Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ከተወዳጆቹ ዕድሜ ጠገብ አገራዊ አባባሎቻችን መካከል ‹‹ምከረው ምከረው እንቢ ካለ መከራ ይምከረው›› የሚለው ቀልቤን ይስበዋል፡፡ ምክር በቤተሰብ፣ በቤተ ዘመድ፣ በጎረቤት፣ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው፡፡ ምክር መስጠት ብቻ ሳይሆን መቀበልን መልመድም እንዲሁ፡፡ የምክር ነገር ሲነሳ ‹‹ምክር ለሰጪው እንጂ ለተቀባዩ ከባድ ነው›› የሚል አባባልም አለ፡፡ ለዚህም ነው መካሪም ሆነ ተመካሪ በሥርዓት ሲነጋገሩ ግለሰባዊም ሆኑ ማኅበረሰባዊ ስብራቶች የሚጠገኑት፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካይነት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ስትዘጋጅ፣ በጎን እያፈተለኩ የሚያስቸግሩ ፖለቲካዊ እንከኖችም መላ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ መታሰብ አለበት፡፡ በዚህ ስሜት ላይ ተመርኩዤ አንዳንድ ገጠመኞቼን አቀርባለሁ፡፡

ወጣትነት ለሁላችንም ከባድ ጊዜ እንደሆነ ማንም አይስተውም፡፡ በወጣትነታችን ወቅት ለእኛ ሁሉም ነገር ቀላል መስሎ ስለሚታየን ለአጉል ጀብደኝነት የምንጋለጥባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በወጣትነታቸው ጊዜ የተረጋጉና በማስተዋል የሚራመዱ መኖራቸው አይካድም፡፡ ነገር ግን ብዙኃኑ ወጣቶች በአፍላነታቸው ጊዜ ሁሉንም ነገር መሞካከር ስለሚፈልጉ ከብዙ ነገሮች ጋር ይጋጫሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው አንጋፋዎች በምክር እንዲያግዟቸው ጥረት የሚደረገው፡፡ ‹‹ወይፈን ማረስ የሚችለው ከነባሩ በሬ ጋር ሲቀናጅ ነው›› እንደሚባለው፣ አንጋፋዎች ወጣቶችን የማገዝና የመምከር ኃላፊነት አለባቸው ማለት ነው፡፡

እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በምማርበት ወቅት፣ አብሮኝ ይማር የነበረ በዕድሜ ጠና ያለ በመምህርነት ያገለገለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው ከሐረር መምህራን ማሠልጠኛ በዲፕሎማ ተመርቆ ለስምንት ዓመታት ካስተማረ በኋላ፣ በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ዕድል መሠረት ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሆኖ ነበር የተገናኘነው፡፡ እንደ ጓደኞቼ ብዙ ጊዜ በስሜት እየተገፋሁ አላስፈላጊ ንግግሮችን ስናገርና በቅጡ ያልተረዳሁትን ፖለቲካ ሳቦካ፣ ‹‹አንተ ጎረምሳ ነገ ለፀፀት ሊዳርጉህ ከሚችሉ ነገሮችና የፖለቲካ ውዝግቦች ተቆጠብ፡፡ ባልበሰለ ጭንቅላት ከየትም የተቃረመ ማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም አግበስብሰን አምጥተን ነው አንድ ትውልድ አልቆ አገራችንን ከል ያለበስናት፡፡ ከአንተ ታላቆች ብዙዎቹ በቀይና በነጭ ሽብር አልቀዋል፡፡ በጣም ብዙዎቹ በየእስር ቤቱ ተወርውረው እየተሰቃዩ ነው፡፡ የተቀሩት ደግሞ አስፈሪ በረሃ እያቋረጡ ለስደት ተዳርገዋል…›› እያለ ሲገስፀኝ መለስ እል እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡

ለብዙዎቹ ጓደኞቼ የእዚህን የቀድሞ መምህር የአሁኑን የክፍል ተማሪ ምክርና ተግሳፅ ስነግራቸው አይሰሙም ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ለጊዜው በሐሳቡ ቢስማሙም ቆየት ብለው ግን ሁሉንም ነገር ረስተው የተለመደው የጉርምስና እልህ ውስጥ እየገቡ ተጎድተዋል፡፡ ኮተቤ ስንማር በሰላዮች መረጃ መሠረት እየታፈኑ የተወሰዱ ብዙ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንደ አዲስ የኢሕአፓ እንቅስቃሴ እያገረሸ ነው እየተባለ ሲሆን፣ በስሜት ተሞልተው በኢሕአፓ ጉዳይ የሚብከነከኑ በርካታ ተማሪዎች አድራሻቸው ጠፍቶ መቅረቱን አልረሳውም፡፡ የዚያ መምህር ምክርና ተግሳፅ ብዙዎችን በሚገባ የገባቸው ከረፈደ በኋላ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ሁላችንም ሰከን ማለትና አደብ መግዛት የጀመርነው ከአጠገባችን ጓደኞቻችን በኩንቢ ቮክስ ዋገን እየታፈኑ ከተወሰዱ በኋላ ነበር፡፡

