Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን የሚመጥናት በሕግና በሥርዓት መተዳደር ነው!

ወትሮም በሰላም ዕጦት፣ በድርቅና በድህነት አዘቅት ውስጥ በሚንፈራገጠው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ አንፃራዊ ሰላሟ ጠፍቶ በሥጋት መኖር ከተለመደ ሰነባብቷል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ ከሚገኙ አገሮች ከኬንያ በስተቀር ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ሰላም የላቸውም፡፡ ሱዳን አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ገብታ መውጫው ከጠፋት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን ከእርስ በርስ ጦርነት መውጣት አቅቷት ውሉ ያለየ ችግር ውስጥ ነው የምትኖረው፡፡ ሶማሊያ በሁለት እግሩ መቆም ባቃተው መንግሥት እየተመራች አልሸባብ እንዳሻው እየፈነጨባት ነው፡፡ ጂቡቲ አንፃራዊ ሰላም ቢታይባትም ተፃራሪ የሆኑ የኃያላን አገሮች ጦር ሠፈር መሆኗ ለአካባቢው ከፍተኛ ሥጋት ነው፡፡ ኤርትራም ብትሆን ለሦስት አሠርት ዓመታት ከየመን፣ ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ ጋር በመጋጨት የምትታወቅና አሁን ያለው ሥርዓት በአካባቢው አገሮች ጭምር በሥጋት የሚታይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የሩቅ ዘመኑ ቢቀር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን የአገሪቱ ክፍሎች ከተካሄዱና እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ጥቃቶች ሳቢያ ሰላም ከራቃት ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ወጣ ሲባል ደግሞ በቅርቡ በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በሐማስ መካከል የተጀመረው አውዳሚ ጦርነት፣ በአካባቢውና በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከቷል፡፡ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ በርካታ ንፁኃንን ከጨፈጨፈና ካገተ በኋላ፣ እስራኤል በበቀል ተነስታ ጋዛ ከተማ ውስጥ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመችው ያለችው የጅምላ ጭፍጨፋ አሰቃቂ ሆኗል፡፡ ባለፈው ሰሞን ጋዛ ውስጥ በሆስፒታል ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት ከ500 በላይ ፍልስጤማውያን ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ እስራኤል በአውሮፕላን ጥቃቱን ፈጽማለች ተብሎ ብትወነጀልም፣ ጥቃቱን የተፈጸመው ዒላማውን በሳተ የሐማስ ሮኬት ነው ብላ አስተባብላለች፡፡ ያም ሆነ ይህ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሱ የጦር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ንፁኃን እያለቁ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አደገኛ አካሄድ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ መካከለኛው ምሥራቅ ብቻ ሳይሆን፣ በአካባቢው በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ አገሮች ጭምር የገፈቱ ቀማሽ ሊሆኑ እንደሚችሉ አይጠረጠርም፡፡ የባህር መተላለፊያዎችም ሊዘጉ ይችላሉ፡፡

በሰላም ዕጦት እየተሰቃዩ ያሉ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ብቻ ሳይሆኑ አንፃራዊ ሰላም ያላቸው ጭምር ካልተባበሩ፣ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሲታወክ አካባቢው የሽብርተኞች መናኸሪያ ሊሆን እንደሚችል በዓለም ታዋቂ የሆኑ የፖለቲካ ጠበብት ያሳስባሉ፡፡ ሽብርተኞች ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ደካማ ጎኖችን በመጠቀም አገሮቹ ውስጥ ያሉ ብሶተኞችን መረባቸው ውስጥ በመክተት፣ ድንገት ሳይታሰብ በበርካታ ሥፍራዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት በመክፈት ትርምስ መፍጠር ይችላሉ፡፡ በተለይ ለዓመታት ሰላም ባጡ አገሮች ውስጥ የስለላ መረባቸውን በስፋት በመዘርጋት የሚፈልጉትን ዓላማ ለማስፈጸም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በአካባቢው ተደማጭነት በማግኘት ዘለቄታዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚፈልጉ አገሮች፣ የፋይናንስና የወታደራዊ ድጋፎችን በማጠናከር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ለማዳከም ያደባሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብ አንዱ መነሻ ሰበብ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት ሰላም ማስፈን አቅቶ አለመረጋጋቱ ሲቀጥል፣ የታሪካዊ ጠላቶች አንዱ ተግባር የማፈራረስና የማጨራረስ ስትራቴጂያቸውን በረቀቀ መንገድ ማከናወን ነው፡፡ የእርስ በርስ መስማማት ጠፍቶ ውድመቱና መጋደሉ ሲቀጥል ታሪካዊ ጠላቶች ይመቻቸዋል፡፡

