለያዩ ንግዶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች የባንክ አገልግሎት የግድ ስለሚሆን ይህ ማስታወቂያ ስምምነት ከዚህ አንፃር ለዘመን ባንክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ 

በሁለቱ አገር በቀል ከኩባንያዎች መካከል የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ መልካም ዕድል የሚያየው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ለማ፣ እንዲህ ያለው ስምምነት አየር መንገዱ የሚሠራውን ሥራ የሚያሰፋለትም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎትና በመዳረሻ አገሮች ባሉት ቢሮዎቹ በተጨማሪ በሆስፒታሊቲ (የሆቴል መስተንግዶ) ዘርፍ ላይም የተሰማራ በመሆኑ ዘመን ባንክን የማስተዋወቅ ስምምነቱ እነዚህ አገልግሎቶቹንም ጭምር የሚያካትት ይሆናል። በዚሁ መሠረትም አየር መንገዱ በበረራ አውሮፕላኖቹና በመዳረሻ አገሮች በተጨማሪ ባንክ በአየር መንገዱ ሆቴል ለሚስተናገዱትም ዘመን ባንክን እንደሚያስተዋውቅ ጠቁመዋል፡፡ 

‹‹አየር መንገዱ በመላው ዓለም በሚያደርጋቸው በረራዎች አማካይነት መንገዶኞች ስለ ዘመን ባንክ የሚያውቁበትን ዕድል የሚሰጥ ነው፤›› ያሉት አቶ ደረጀ እንዲህ ያለው ስምምነት ባንኩን በከፍተኛ ደረጃ በማስተዋወቅ ትልቅ ዕገዛ እንደሚኖረው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

‹‹በመላው ዓለም ወደ 131 መዳረሻዎች ያሉት በመሆኑ በእነዚህ መዳረሻዎች በሙሉ ስለዘመን ባንክ እንድናገር ዕድሉ ተሰጥቷል፤›› ያሉት አቶ ለማ ለመንገደኞቻችን ይህንን አማራጭ ብናስተዋውቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት 13.9 መንገደኞች አጓጉዟል፡፡ በ2035 ይህንን ቁጥር 67 ሚሊዮን ለማድረስ ነው፡፡ ይህንን ግብ ለማሳካት ደግሞ የፋይናንሻል አማራጭ ተገቢነት ያለው በመሆኑ የሁለቱ ወገኖች ስምምነት ትልቅ ትርጉም ያለው ስለመሆኑ ከአቶ ለማ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ዘመን ባንክ ከአየር መንገዱ ጋር ያደረገው ስምምነት ከፍተኛ የሚባል ወጪ ቢያስወጣውም ቢሆን ባንኩን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችለው በመሆኑ ተጠቃሚ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ 

ባንኩን ተወዳዳሪ ከማድረግ አንፃር ወደፊትም ከሌሎች የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር እንዲህ ያለው ማስተዋወቂያ ስልት መጠቀሙ አጋዥ እንደሚሆንም በስምምነቱ ወቅት ከተሰጠ ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

ዘመን ባንክ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ አፈጻጸም ካላቸው የግል ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ከ 2.9 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገበ ሲሆን የተፈረመ ካፒታሉን መጠን 13.7 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቅርንጫፎች ቁጥር ደግሞ 110 ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች