Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን እየተመረጠ የመጣው የኢትዮጵያ ሜዳ ቴኒስ

በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን እየተመረጠ የመጣው የኢትዮጵያ ሜዳ ቴኒስ

ቀን:

በዓለም ከሚዘወተሩ ስፖርቶች መካከል የሜዳ ቴኒስ ይጠቀሳል፡፡ የኦሊምፒክ ስፖርት የሆነው የሜዳ ቴኒስ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሣይ የተጀመረ ሲሆን፣ ዘመናዊው የቴኒስ ጨዋታ የተጀመረው በእንግሊዟ በርሚንገሃም እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ቴኒስ በኢትዮጵያ በመጀመሪያ የተዋወቀው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን (1881-1909) በፈረንሣይ የምድር ባቡር ሠራተኞች አማካይነት እንደሆነ፣ በ1930ዎቹ መዘውተር መቀጠሉና ክለብም መቋቋሙ ይወሳል። በጊዜ ሒደትም በተለያዩ ዓበይት ከተሞች ቴኒሱን በግል ሆነ በቡድን የሚያዘወትሩ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

 በኢትዮጵያ የሜዳ ቴኒስ በፌዴሬሽን ደረጃ የተቋቋመው በ1972 ዓ.ም. በስፖርትና የአካል ማሠልጠኛ ኮሚሽን አማካይነት እንደሆነ ይወሳል፡፡

የሜዳ ቴኒስ በሀብታሞች ብቻ እንደሚዘወተር ቢጠቀስም በሁሉም የዕድሜ ክልል ይዘወተራል፡፡ ቴኒስ የሀብታም ስፖርት ተደርጎ የሚወሰድበት ምክንያት የቴኒስ መጫወቻ ቁሳቁሶች ውድ በመሆናቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተር ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአኅጉርና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የሚካፈሉ አትሌቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በቅርቡም የኢትዮጵያ ቡድን ከ25 ዓመታት በኋላ በኮንጎ ኪንሻሳና ሩዋንዳ በተዘጋጀው የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮና ላይ መካፈል ችሏል፡፡

ከዚህም ባለፈ ቴኒስን በአገር አቀፍ ደረጃ በወጣቱ እንዲዘወተርና እንዲስፋፋ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴኒስ ፈዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታምራት በቀለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስፖርቱን ለተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የአሠልጣኝነትና የዳኝነት ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ይናገራሉ፡፡ በተለይ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች የማዘውተሪያ ሥፍራና የገንዘብ አቅም ስላላቸው፣ ቴኒሱን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናው በክልሎችና በትምህርት ቤቶች እየተሰጠ እንደሚገኝ የሚያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ ፕሮጀክት ተቀርፆ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ አርባ ምንጭና አዳማ  እየተሠራ መሆኑ፣ በተለይም በአዲስ አበባ በአራት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚሆን ፕሮጀክት ከዓለም አቀፉ የሜዳ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር በመቅረፅ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

‹‹ስፖርቱን በደንብ ተገንዝበውና ተረድተው ከሚያዘወትሩት ባሻገር፣ ሌሎቹም ወደ ስፖርቱ እንዲመጡ ቅስቀሳ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አቶ ታምራት ያክላሉ፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ቴኒስ ፌዴሬሽን ዓይን ውስጥ መግባቷ የተጠቆመ ሲሆን፣ በ2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ሁለት ዓለም አቀፍ ውድድሮች አዲስ አበባ ላይ ማስተናገድ ችላለች፡፡

በውድድሩ ከ30 በላይ አገሮች የተወጣጡ ወጣቶችና አዋቂዎች ተሳትፈውበታል፡፡ እንደ አቶ ታምራት ማብራሪያ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሩን በብቃት ማስተናገድ በመቻሏ ውድድሩን ዘንድሮም በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ ዕድል ተሰጥቷታል፡፡

ኢትዮጵያ ውድድሩን ማስተናገዷ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉበት   ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህም ውድድሩ በግል የሚደረግ በመሆኑ ወደ ውጭ አገር አምርተው በርካታ ገንዘብ ከማውጣት እንዳዳናቸው ተጠቁሟል፡፡

በዓምናው ውድድር 14 ወጣት ኢትዮጵያውያን መካፈል ብቻ ሳይሆን ጥሩ ነጥብ መሰብሰብ የቻሉበት መሆኑም ተወስቷል፡፡

‹‹ውድድሩ ቴኒስን ከማነቃቃቱም በላይ፣ ወጣቶች ወደ ስፖርቱ የበለጠ እንዲመጡ ትልቅ አጋጣሚ መፍጠር ችሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር በውድድሩ ለመካፈል ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ተሳታፊዎች የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ አስችሏል፤›› ሲሉ አቶ ታምራት ያብራራሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ውድድሩ የቱሪዝም ዕድል ከመክፈቱ በዘለለ ለገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ቴኒስ ከአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል  ስላልደረሰ፣ ግንዛቤ በመስጠት እንዲዳረስ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ የመጫወቻ ሜዳዎች በተለያዩ ሥፍራዎች እንዲገነቡ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

‹‹በእርግጥ ፌዴሬሽኑ በሁሉም ሥፍራ የማዘውተሪያ ቦታ የመገንባት አቅም የለውም፡፡ በአንፃሩ ከዓለም አቀፍ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያሠራጨን እንገኛለን፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ ያክላሉ፡፡

የዓምናውን ዓለም አቀፍ የቴኒስ ውድድር ከፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር ያስተናገደው አብደላ ኢቨንትስ ድርጅት ነው፡፡ አብደላ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ሆኖ በተለያዩ አገሮች መወዳደር ችሏል፡፡

ከውድድሩ በኋላ ከተሳታፊዎች የተገኘው ምላሽ አስደሳች እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ ታምራት፣ ሁሉም ተወዳዳሪዎች በዝግጅቱ ደስተኛ እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ ውድድር የማሰናዳት አቅሟን ማሳየት የተቻለበት አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴኒስ ያላት ስም እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽንና ከአፍሪካ ቴኒስ ኮንፌዴሬሽን ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩንም በማመልከት ጭምር፡፡

‹‹ቴኒስ በወጣቶች ብቻ ታጥሮ መቆየት አለበት የሚል ሐሳብ የለንም፡፡ ስፖርቱ በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ እንዲዘወተር አስፈላጊውን ሁሉ መደረግ ይኖርበታል፤›› በማለት አቶ ታምራት ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ በ33 ዩኒቨርሲቲዎች የቴኒስ ሜዳዎች መኖራቸውን የሚያነሱት ፕሬዚዳንቱ፣ እነዚህ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ መድረኮቹም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴኒስ ውድድሮች መካፈል የሚችሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚያስችሉ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...