Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉድርቅ የፖለቲካ ችግራችንን እንዳያባብስ ይታሰብበት

ድርቅ የፖለቲካ ችግራችንን እንዳያባብስ ይታሰብበት

ቀን:

በያሲን ባህሩ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጄንሲ ይፋ ያደረገው አንድ ቀደም ያለ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከ1900 እስከ 2009 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ዓመታት 26 ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ኤልኒኖ ድርቅ አስከትሏል። ከኤልኒኖ በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት 30 ዓመታት ተጨማሪ የድርቅ አደጋዎች በአገሪቱ ላይ ተከስተዋል። ባለፉት ስድስት ዓመታት ገደማም ቦታውና መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የድርቅና የተረጅነት ችግር ሲቀንስ አልታየም፡፡

በተለይ በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች ቦረናና አከባቢው፣ በደቡብ ክልል ኦሞ ሸለቆ አካባቢ በአፋርና ሶማሌ ክልል ጠረፋማ ዞኖች በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ እንስሳት አልቀዋል፡፡ ዜጎች ለተረጂነትና ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አሁን በምንገኝበት የቀውስና የግጭት ፖለቲካ ምክንያት መረጃው ቢድበሰበስም በትግራይ፣ በዋግህምራ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደርና አፋር ክልሎች በድርቅ ምክንያት የሰዎች ሕይወት ጭምር እያለፈ ስለመሆኑ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ አስደንጋጭ ክስተት ነው፡፡

በዚያው ልክ ደግሞ በዓለም መድረክ ላይ ቀና ብለን እንድንሄድ ያስቻሉን የበርካታ ድሎች ባለቤትም ነን። እ.ኤ.አ. በ2003 ቶጎ/ሎሜ ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስበሰባ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ የሊቢያዋ ትሪፖሊ እንድትሆን የአኅጉሩን መሪዎች ማግባባት የጀመሩት የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ፣ ‹‹አዲስ አበባ የምንሄደው ቆሻሻ ለማሽተት ነው? ስለዚህ ከቆሻሻዋ ከተማ ይልቅ ትሪፖሊ የኅብረቱ መናገሻ ልትሆን ይገባል፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በነዳጅ ዘይት ሀብት አቅላቸውን የሳቱትን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ሲከራከሩ፣ ‹‹እውነት ነው ከተማችን ቆሻሻ በዝቶባት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አገራችን ቆሻሻ ታሪክ የላትም፤›› ሲሉ መመለሳቸውን ስለፀረ ድህነት ዘመቻችንና የቆሸሸ ታሪክ ባለቤት ላለመሆን የተከፈለውን ዋጋ ለማስታወስ ይረዳ ይመስለኛል።

አሁን ይህንንና ቀና ያደረገንን የቀደመ ስማችንን ለማስመለስና ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመሸጋገር በሚያስችለን የለውጥና የብልፅግና ጉዞ ላይ መገኘት ሲገባ በግጭት፣ በጦርነትና በሁከት ላይ መሆናችን የሚያስቆጭ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በተለመደው የድርቅና የኢሊኖ አዘሪት የሚከሰተውን የምግብ እጥረት በውጭ ዕርዳታ እንኳን ለመሸፈን እንዳይቻል መንገዶች መዘጋታቸውና በዕርዳታ ማከፋፋሉ ሥራም ላይ የከፋ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለ መነገሩ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ስለመገኘታችን አመላካች ናቸው፡፡

ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊያን ትግል የምናደርገው ከድህነት ጋር ይመስል ነበር። ድህነትን ለመታገል ደግሞ አስፈላጊው ሥራና የሥራ ተነሳሽነት ብቻ ነው። ጠላታችን ያለው እዚሁ ጉያችን ሥር ነው ሲባል የነበረውም በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር የውስጥ ችግራችንን የለየም ነበር። የቀደሙ አባቶቻችን ግን ከውጭ ጠላት ጋር በፅናት ተፋልመውና የሕይወት መስዋዕትነትን ከፍለው ለዚህ ዘመን አብቅተውናል። እንዴት ጎዶሏችንን እየሞላን የነበረችን እንጥፍጣፊ ተስፋ እናጣለን ነው የቁጭት ማጠንጠኛው፡፡

