Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አሁን ያለው መንግሥት ከበፊቱ እንደሚሻል የሚያሳየው ለተማሪዎች የማይመጥን ፈተና ሰጥቶ እንዲወድቁ በማድረግ መሆን የለበትም›› በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ፣በሽግግርመንግሥት ወቅት የትምህርት ምክትል ሚኒስትር፣እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለረዥም ዓመታት የሚታወቁ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ(ኢሶዴፓ) ሊቀመንበርና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከሰሞነኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የፈተና ውጤት ማሽቆልቆልና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ሲሳይ ሳህሉከበየነ (ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በሽግግር መንግሥት ወቅት የትምህርት ምክትል ሚኒስትር ነበሩ፡፡ በኋላም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በነበሩበት ወቅት የትምህርት ጥራት ላይ በተደጋጋሚ ድምፅዎን ሲያሰሙ ይታወቃሉ፡፡ ከሰሞኑ በ12ኛ ክፍል ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ውጤት መውረድ ጉዳይ እየተሰማ ያለውን ቅሬታ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር በየነ፡-ኢትዮጵያ ያፈራቻቸው ብዙ የትምህርት ባለሙያዎች አሉ፡፡ አገሪቱ በየዩኒቨርሲቲውና በየኮሌጁ ዕቅድ በማውጣትና ስለትምህርት ጉዳይም ሐሳብ መስጠት የሚችሉ በርካታ ባለሙያዎች አሏት፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ነገሩ ጦዞ ባለበት በዚህ ጊዜ አንድም ባለሙያ ሲናገርና ትንፍሽ ሲል አይሰማም፡፡ ሁሉም አድርባይ የሆነበት ጊዜ ነው፡፡ ስለትምህርት ጥራት ሲነሳ የ12ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተና ብቻ ላይ በማተኮር የሚከናወኑ ሥራዎች ሙያዊም ሳይንሳዊም አይደሉም፡፡ አገሪቱ ያፈራቻቸው ስንትናስንት ባለሙያዎችእያሉ አስተያየት የሚሰነዝር ሰው እንዴት ይጠፋል? እኔ ይህን የ12ኛ ክፍል ውጤት በተመለከተ እየተከናወነ ያለውን ነገር በአንድ ዓረፍተ ነገር ባስቀምጥልህ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ወጣት ፈተና ማለፍ የማይችል ደደብ ነው›› እየተባለ ነው፡፡ እኔ ይህ ነገር በቀጣይ የአገሪቱ ዕድል ላይ አደጋ ያዘለ ሌላ ትርጉም ያለው በመሆኑ ስለጉዳዩ ብናገር ብቁ ነኝ እላለሁ፡፡ ይህን የምልህ ለምንድነው ካልክ እኔ ከጅምሩ በተፈጥሮ ሳይንስ የመምህርነት ሙያ የሠለጠንኩና በተመራማሪነት ዕድሜን የገፋሁ፣ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በማውጣት፣ በመፈተንና በማረም ትልቅ ሚና የነበረኝ ሰው ነኝ፡፡ በተጨማሪም በሽግግሩ ወቅት የጠቅላላ ትምህርት ዘርፍ ምክትል ሚኒስትር ነበርኩ፡፡

በሽግግሩ ወቅት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ኃላፊነት ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ፖሊሲን እንዲፈተሽ በተሰጠኝ የቤት ሥራ መሠረት ፖሊሲውን በመፈተሽ፣ ለበርካታ ወራት ግምገማ አድርገንና ክፍተት ለይተን ለአዲስ ፖሊሲ ቀረፃ ሐሳብ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረግን በነበርንበት ጊዜ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጣልቃ ገቡ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር እንዴት ራሱ ገምጋሚ ራሱ አስፈጻሚ ሊሆን ይችላል በሚል ጣልቃ ገቡ፡፡ከእኛ ቀምተው በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ነው መሠራት ያለበት ብለው ወሰዱት፡፡የአገሪቱ የትምህርት ውድቀት መነሻ እንግዲህ እዚያ ላይ ነው፡፡በዚህ ውሳኔካበላሹትአንደኛው ነገር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጨረሻው 10ኛ ክፍል ነው የሚለውየፖሊሲቀረፃ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ12ኛ ክፍል የጨረሰ ተማሪ የመጀመርያ ዓመት ጨርሷልተብሎትምህርቱን ይቀጥላል፡፡የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱም በአራት ዓመት መሆኑ ቀርቶ በሦስት ዓመት ይሆናል የሚል የእንግሊዝሥርዓት ተከሉ፡፡ ነገር ግን በእንግሊዝ የትምህርት ጥራቱ ከታች ጀምሮ ስለሚሠራበት አሠራሩ የተፈለገው ደረጃ ሊያበቃ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ባለው የትምህርቱ ጥራት ቢያንስ አራት ዓመት ዩኒቨርሲቲ እንዲቆይ መደረጉ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ይህን ምሳሌ አነሳሁልህ እንጂ ጉዳዩ ብዙ ነው፡፡ ይህ ችግር ሊፈጠር የቻለው የትምህርት ሥርዓቱ በፖለቲከኞች እንጂ በባለሙያዎች እንዳይመራ በመደረጉ ነው፡፡

      ከዚህ ተነስቼአሁን ሰሞኑን የወጣውንየፈተና ውጤት ስመለከት አንድን ተማሪ ለቀጣይ የትምህርት ደረጃ ብቁ መሆኑን ለመመዘን የሚያበቃ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እነሱ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ተማሪ ኮራጅ ነው፣ አስተማሪው ሁሉ አስኮራጅ ነው፡፡ባለፈው ዓመት ያየነው ተማሪውን ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር፣ወይም ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ መውሰድ ነው፡፡ ተማሪውንም መምህሩንም፣ በአጠቃላይ ዜጋው በሙሉ እንደማይታመን የታየበት የድራማ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ፈተና በቂና ገማች አለመሆኑን ለማሳየት፣ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የልዑል በዕደ ማርያም የሙከራ (Laboratory) ትምህርት ቤት የሚባል ነበር፡፡ በዚህ የሙከራ ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪን በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ብቻ መዝኖ መግለጽ አይቻልም የሚል አንድምታ ነበር፡፡ በዚህ የሙከራ ትግበራ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ተማሪ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ሳይፈተን፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይችላል የሚል የሙከራ ማሳያ ነበር፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ተመርጠው አዳሪ ትምህርትቤት ገብተው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ሳይፈተኑ የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ተመድበው ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፣ ለሁለተኛ ደረጃ መምህርነት ይመደቡ ስለነበር በጣም ጎበዞች ነበሩ፡፡

በዚህ ዓመት ተማሪን ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል የማዘዋወሩና የማዋከቡ ጉዳይ ቀርቶ፣የአሁኑ ፈተና ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎበት እንዲፈተኑ ተደረገ ተባለ፡፡ ስንት አለፈ ስትል ከአጠቃላይ ተማሪ 3.2 በመቶ ብቻ የሚሆነው ነው፡፡ዓምና ከነበረው 3.3 በመቶ ጭራሽ በአንድ ነጥብ የወረደ ውጤት ተመዘገበ፡፡ ነገር ግን እንደጤነኛ ሰው ይጠበቅ የነበረው ካለፈው ዓመት ይልቅ በዚህ ዓመት እንዲሻሻል ነበር፡፡ እሺ እሱ ይቅር እንዲያው ‹‹ዕባብ ያየ በልጥ በረየ›› እንደሚባለው ባለፈው የደነገጠ ተማሪ እኮ ለዚህ ዓመት መጣብኝ ብሎ መዘጋጀቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የሚወራው ምንም እንደማይዘጋጁ ነው፡፡ ስለዚህ እየሆነ ያለው‹‹ላም ባልዋለችበት ኩበት ለቀማ›› ዓይነት ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ ተማሪ ማሳለፍ አይችሉም የሚባለው ነው፡፡ 43 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ እንኳ ማሳለፍ አልቻሉም ተብሏል፡፡ ይህ ለአንድ ተመራማሪ የምርምር ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እኛ ዕድሜ የሰጠን የተማርንበትን ትምህርት ቤት መለስ ብለን ስናይ እኮ በምን ዓይነት ትምህርት ቤት ነበር መሰለህ የተማርነው? በተለይ በገጠር የነበረንን አስታውሳለሁ፡፡ ሰኞ ስንገባ መቀመጫ የሌለ በመሆኑ ሳር ይዘን እንድንሄድ ነበር የሚጠየቀው፣መቀመጫ እንዲሆነን፡፡ አሁን እንዲያው የኢትዮጵያ ትምህርት ከዚያ ዓይነት ሁኔታ አልተሻሻለም? ሌላው ቢቀር ብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች ወንበርና ጠረጴዛ የላቸውም?የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚረዳ አይደለም ይህ መደላድል?በበኩሌ 1,328 ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ አላሳለፉም ብዬ ለመቀበል ህሊናዬ አይፈቅድልኝም፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንን ተማሪ ማብቃት አይችሉም?በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ልጆች ከዚህ በፊት ዩኒቨርሲቲ ገብተው ጥሩ ውጤት አላመጡም? ወደቁ አልቻሉም ብሎ በአደባባይ መሳለቅ ምን ይባላል?

ሪፖርተር፡- እርስዎ ትምህርት ላይ ሳሉምሆነ ሲባል እንደሚሰማው የቀድሞ ተማሪ የተሻለ ውጤት ነበረው፡፡ አሁን ለሚታየው ችግር መንስዔው ምንድነው የሚሉት?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ያኔ ጥቂት ነበርን፣ መምህሩም ያግዛል ተማሪውም ይተጋገዛል፡፡ እንግዲህ የድሮው ዕፁብ ድንቅ ነው ማለት አትችልም፡፡ ድሮ ትምህርት ተደራሽ አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግም ይሁን ደርግ ትምህርትን ተደራሽ ማድረጋቸው ነውር የለውም፡፡ አሁን ደግሞ የተማሪው ቁጥር በዛ፣ በመብዛቱ ደግሞ ጥራት የለውም የሚለው ሚዛን ደፋና ሁኔታውን ደበቀው፡፡ በዚህ ፈተና የወደቀው ተማሪው ሳይሆን ትምህርት ሚኒስቴርና እዚያ ውስጥ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ አደራ የተቀበሉ አካላት ናቸው እንጂ፣ የኢትዮጵያ ወጣት ሁሉም ደደብ ነው ዓይነት ንግግር ተገቢ አይደለም፡፡ በፈረንጆች አገር ቢሆን ይህ ንግግር ዘረኛ ነው ያስብል ነበር፡፡ ስለዚህ የችግሩ ምንጭ ብዙ ነው፡፡ እስኪ ትምህርት ሚኒስቴር ለስንት ትምህርት ቤትና ለስንት ተማሪዎች መጽሐፍ አቅርቦ ነው ለፈተና ያቀረባቸው፡፡ በቂ የትምህርት መሣሪያ ቀርቦ ነበር ወይ? ለምንድነው የተወሰኑ ከተማ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በተሻለ መጠን ያሳለፉት?ግብዓት ስላገኙ እኮ ነው፡፡ የማጥናት ዕድል ስላገኙ ነው፡፡ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት መጽሐፍ ሳያቀርብ፣ ጊዜውን ጠብቆ ትምህርት ሳይሰጣቸው፣ ትምህርት በውሉ ሳይማሩ ለምን እንደተፈተኑ ራሱ አልገባኝም እኮ፡፡

አንድን ተማሪ ለመፈተን ሊሸፈን ከሚገባው ካሪኩለም ምን ያህሉን ማስተማር ተችሏል ተብሎ እኮ መጠየቅ አለበት፡፡ በጦርነት ውስጥ የነበሩ ስንቱ ገብቷቸው ተማሩ? አሁን ከ50 በመቶ በላይ ያመጡ እነዚህ ብቻ ናቸው ከማለት በፊት፣ መጀመሪያከ50 በመቶ በላይ ተማሪዎች መጽሐፍ ደርሷቸው ነበር ወይ? ክፍል ገብተው ተማሩ ወይ? የሚለውን እኮ መልስ መስጠት አለባቸው፡፡ በተቃራኒው አዳሪ ትምህርት ቤት ተብሎ በቁሳቁስ እየተደገፈ ያለው ተማሪ ጥሩ ውጤት መጣለት፡፡ በዚህ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? መጽሐፍ የቀረበለትንና ያልቀረበለትን በፈተና ለመለየት እኮ ቀላል ነው፡፡ ግብዓት የቀረበላቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶችና እገሌ እያሉ የሚጠሯቸውን እኮ እንደሚያሳልፉ ድሮም እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ቤቶቹ የተሻለ ገቢ ያላቸው ወላጆችና የተሻለ ውጤት ያላቸው ልጆች የሚማሩባቸው ናቸው፡፡ የችግሩ መነሻ የግብዓት አቅርቦት ነው፡፡ ግብዓት የሌላቸውን እንዴት ደግፎ ውጤት ይስተካከል የሚለውየትምህርት ሚኒስቴር ሥራ ነው እንጂ ያላቸውማ ሁሌም አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጤቱ መውረድ የፖለቲካው ግልባጭ ነው ብሎ መወሰድ ይችላል?

