Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ“ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል”

“ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል”

ቀን:

በአመሐ ኃይለ ማርያም

‹‹አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሥርዓት የለውም፣ ሥርዓት የሌለው ሕዝብ የደከደከ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው አንጂ የሠራዊት ብዛት አይደለም። ሥርዓት ከሌለው ሰፊ መንግሥት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሙያ ትሠራለች፤›› ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ከፍተኛ መከራ እየደረሰ ነው፡፡ በጭካኔ እየተገደሉ፣ አካላቸው እየጎደለ፣ እየተፈናቀሉና ንብረታቸው እየወደመባቸው ያሉ ወገኖች ከዚህ ሰቆቃ በፍጥነት ይላቀቁ ዘንድ መላ መፈለግ አለበት፡፡

በመንግሥት ቸልተኝነት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳትም መዘዙ የከፋ ይሆናል፡፡ ከነዳጅና ከኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች በተጨማሪ በርካታ የምግብና የፍጆታ ዕቃዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባ አገር፣ ከውጭ የምትጠብቃቸው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች፣ የኤክስፖርት ገቢዎች፣ የሃዋላ ገቢዎች፣ ብድሮችና ድጋፎች መጠናቸው ሲቀንስና ሊጣል በሚችል ማዕቀብ ምክንያት ፍሰታቸው ሲቆም ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶች አቅርቦት እያደገ ከመጣው ፍላጎት ጋር ሊመጣጠን እንደማይችል ይታወቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ተኩኖ በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግድያና መፈናቀል ካልቆመ፣ ሊያስከትል የሚችለው ጦስ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ፈጽሞ መቀጠል አይቻልም፡፡ 

ልማዳዊው የመንግሥት አሠራር በነበረበት መቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ለመሆኑ ማሳያ ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት፣ በኦሮሚያ ክልል በንፁኃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች፣ የኑሮ ውድነት፣ በተለያዩ መንገዶች የሚስተዋሉ ሌብነቶች፣ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶች፣ እንዲሁም ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ሥጋት የሚፈጥሩ ችግሮች ላይ የሚታዩ ቸልተኝነቶች ናቸው፡፡

ለዛሬ በባንኮች በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚስተዋለው መረን የተለቀቀው ሥርዓተ አልበኝነት ላይ ትኩረት ለማድረግ ተገድጃለሁ። ከኢኮኖሚው ምስቅልቅል መገለጫዎች አንደኛው የሆነው በባንኮች አካባቢ የሚስተዋለው አደገኛ ሁኔታ ፈር ካልያዘ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው አደጋ ከባድ ነውና፡፡

አገራችን በነፃ ገበያ የሚመራ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደምትከተል ስታውጅ በወቅቱ ከነበረው አንፃራዊ አቅም አኳያ ትልቅ ሊባል የሚችል ካፒታል ይዘው ገበያውን የተቀላቀሉት ባንኮች ናቸው፡፡ ባንኮቹ ኢኮኖሚውን ለመቀላቀል የወሰዱት ዕርምጃ ገበያውን ከማሳለጥ፣ የተቀየዱ የአሠራር ሥርዓቶች ከማዘመንና በተለይ ደግሞ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ የኢንቨስትመንት መስኮች የአገራችንን ኢኮኖሚ ደፍረው እንዲቀላቀሉ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የባንኪንግ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ላይ የሚጫወተው ገንቢ ሚና በሒደት እያደገ ቢመጣም፣ ራሱን በአዳዲስና በዘመናዊ አሠራር እያጎለበት አዳዲስ አገልግሎቶችን እየቀረፀ፣ ተጨማሪ ደንበኞችን በመሳብ ዕድገቱን በሚፈለገው መጠን ማመጣጠን አልቻለም፡፡

ለዚህም ምንም እንኳን የሥራው ባህሪ ቢሆንም በአንድ በኩል ብሔራዊ ባንክ ኢንዱስትሪው በሚፈልገው የዕውቀት፣ የአቅምና የብቃት ደረጃ ላይ አለመገኘትና አቅጣጫ ከመስጠት ይልቅ ክልከላና ቁጥጥር ላይ ብቻ ከሚገባው በላይ ማተኮሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮች ከባንኮቹ አመራሮችና ከአክሲዮን ባለቤቶች ጋር ባለው የትርፍ ተጋሪነትና ከተወካይ ወካይ (Agent Principal) ጋር በተያያዘ ሚናቸው ተገቢውን አገልግሎት ሰጥቶ ተገቢውን ክፍያ ማግኝት ሳይሆን፣ ወደ ስግብግብነት የተጠጋ አንዳንዴም ኃላፊነት የጎደለው ትርፍ የማግበስበስ ፋላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየተንሰራፋ መምጣቱ ከባንኮቹ የተገኘው ዕዳ ሁሉ ተጠቅመው ሕገወጥ አሠራር እንዲከተሉ አድርጓቸዋል፡፡