በእውነቱ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ ጫፎች ድረስና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚገለጹበት ስያሜ የአንድነትና የጀግንነት መገለጫ መሆኑን መዘንጋት አይገባንም ነበር፡፡ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፆታ፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ የጋራ በሆነው ጠላታቸው ላይ ድርድር የማያውቁ መሆኑንም ስለፀረ ድህነት ዘመቻው ማስታወስ ተገቢ ነው። እርግጥ ከምገኝበት ወቅት አንፃር ይህ እውነት አለ ወይ ነው ቁምነገሩ፡፡

ድህነት ከሁሉም የከፋ ጠላት ነው። ይህች አገር የኢትዮጵያዊያን የጋራ ቤታቸው በመሆኗም በሚገጥማቸው የጋራ ጠላት ላይ ልዩነቶቻቸው ትዝ ሊላቸው ባልተገባ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ ቀድሞው ጊዘ በመነጋገር መፍታት የሚችሉ ችግሮችን ሁሉ በማድበስበስና በማካረር መድፍና ጦር መስበቅ ፋሽን ሆኗል፡፡ ጋሻና ጦር ለማያስፈልገው የፀረ ድህነት ዘመቻ መነሳት ሲገባ፣ በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት አገር እየደቀቀች፣ ዜጎችም ለተደራራቢ ችግሮች እንዲጋለጥ እየተደረገ ነው። ዕውን የአሁኗን ትግራይ ያየ በጦርነት ይጫወታል?

አሁን ላይ በግጭትና አለመግባባት ምክንያት አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ሙሉ ትኩረቱን በድህነት ዘመቻና ምርታማነት ላይ እንዲያደርግ ማነሳሳት አልተቻለም፡፡ እጅ እግርን ከዶማና አካፋ ጋር ማስተሳሰርና በየመስኩ ውጤት ለማምጣት መነሳት ነበር ተመላላሹን ድርቅና ረሃብ ሊያስወግደው የሚችለው፡፡ ግብዓትና ምርጥ ዘርን ለአምራቹ ማቅረብም ሆነ ምርትን ወደ ገበያ ማውጣት የቀለለ ሥራ አልሆነም፡፡

ይኼ ደግሞ ካለመደማመጥና ካለመስማማት ብቻ ሳይሆን በክፉውም በመልካሙም አንድ ካለመሆናችን የሚመጣ ቀውስ ነው፡፡ ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ድል በመላው ዓለም አንፀባራቂ ሊሆን የቻለው፣ በጠንካራ አንድነት ለአገር ራሱን አሳልፎ በሰጠ ጥቁር ሕዝብ የተገኘ የመጀመሪያው ድል በመሆኑ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊነት ታላቅ መስዋዕትነት የተከፈለበት የጋራ እሴት ነው የሚባለው፡፡ አሁንስ ነው ጥያቄው፡፡

በዚህ ዘመን ከመጠን በላይ ኢትዮጵያዊነትን የሚሸረሽሩ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ የትናንቱን የሕዝባችንን የአገር ፍቅርና ታላቅ የአርበኝነት ስሜት የሚያደበዝዙና ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ማንነት ላይ ብቻ በመንጠልጠል ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ሞልተዋል፡፡ በብሔር ፖለቲካው መዘዘ አስፈሪ መንደርተኝነት የሥጋቱ ሁሉ ምንጭ እየሆነ የተዳከመ አገረ መንግሥት ባለቤት አድርጎናል፡፡

ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ታጋሽነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ርኅራኄ፣ ጀግንነት፣ መከባበር፣ ወዘተ. ያሉበት ትልቅ የጋራ እሴት መሆኑ ከቶም ሊዘነጋ ባልተገባ ነበር፡፡ አገር እየመራ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓቱ ጭምር ኅብረ ብሔራዊ አንድነትንና መደጋገፍን የሚያጠናክር መንገድ ባለመከተሉ (አሁን አሁን እየተባባሰ ያለው የእኔ የእኔ ማለት፣ ራስ ወዳድነትና መገፋፋትም ስለሆነ) ድርቅን ለመሰሉ የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እየተገኘ አይደለም፡፡

ያ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ አገሩንና ወገኑን ማስቀደም አለበት የሚባለውም፣ አንዱ ለሌላው ችግር መፍትሔ መሆን ስላለበት ነው፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ልዩነቶች ቢኖሩት እንኳን ከልዩነቶቹ ይልቅ ልክ እንደቀደመው ለአንድነቱ ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑም መዘንጋት አይገባም፡፡ በአንዱ አካባቢ የሚስተዋልን ድህነትና ችግር ሌላው እንደ ራሱ ተሰምቶት ለማገዝ የሚችለው እውነተኛ መተሳሰብና አብሮነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ መንግሥትም ከምንም ተግባር በፊት የሕዝብን ሕይወት ይታደግ፣ ንፁኃንን ከውድቀት ያትርፍ እላለሁ፡፡

ይህች አገር ከዚህ በኋላ በዓለም ፊት የምትዋረድ ከሆነ ሰላምና ደኅንነቷን አናግታ ልትተራመስ፣ ብሎም በዚሁ ምክንያት የሚባባሰው ድህነትን ማሸነፍ ካቃታት ብቻ ነው። ድህነቷን በጋራ ታግለው ከላይዋ ላይ ከማራገፍ ይልቅ በትንሽ በትልቁ ወደ ግጭት የሚገቡና ከሰላማዊ ውይይት ይልቅ ጦርነትን አማራጭ ያደረጉ ኃይሎች የጀመሩት ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የማበር ድርጊት የክህደት የመጨረሻው ጣሪያ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ መወገዝ አለባቸው፡፡ በአገርና በኢትዮጵያዊነት ቀልድ የለም፡፡ መንግሥትም ወደደም ጠላም የሰላምን አማራጭ ሊመለከት ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት መከበር አለበት ሲባል ለአገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ በክፉ ጊዜ ደራሽ የሆኑና እንደ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ለአገራቸው ቀናዒ የሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው፡፡ ለዘመናት በላይዋ ላይ ሲጋልቡ ከኖሩት ጦርነት፣ ድህነት፣ በሽታ፣ ማይምነት፣ ኋላቀርነትና ተስፋ መቁረጥ ጋር ተፋላሚ የሚሆኑ ዜጎች ያስፈልጉናል ማለት ነው። ታዲያ አሁን እንዴት ወደ ትርምስና ውድቀት አመራን ማለትና ለምን ተሳነን መባልም አለበት፡፡

ባለፉት ዓመታት የተያያዝነውን የፀረ ድህነት ዘመቻ እየተፈታተኑብን ከሚገኙ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች መካከል ድርቅ የመጀመሪያውን ረድፍ እየያዘ ነው። ስለሆነም ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ ሲባል ከሚደረጉ ኋላቀር አስተሳሰቦችና አንድም ዕርምጃ ከማያራምዱ ድርጊቶች በመላቀቅ፣ ለመፍትሔው መሥራትና ለጊዜውም ቢሆን መደጋገፍ ዋነኛው ሥራችን እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋናነት ከግጭትና ከትርምስ ወጥቶ መነጋገር ያስፈልጋል፣ የግድም ነው፡፡ ለምነን እንኳን ወገን ለማትረፍ አገርን መተላለፊያ አሳጥተን ምን ተስፋ ሊኖር ይችላል?

የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን ይዞ መንግሥት የመሠረተው ብልፅግና፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሒደት ውስጥ ግንባር ቀደም እንደሚሆን በርከት ያሉ ተስፋዎችን ሰጥቶ ነበር፡፡ በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና የዓለማችን ዳፋ በተደጋጋሚ ለሚከሰት ድርቅና በዚህም ዜጎቿን ለቸነፈር የአገሪቱን ኢኮኖሚም ለከባድ ፈተና እየዳረገብን ቢሆንም፣ ሙሉ ትኩረታችን ልማትና ዕድገት ላይ አለመሆኑም የፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም።

በእርግጥም ጨርሰን ማስወገድ ባይቻለን እንኳ ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣን ክስተትና ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው፣ ለአየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋውን ያሳረፈው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድህነት ጎጆውን በሠራባቸው አገሮች ላይ ሲሆን፣ በተለይ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ በመሠረቱ አገሮች ላይ መሆኑን ዓለም በተገነዘበበት ጊዜ ወደ መፍትሔው መሮጥ እንጂ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ ግጭትና ትርምስ ላይ መሆን አልነበረበትም።

የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባወጣው መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት ከ5.6 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን አስታውቋል። ነገር ግን ይህ አኃዝ ከፍ ሊል እንደሚችል ደግሞ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች ተናግረዋል። በተለይ ግጭት በበረታባቸው በአማራ፣ በትግራይና በአፋር አካባቢዎች መረጃዎች በተጨባጭ ባለመውጣታቸው እንጂ በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶች ስለመከሰታቸው የሚጨነቁ በርክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች፣ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በአፋር ክልልም ድርቁ ሊከፋ እንደሚችል ግምቶች እንዳሉም ለጋሽ ድርጅቶች ሳይቀሩ አስረድተዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል (በአሁኑ ወቅት ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሃብ ሥጋት የተጋለጠበት ክልል ነው) እና በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አርብቶ አደር አካባቢዎችም የድርቅ ሥጋቶች አሉ፡፡ እነዚህ ቀላል የማይባሉ አደጋዎች መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እያስተባበረና የአቅሙን እያደረገ፣ ለጋሽ ድርጅቶችም በተለመደው የድጋፍ ዑደታቸው ካላገዘ ፈተናው ሊበረታ ይችላል፡፡

በቅርቡ ይፋ በሆነ የዓለም ሚዲያዎች መረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ አጎራባች በሆኑት በሶማሊያ፣ በኬንያና በደቡብ ሱዳን ድርቅ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን በሶማሊያ ወደ 200 የሚጠጉ ዜጎች ሞተዋል። በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳንና ደቡብ ሱዳንም ደግሞ ድርቁ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን አውጀዋል። እነዚህ አጎራባች አገሮች በተለይም ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ከድርቁ በተጨማሪ ባለባቸው የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በርካታ ዜጎቻቸው እግራቸው ወደ መራቸው የሚሰደዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያና ኬንያን ደግሞ የመጀመሪያ መጠጊያቸው አድርገዋል። በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው መረጃ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሱዳን ስደተኞች ሰሜን ጎንደር ከተጠለሉበት ጊዘያዊ ካምፕ ጥይት ቢገድለን ይሻላል ብለው ወደ ኦምዱርማን የተመለሱት ረጂ በማጣታቸው ነበር፡፡

በጦርነቱ ላይ ድርቁ ተጨምሮ በሁለቱ አገሮቸ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በእኛው ምድር ጭምር የሚደርሰው ሰቆቃ የበረታ ሊሆን ስለሚችል ዓለም ጭምር ሥጋት እየገባው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከራሷ ችግር በዘለለ ድንበር ተሻጋሪ ችግር ተጨምሮባት የበለጠ ሥጋት ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ይጠበቃል። ስለሆነም የቤት ሥራችንን በሚገባ መሥራትና በተለይም የሞላለት ላልሞላለት፣ ሦስቴ የሚበላው የተቸገረ ወገኑን በማገዝ ይህንን ክፉ አጋጣሚ ማለፍ ወሳኙና ቁልፉ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል። መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ፖለቲከኞች ከጦርነት ወጥተው ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ ግፊት መደረግ አለበት፡፡

ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ዛሬም ዋናው ችግር የግብርና ሥራው ኋላቀር ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ደግሞ በየጊዜው ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ተያይዞ የሚገጥሙንን ችግሮች በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቋቋም አያስችልም፡፡ ሕዝቡን ከድህነት የሚያላቅቅ በሒደትም የበለፀገ አገር ለመገንባት የሚያስችልና የግብርና ልማትን የሚያፋጥን ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ፣ በሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ወሳኝ ዕርምጃ ሊታይ ይገባዋል፡፡ መንግሥትም ለግብርናና ገጠር ልማት ሥራዎችና ለገጠሩ ኅብረተሰብ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ቢመስልም፣ በዕቅድና በፍላጎት እየተሠራ አይመስልም።

የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂው ያለንን የልማት አቅም ማለትም ከፍተኛ የሰው ጉልበት፣ መሬት፣ ውኃና ውስን ካፒታል በቁጠባ ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን መዘንጋት ለእንዲህ ያለ አደጋ ከሚያጋልጡን ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑን ተገንዝቦ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመሥራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከር፣ የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን ዘላቂነት ያለው መፍትሔ ነው፡፡ ይህንን ችላ ብሎ ባልተገባ ጉዳይ ላይ መዳከርም ሆነ አምራቹን ኃይል ጦርነት ውስጥ መማገድ ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ድርቅ የፖለቲካ ችግራችንን እንዳያባብስ ይታሰብበት!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...