ፕሮፌሰር በየነ፡-እንግዲህ እነዚህ ሰዎች ውስጣቸው ያለው በሽታ ፈንድቶ በዓይናችን ውስጥ እንዲወድቁ ያደረገው ይኼው የ12ኛ ክፍል ውጤት ነው፡፡ ይህ በደንብ መገምገም አለበት፡፡ እኔ ግን ያሳዘነኝ አንድ ጋዜጣ ላይ ተጽፎ ያገኘሁት ‹‹ዕርምጃው የአጠቃላይ ማኅበረሰብን ድጋፍና ይሁንታን አግኝቷል›› በሚል የቀረበ የጋዜጠኛ ጽሑፍ ነው፡፡ ይኼን ድጋፍ በየትኛው ጥናት አረጋገጥህ ብለህ ብትጠይቀው እኮ መልስ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ቆጥቦናአስተምሮ ልጁ ሲወድቅበት ነው ድጋፍ የሚሰጠው? አንዳንዴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትዕግሥት ይገርመኛል፡፡ ይህን ሁሉ የሚችለው ግን ቆሽቱ እያረረ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የተማሪዎች የፈተና ውጤት ላይ ከመፍረድ ትምህርት ሚኒስቴር እንደተቋም ለውጥ ያስፈልገዋል ነው እያሉ ያሉት? 

ፕሮፌሰር በየነ፡- የትምህርት ግብዓቶች በተለይም አንድም ተማሪ ማሳለፍ አቃታቸው ለሚባሉት ትምህርት ቤቶች መዳረስ አለባቸው፡፡ ሌላው ጉዳይ አንዳንድ መምህራን እኔ መፍትሔ ያለኝ እየመሰላቸው ለስድስት ወራት ለአምስት ወራትደመወዝ አልተከፈለንምእያሉ ይነግሩኛል፡፡ መምህር ማለት የመንግሥት ሠራተኛ ነው፡፡ በመንግሥት ሠራተኛ ሕግ መሠረት ደመወዝ ማለት አስገዳጅ ክፍያ ነው፡፡ ለደመወዝ የተያዘ በጀት ለሌላ ነገር አይውልም፡፡ በዓመቱ የተያዘው የደመወዝ በጀት የት ሄዶ ነው መምህራን ወጥተው እስኪጮኹ ድረስ የማይከፈለው?ይህንን ዓይነቱን አሠራር ሥርዓት አለማስያዝ ማለት ውድቀት ነው፡፡ ይኼንን አልፈው ደግሞ የራሳቸውን ቤት ሳያፀዱ ስለተማሪ ውድቀት ያወራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የመምህራን ብቃት ላይ ሁልጊዜ ጥያቄ ሲነሳ ይስተዋላል እኮ?