ባንኮች ከገንዘብና ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር ካላቸው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ቁጥጥር (Monopoly and Control) አኳያ አካሄዳቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አደገኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ (ዶላርን) በድርድር ከተፈቀደለትና ተራ ካልያዘ ደንበኛ ጋር በጥቁር ገበያ ዋጋ ተደራድሮ መሸጥና ለራስ በዶላር ላይ እስከ አሥር ብር የሚደርስ ኮሚሽን መውሰድ፣ በተለያየ መንገድ በደላላ፣ በዝምድና በወዳጅነትና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አማካይነት የእጅ መንሻነት በመቀበል የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሪ ማሸሽና ባልተቀመጠ የውጭ ምንዛሪ ኤልሲ መክፍት የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በቅርቡ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው ባንኮች እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እጅግ የዘገየና አስተማማኝ ያልሆነ የኤልሲ ክፍያ ዕዳ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ዕዳ የተከማቸው ላኪው ድርጅት ኤልሲ ከተከፈተና ዕቃውን ከላከ በኋላ ከባንኩ ጋር ባለው ስምምነት መሠረት ክፍያ ሳይፈጸምለት እስከ አንድ ዓመት ድረስ በመቆየቱ ነው፡፡ የሚያስደንቀው ነገር አስመጭው በብር የውጭ ምንዛሪውን ተመጣጣኝ ለባንኩ ከፍሏል፣ ባንኩ ተገቢውን ኮሚሽንና የአገልግሎት ክፍያውን ወስዷል፡፡ ዕቃውም ለአስመጭው ደርሷል፡፡ ለላኪው ክፍያውን የነፈገው ባንኩ መሆኑ ነው፡፡

አንድ ኤልሲ ተከፍቶለት ግብይቱ ተፈጽሞ ወደ አገር የገባ ምርት ሒሳብ መወራረድ ያለበት በአምስት ቀናት ውስጥ ነው፡፡ አሁን በብዙ ባንኮች እየታየ ነው የሚባለው ግን በአምስት ቀናት መክፈል ያለበት ክፍያ ሳይከፍል ዓመታት እያስቆጠረ እየሆነ ነው፡፡ ይህ እየታወቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ ዕርምጃ አለመውሰዱ ያመጣው ችግር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ማንኛውም ባንክ በሌለው የውጭ ምንዛሪ የሚከፈተው ኤልሲ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ክፍያ ለሚፈልገው የውጭ ኩባንያ ካልተከፈለ የአገርንም ስም ያስነሳል፣ እየተነሳም ነው፡፡

ክፍያው ሳይፈጸም ከሦስት ወራት በላይ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ምን ይጠብቅ ነበር የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባንኮች በወቅቱ ላለመክፈል ከሥር ከሥር ብዙ ኤልሲ እየከፈቱ መዝለቃቸው ዋነኛ ምክንያት ሲፈተሽ አንድ ሁለት ገፊ ምክንያቶች ልብ እንዲባሉ ያስገድዳል፡፡ ይህም ባንኮች ለከፈቱት ኤልሲ በወቅቱ ክፍያ ላለመክፈላቸው አንዱ ምክንያት የባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸው ከፍ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ ጭምር የሚሠራ መሆኑ ነው፡፡ አልሲውን በመክፈት የሚገኘውን ኮሚሽን ትርፋቸውን ለማሳደግ ይጠቁሙበታል መባሉ ለጆሮ ደስ አይልም፡፡ ለእነሱም አደጋ መሆኑን እያወቁ ማድረጋቸው ደግሞ ለምን ያሰኛል፡፡

ብዙ ጊዜ ባንኮች ወደ በጀት ዓመቱ መጨረሻ በሌላቸው የውጭ ምንዛሪ ኤልሲ ከፍተው በኮሚሽን የሚያገኙትን ገቢ እንደ አንድ የትርፍ ማሳደጊያ የሚጠቀሙበት ዋና ምክንያት ደግሞ ወደ ችግሩ ሁለተኛ ገፊ ምክንያት ይወስደናል፡፡ ለምን እንዲህ ይፈረጃሉ ከተባለም በሁሉም ባንኮች ባለአክሲዮኖች ከፍ ያለ ትርፍ አገኘን ለማለት ነው፡፡ይህ እጅግ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች በእርግጥም ትርፍ ይሻሉ፡፡ ሁሌም ግን ትርፍ ላይኖር ወይም በቂ ላይሆን ይችላል፡፡ የማንኛውም ድርጅት ዓላማ ትርፍና ትርፍ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ወሳኝ በሆነ አገራዊ ሀብት ላይ እየወሰኑ ከለላ የሚደረግላቸው ተቋማት ከትርፍ በላይ የሞራልና የሕግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ባለአክሲዮኖችም ሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ተግባራቸው ‹‹የስሙኒ ዶሮ የአንድ ብር ገመድ›› ይዞ ጠፋ ዓይነት ሥራቸው እንዳይሆን ጫናቸውን ከአገራዊ ጉዳት አኳያ መመዘን አለባቸው፡፡