ደርግ ወድቆ ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ በቦታው ሲተካ በሰል ብዬ ስለነበር፣ አፍላ ወጣት የሥራ ባልደረቦቼ በደርግ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋልና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከአምባገነንነት አገሪቱ ተላቀቀች በማለት በደስታ ሲቦርቁ አይረሳኝም፡፡ እኔ ራሴ በደርግ ባለሥልጣናትና የአብዮት ጠባቂ በሚባሉ ነፍሰ በላዎች መንኮታኮት ብደሰትም፣ ኢሕአዴግ በፖለቲካ ይፎካከሩኛል ያላቸውን ኢሕአፓና መኢሶን አግልሎ በመሰሎቹ ታጅቦ ሥልጣኑን መቆጣጠሩ አላስደሰተኝም ነበር፡፡ በማይረቡ ሰበቦች ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ተገፍተው በብሔር ብሔረሰቦች ስም የተደራጁ ጩሉሌዎች የበዙባቸው የኢሕአዴግ አጃቢ ድርጅቶች እንደ አሸን መፍላታቸው በጣም ነበር ያናደደኝ፡፡ ለወጣቶቹ ይህንን ሴራ ላስረዳቸው ብሞክርም በወቅቱ ሊገባቸው አልቻለም ነበር፡፡ ይሁንና እየዋለ ሲያድር የሴራ ፖለቲካውን ሲረዱ እንደ መአሕድ፣ ከዚያም መኢአድ፣ ኢዴፓና መሰል ድርጅቶች አባል እየሆኑ፣ በግንፍልተኝነት ብዙዎቹ በእስር ቤት መከራቸውን ማየታቸው አይረሳኝም፡፡ ከስሜት በፊት ብስለት ቢኖራቸው ኖሮ ድርጅቶቹ ጠንካራ መሠረት እንዲይዙ ያግዙ ነበር ባይ ነኝ፡፡

ከዚያም በኋላ በምርጫ 97 ጊዜ ብዙዎቹ በቅንጅት ተሳትፎአቸው ለበርካታ ጊዜያት ከመታሰራቸውም በላይ፣ በእስር ቤት ውስጥ ሳይቀር ለከፍተኛ እንግልትና ሥቃይ ተዳርገዋል፡፡ ከእስር ወጥተው በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎም ተሰቃይተዋል፡፡ እኔ እንኳን በሥራ ዓለም ከማውቃቸው ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ30 በላይ የሚሆኑት በአሜሪካና በአውሮፓ የስደት ሕይወት ይገፋሉ፡፡ ብዙዎቹ ከአገራቸው በኬንያ በኩል ሸሽተው ወጥተው በስደት ተጎሳቁለዋል፡፡ አገር ያስተዳድሩ የነበሩ ሰዎች ምክር መቀበል ባለመፈለጋቸው እንጂ፣ በወቅቱ በበርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች በጣም ብዙ አንጋፋ ምሁራንና የተከበሩ አረጋውያን ከበቂ በላይ መክረዋል፡፡ ሰሚ በመጥፋቱ አገር እንዳትሆን ሆና በመጨረሻም ሕወሓታውያንም ሆኑ አጃቢዎቻቸው ኢሕአዴጋውያን በሕዝባዊ ማዕበል ተገፍተው ተሸኙ፡፡

አሁንም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ሆነ አመራሮቹ ምክር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች አማካሪዎች እንዳሏቸው ቢታወቅም፣ አማካሪዎቹ ይደመጡ ወይም አይደመጡ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ በችጋር እየተቆላ የቱ ከየቱ መቅደም እንዳለበት ብርቱ መካሪ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ሲጠፋ እንዴት መረጋጋት መፈጠር እንዳለበት የሚያማክሩ ያስፈልጋሉ፡፡ ትልልቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና መሰል ውሳኔዎች ላይ ከመደረሱ በፊት በሚገባ የመመካከር አስፈላጊነት አፅንኦት ያስፈልገዋል፡፡ የሰሞኑ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካዊ ነገር ወደ መድረክ ከመቅረቡ በፊት በውስጥ ከብልሆች ጋር የመምከር ተገቢነት መረሳት አልነበረበትም፡፡ ‹‹በፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ›› የሚለውን አገራዊ አባባል በማስታወስ፣ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮቻችን የምክክርን አስፈላጊነት ደጋግሞ ማውሳት ተገቢ ነው እላለሁ፡፡ ‹‹ተማክረው የፈሱት አይሸትም›› እንደሚባለው ለማለት ነው፡፡

(ናኦድ ተሬሳ፣ ከፒያሳ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...