ፕሮፌሰር በየነ፡-መምህራን ብቃት የላቸውም እያሉ ዝም ብሎ ፍርድ መፍረድ ምን ይሉታል? ብቃት ከሌላቸው ማብቃት ነው፡፡ እኛ ስናስተምር እኮ ድሮ መምህራን የክረምት ትምህርት እየተባለ ለትምህርት ማሻሻያ ይላኩ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጥር ሲጠሩ ነው የሚሰማው፡፡ ይህ ሁሉ የሚናገረው አካል ከብት የሚጠብቅ መሰለው እንዴ? የሰው ልጅ እኮ በየጊዜው ራሱን ማጎልበት አለበት፡፡ መምህራኑ እንዲህ ናቸው ከማለት ያልከፈለውን ደመወዝ መክፈል፣ ሥልጠና መስጠት ካለበት በአግባቡ መስጠት አለበት፡፡ መምህር ገንዘብ ካላገኘ እኮ ተሸካሚ ሆኖም ቢሆን ቤተሰቡን ወደ መመገብ ይሄዳል፣ወይም መሬት ተኮናትሮ ሌላ ሥራ መሥራት ይጀምራል፡፡ በመሆኑም ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል ሪፎርም መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሪፎርም ከተማሪ ፈተና አይጀመርም፡፡ የኢትዮጵያ ወጣት ፈተና ይሰርቃል፣ ሌባ ነው የሚለውን ማረጋገጫ ለማግኘት ነው እንዴ ፈተና የሚዘጋጀው?ለውጤቱ መውረድየችግር ምንጭ ምንድነው የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶችን በብዛት መክፈት ለተደራሽነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው መንግሥት ከበፊቱ እንደሚሻል የሚያሳየው ለተማሪዎችየማይመጥን ፈተና ሰጥቶ እንዲወድቁ በማድረግ መሆን የለበትም፡፡ ለእኔ አሁንም ፈተናው የሚመጥን አይደለም፣ ሰው ያልተማረውን አይጠየቅም፡፡

ሪፖርተር፡- የሚወጣው ፈተና ለተማሪዎች የሚመጥን አይደለም ማለትም ምን ማለት ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ምን መሰለህ?ስለፈተና ውጤት ከመናገር በፊት የትምህርት ዝግጅቱከሚወጣው ፈተናው ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን፣ ፈተና አውጪዎች በቂ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን፣ፈተና ከተማሪው ጋር ፉክክር ለማድረግና እልህ ለመጋባት የሚወጣ አለመሆኑንመጀመሪያ መመርመር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የበርካታ ተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ምን ዓይነት ተፅዕኖ አለው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ለእኔ ይህንን ያህል ተማሪ በአገር ደረጃ ወድቋል ማለት አስፈሪ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከመንግሥት የመጣ ነው በማለት የተባለውን ሁሉ እንደወረደ ተማሪዎች ላይ ከማስፈጸምና የውግዘት መልዕክት እያባዙ ከመሄድ፣ቅድሚያ የችግሩ ምንጭ መለየት አለበት፡፡ መንግሥት ተማሪውንም ኮሌጁንም የጥራት ችግር እያለ በመኮነን የትም አይደርስም፣ የሚሻለው ለማብቃት መሞከር ነው፡፡ ነገር ግን ያለውን ሁሉ ቁጭት በኢትዮጵያ ወጣት ላይ እየተወጡና የማይሆን ስም እየሰጡ መፍትሔ አይመጣም፡፡ ዝም ብሎ የፕሮፓጋንዳ ሥራና መተራመስ ነው የሚሆነው፡፡ በመሆኑም አሁንም ትውልድን መቅረፅ ከሆነ ዕሳቤው የትምህርት አሰጣጡና ፈተናው መፈተሸ አለበት፡፡ አሁንም በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ አገር አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡ የተማረ የለም እየተባለ የሚፈተነውን የመጣል ዕርምጃ መዘዙ እንደአገር ከባድ ይሆናል፡፡ አሁንም መናገር የምፈልገው በተለይ ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር የትምህርት ግብዓቶችን አስፍቶ በመስጠት፣ ለመምህራን ሥልጠና በመስጠት፣ ደመወዛቸውን ቢያንስ በጊዜው በመክፈል ነው፡፡ ደመወዝ የማይችል መንግሥት መምህር ለምን ይቀጥራል? ከሰሞኑ የደወሉልኝ መምህራን ደመወዝ ስላልተከለን ንብረታችን ሸጠን ጨረስን እያሉ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት መጀመሪያ ራሱን ይለውጥ፣ ሪፎርም ያድርግ፣ የማሻሻያ ሥራ ይከውን፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የትልቅ አገራዊ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም መሪ ነዎት፡፡ ተቋሙ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት የማድረግ ዕቅድ አልያዘም?