በዚህ መንገድ ክፍያ በወቅቱ ባለመድረስ በላኪና በአስመጭ መካከል የሚነሱ ውዝግቦች አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በተለያየ ጊዜ ለንግድ ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ ባንክና ለመንግሥት የተለያዩ አካላት አቤት ቢባልም ባንኮቹን ሥርዓት ማስያዝ ግን አለመቻሉ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ይዋል ይደር እንጂ የአገራችንን ገጽታ ከማጥፋቱም በላይ ላኪ ድርጅትና አስመጭዎችን የሚያቆራርጥ፣ አቀባባይ ባንኮችን የሚያሳጣና የውጭ ግብይት ሥርዓታችንን ሊያዛባ የሚችል አደገኛ የስግብግብነት አካሄድ ነው፡፡

ከላይ እንዳነሳሁት የባንኪንግ ኢንዱስትሪውን የሚጎረብጡ አንዳንድ መመርያዎችና ፖሊሲዎች የመኖራቸውን ያህል የባንክ እንዲስትሪው መስመር እንዳይስትና ለአገር ውድቀት ሰበብ እንዳይሆኑ ለማድረግ፣ እስካሁን ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠሪያ ሥልት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመመርመር፣ በማዘመንና አሠራሩን በዕውቀትና በአቅም ላይ የተመሠረተ ማድረግ አለመቻሉ፣ ባንኮቹ መሠረት በሌለውና በስግብግብነት ላይ ብቻ በተንጠለጠለ የትርፍ ኅዳግ ጉጉት ላይ ተመሥርተው ተቋሙን መጫወቻ እንዲያደርጉት ከመሆኑም በላይ፣ ለናረ የግል ጥቅማቸው የአገርን ጥቅም ቀስ በቀስ በመሸርሸር አገርና ሕዝብን በሚጎዳ መንገድ ለኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል እየዳረጉን ነው፡፡

ኢንዱስትሪውን የበለጠ ጤናማ ለማድረግና የተሻለ እንዲሆን ግን አሁንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ግድ ይላል፡፡ ጊዜ የሚወልዳቸውን ችግሮች በመገንዘብ ተስማሚ የሆነ አሠራር መዘርጋት የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ ጡንቻዬን እዩልኝ ለማለት ሳይሆን፣ አግባብ ባለው ሁኔታ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር በመፈተሽ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሥራዎችን ማከናወን አለበት፡፡ይህንን ለማለት የወደድኩትና ጉዳዩን ወደ መሬት ለማውረድ የፈቀድኩት፣  ብዙዎቹ ባንኮች ለውጭ ኩባንያዎች እንዲከፍሉ ግድ የሆነባቸውን ክፍያ ባለመፈጸማቸው፣ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር መሥራት አንፈልግም እስከ ማለት የደረሱበት ሁኔታ ይሰማል፡፡ ይህ መስተካከል ካልቻለ አደጋው የበረታ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በዓለም የግብይት ሥርዓት ውስጥ የአገር ስም እየተነሳ ነው ማለት ነው፡፡ ውሎ አድሮ የሚፈለግ ምርት ወደ አገር እንዳይገባ ዕንቅፋት ይሆናልና ችግሩ ገዝፎ የማንወጣው ችግር ውስጥ ከመግባት በፊት ብሔራዊ ባንክ ሁኔታውን መርምሮ መስመር ማስያዝ አለበት፡፡አሁን ችግሩ የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ስለመሆኑ እየታየ ነውና ድብብቆሹን በማቆም ተነጋግሮ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡
ሌላው ጉዳይ ለውጭ ኩባንያዎች መከፈል ያለበት የውጭ ምንዛሪ በዘገየ ቁጥር የሚባክነው የውጭ ምንዛሪ ብዙም ሳይታሰብበት የቆየ ነው፡፡ በመከራ የሚገኝን ሀብት በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪን የሚመለከቱ ሕግጋቶቻችንን፣ ብሎም አሠራሮችን በመፈተሽ ነገሮችን ማስተካከል ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ የብልፅግና መንግሥት በባንኮች ውስጥ የሚፈጸሙ ሥርዓተ አልበኝነቶችን ችላ ያለ ይመስላል፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሪ ላይ የሚስተዋለው መረን የተለቀቀው ሥርዓተ አልበኝነት ፈር ካልያዘ፣ ባንኮቹ ባለአክሲዮኖቻቸውንና ደንበኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም ኢኮኖሚ ይዘው እንጦረጦስ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ ጀምሮ እስከ ቶጎ ጫሌ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ ድረስ የዘረጉት የውጭ ምንዛሪ አደን መረብ፣ ከጥቁር ገበያ ጋር እየተሸራረበ አገሪቱን ራቁቷን እያስቀራት ነው፡፡ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት የሚሳተፉ ባንኮችን፣ አመራሮችንና ሠራተኞችን እንዳላዩ ማለፍ ተባባሪ እንደ መሆን ይቆጠራል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ጤና ሲያጣ ኢኮኖሚው በአፍጢሙ እንደሚደፋ መገንዘብ ይገባል፡፡ መንግሥት ይህንን ሥርዓተ አልበኝነት ያስቁም፡፡ ሕዝብ አገሩ የወረበሎች መጫወቻ ስትሆን ቆሞ አይመለከትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...