‹‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል›› እንደሚባለው ለበርካታ አገሮች ሰላም አስከባሪ በመሆን በዓለም የታወቀችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ሰላም ርቋት ልጆቿ በከንቱ ፖለቲካ እርስ በርስ ሲባሉ ከማየት በላይ የሚያም ምንም ነገር የለም፡፡ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የተለኮሰው አዲሱ አውዳሚ ጦርነት ራሱን እያስፋፋ አፍሪካ ቀንድ እንደማይደርስ መተማመኛ በሌለበት ሁኔታ፣ ትንሽ እንኳ ደንገጥ በማለት አገር ውስጥ ያለውን እሳት ለማጥፋት ነቅነቅ አለማለት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ለአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌትና አርዓያ የነበረች አገር በዙሪያዋ እሳት እየተንቀለቀለ ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ በመሸበብ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› በሚል ተምኔታዊ ማዘናጊያ እንደ ሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ ተደብቆ ማምለጥ አይቻልም፡፡ ትናንት ከሰሜኑ አውዳሚ ጦርነት በተዓምር ተርፋ አንፃራዊ ሰላም ልታገኝ ነው ተብሎ ተስፋ የተደረገባት ኢትዮጵያ፣ ተመልሳ እዚያው የጥፋት አረንቋ ውስጥ ስትገኝና የሰላም ዕጦቱ ሲባባስ ጨከን ተብሎ በመወቃቀስ መፍትሔ መፈለግ የኢትዮጵያውያን ድርሻ እንጂ የማንም ሊሆን አይችልም፡፡ አለበለዚያ ግን በጥፋት ማዕበል ተጠራርጎ መወሰድ ይከተላል፡፡

የኢኮኖሚው ዕምቅ አቅም ጥቅም ላይ ውሎ ምግብ በአግባቡ ማግኘት የተሳነውን ሕዝብ ከከፋ የኑሮ ውድነት ማላቀቅ የሚቻለው፣ በሁሉም የሙያ መስኮች በቂ ዕውቀትና ልምድ ከሥነ ምግባር ጋር ያካበቱ ኢትዮጵያውያን በፖሊሲና በስትራቴጂ ዕቅዶች ተሳታፊ በማድረግ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በውስጣዊ መረጋጋት መጥፋት ሳቢያ በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ጉዳት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ተባብሶ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በምግብ፣ በማዳበሪያ፣ በነዳጅና በሌሎች ሸቀጦች ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በሕዝባችን ላይ ኑሮ ላይ መከራ ነው የጫነው፡፡ የብር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ መጠን መዳከም የራሱን አሉታዊ ጫና አስከትሏል፡፡ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ይረዳሉ በማለት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ጥረት እያደረግኩ ነው ቢልም፣ የኑሮ ውድነቱ እየባሰበት እንጂ መረጋጋት ማሳየት አልቻለም፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የሰሞነኛው የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ጦሱ ስለሚያስፈራ፣ ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸው ባለሙያዎች እንዲታደጓት ቢደረግ መልካም ነው፡፡

ከኢኮኖሚው በመለስ በተለያዩ ዘርፎችና መስኮች ለሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ተቋማዊ መፍትሔዎች ሊገኙ የሚችሉት፣ ከፖለቲካዊ ውሳኔዎች በፊት በዕውቀት ላይ ለሚመሠረቱ ጥናቶችና ምርምሮች ቅድሚያ ሲሰጥ ነው፡፡ በየመስኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ ዕውቀትና ልምድ ከሥነ ምግባር ጋር የተጎናፀፉ ኢትዮጵያውያን ሲፈለጉ፣ በደመነፍስ የሚመሩ መንግሥታዊ ተቋማት ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ እንደገና ሊዋቀሩ ይችላሉ፡፡ የሙያ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሲመሩዋቸውና ለአንድ ኃላፊነት ትክክለኛው ሰው ሲሾም ወይም ሲመደብ፣ ተቋማቱ ዘመኑን የሚዋጁ ሆነው በሥርዓት ተግባራቸውን መወጣት ይችላሉ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ፣ በአፍሪካ አኅጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተመራጭና ተፈላጊ መሆን የሚቻለው በሕግና በሥርዓት የምትተዳደር አገር ስትኖር ነው፡፡ የትም ሥፍራ ግጭት ሲያጋጥም በጊዜ ምላሽ የመስጠትና የማረጋጋት ሥራ ማከናወን ከመቻሉም በላይ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል ቅራኔና ግጭት የሚፈጥሩ አድሎአዊና ብልሹ አሠራሮችም ተነቅለው ይወገዳሉ፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙም በሥርዓት መነጋገርና መፍትሔ ማበጀት ባህል ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያን የሚመጥናት በሕግና በሥርዓት መተዳደር እንደሆነ ይታወቅ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...