ፕሮፌሰር በየነ፡- እኔ የችግሩ ምንጭ ነው በሚል እስካሁን በተናገርኳቸው ውስጥ ለምርምር የሚበቁ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ በዚያ መሠረት ፍተሻ ለማድረግ ሳይሆን የትኛው ነው በመረጃ የሚደገፈው የሚለውን ጉዳይ በደንብ መፈተሽ አለበት፣እኛም እናደርጋለን፡፡ እኔ አሁንም ተማሪዎች የተማሩትናየቀረበላቸው ግብዓት ከተሰጣቸው ፈተና ጋር የተመጣጠነ መሆኑን ማጤን አለብን እላለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ልጆች በትምህርት የትም አገር ሄደው ጎበዞች ናቸው፡፡ ትምህርት መቀበል እንደሚችሉ የሚታወቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተማሪዎቹ ውጤትአገራዊ ፖለቲካው የደረሰበት ገጽታ ማሳያ ሊባል ይችላል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ልጆቹ ተረጋግተው መማር አልቻሉም፡፡ ይህንን ፍርድ ከማሳለፍህ በፊት ለተማሪዎቹ የሚገባቸውን ሁሉ አቅርቤያለሁ ወይ ብለህ ራስህን መጠየቅ አለብህ፡፡ እኔ ብሆን ይህንን ያህል ሺሕ ተማሪዎች ወደቁ ብዬ ወጥቼ አልናገርም፣ አስፈሪ ነው፡፡ ምንም በመረጃ የተደገፈ አሳማኝ ነገር ሳልይዝ እዚያ ላይ ወጥቼ 43 በመቶ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ አላሳለፉም ብዬ አልናገርም፡፡ ይህንን የሚል ሰው በድፍረት ወጥቶ ከመናገሩ በፊት መጀመሪያ ፈተናውን ይመርምር፡፡ ሪፎርም እየተካሄደ ነው የሚሉን ውዥንብር ነው፡፡ አንድ ተማሪ አላለፈም ተብሎ መድረክ ላይ ወጥቶ ጀግና ጀግና መጫወት ያሳፍራል፡፡ እኛ በኩራዝ ተምረን እኮ ነው እዚህ የደረስነው፡፡ አሁን ባዶ ቤት ውስጥ ግብዓት ሳይኖር በማጎር ብቻ ውጤት አይመጣም፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እየወረደ ሄዷል በማለት ሁሉም ይናገራል፡፡ ችግሩ ያለው ግን ይህንን እንዴት እናስተካክለው የሚለው ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-ከበፊቱ ጋር በማነፃፀር ከዩኒቨርሲቲ ምረቃ በኋላ የሚኖረውን የሥራ ዕድል እንዴት ይገመግማሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ሁልጊዜም ችግርአለ፡፡ እኛ በነበርንበት በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ተምሮ የሚወጣው ጥቂትም ቢሆን፣ ሁልጊዜም ቢሆን የሚመረቀው ከሚኖረው የሥራ ዕድል የበለጠ ነው፡፡ እኔ ሁለተኛ ደረጃ ስማር ከሃረማያ ግብርና ማሠልጠኛ ኮሌጅተመርቀው በግብርና መስክ ሥራ ስላጡ ትምህርት ቤት ተመድበው ሲያስተምሩ አስታውሳለሁ፡፡ በየጊዜው ራሱን የቻለ ችግር አለ፡፡ ኢኮኖሚ ሲያድግ ይህን ማስተባበርና መምራት የሚችል አመራርና ራዕይ ያለው አካል የመኖር ያለመኖር ጉዳይ ነው እንጂ ችግር በየትኛውም ዘመን አለ፡፡ በሠለጠነው ዓለምም ቢሆን ሁለቱ ተጣጥመው እንዲሄዱ በማድረጋቸው ነው የተሻለ ነገር የሚታየው፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታውን እንዴት እየከታተሉት ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡-እንግዲህ የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ የሚነሱትን የፖለቲካ ጥያቄዎች በጥበብ፣ በአስተዋይነትና በትዕግሥት እየፈታን ካልሄድን ሁልጊዜ ካለፈው የባሰ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል እያየን ነው፡፡ መጀመሪያ እንደ መልካም ተብለው የታዩትና ማሳያ የነበሩት ቆይተው ወደ የማንፈልገው ደረጃ እየደረሱ ነው፡፡ በአማራ ክልል እያየን ያለነው ይህንን ነው፡፡ በአማራ ክልል ዜጎች በኩራትና በቁርጠኝነት ተነስተው መስዋዕትነት በመክፈልና የአገር መከላከያን በማገዝ አብረው ሲቆሙ ታይተው፣ ለአገር ዘብ ሆነው ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ ችግር መታየቱ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ለዚህም ነው መፍትሔን በትዕግሥት መፈለግ ያሻል የምንለው፡፡ አገር በእልህ አይመራም፡፡ በእልኸኝነት አንዱ አንበረክክሃለሁሌላው አልንበረከክም በሚል ስሜት የጋራ ቤትን ያፈርሳል እንጂ፣አስተውሎት ያለው መንገድ አይደለም፡፡ እንግዲህ እኔና ፓርቲዬ መልካም ጉዳዮች ለአገር እንዲበጁ ከመንግሥት ጋር እየሠራን ነው፡፡ ብዙ ችግሮች እየተፈቱ ይሄዳሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ የምክክር ከሚሽኑ በርካቶች ተስፋ የጣሉበት ተቋም ቢሆንም፣ በተቃራኒው አሁንም የኮሚሽኑን ቁመና የሚጠይቁ አሉ፡፡ ይህን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰርበየነ፡-ምክክር ላይ ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡ ምክክር ሲባል በራሱ ችግር ፈቺ ነው፡፡ አንተም ተው አንተም ተው ተባብሎ ሰው ሲሰባሰብ ብሶት ተናግሮ፣ መፍትሔና ሰላም ይወርዳል፡፡ የዚህ ዓይነት መንፈስ ይደርብን ነው የምለው፡፡ ለኮሚሽነሮቹ ጋር በቅርብ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ምን ያህሉን የኢትዮጵያ ክፍል ይሸፍናሉ? የተቆጡ አካባቢዎች ስላሉ ሥጋት አለኝ፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካባቢዎች ወደ ምክክር ለመግባት የሚያቀርቧቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ባላቸው ነገር ሁሉ ሁሉንም በአንዴ መሸፈን ባይችሉም እንኳ መጀመሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎ የቀድሞየፖለቲካ ሕይወት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችን አሁንካሉት ጋር እንዴት ያወዳድሯቸዋል? የ1960ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ ለአሁኑ ዘመን ትውልድ ሸክም ነው የፈጠረው የሚሉ ስላሉ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፡-የትውልዶች ክፍተት አለ፡፡ ሁልጊዜም አንዱ ሌላኛውን መኮነን የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ፖለቲካ ስትገባ በርዕዮተ ዓለም በሚመራ ፖለቲካና በብሶት በሚመራ ፖለቲካ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ትልቁን ሚዛን የሚይዘው የብሶት ፖለቲካ ነው፡፡ በዚህ ተበደልኩ፣ ይኼ ቀረብኝ የሚሉ የቡድን ብሶቶች የበላይነት የያዙበትና የገነኑበት ጊዜ ነው፡፡ እኔ የምመራው ፓርቲም የፖለቲካ ብሶት መጠየቂያ ነበር፡፡ እየቆየ ወደ መስመር ገባና ኢሶዴፓን በርዕዮተ ዓለም አቆምነው፡፡ በእርግጥ ሕዝቡ ብሶቱን በዚህ መንገድ መጠየቅ ካልቻለ የተደራጀ ሥርዓት በሌለበት አገር የሚወክለውን አካባቢ ጉዳይ አጉልቶ ለማሳየት ዕድል አይሰጥም፡፡ ስለዚህ እየጠነከርን ስንመጣ ሶሻል ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ነው በማለት ነው እየታገልን ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲ አደራጅተህ ርዕዮተ ዓለም ከሌለህ ብሶት ነው ሊሰማ የሚችለው፡፡ ብሶት የሚያሰሙትን መኮነን አልችልም፣ ምክንያቱም የሚያደምጣቸው ስላጡ ነው ብሶት የሚያበዙት፡፡ በእኛ ዘመን የነበሩት ፖለቲከኞች ለሕይወታቸው ሳይሳሱ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ እኛ የተረፍነው ሰፋ ያለ አመለካከት ይዘን መቀጠል አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ምሁራንም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ›› አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የውኃ ሀብት ተመራማሪ

በምርጫ 97 ጊዜ በእጅጉ ከሚታውሱት ውስጥ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የነበረው ሚና ሲሆን፣ በጊዜው የታሪክ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስብስብ ነበር፡፡ ቅንጅትን ከመሠረቱት አራት የፖለቲካ ድርጅቶች...

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...