Sunday, July 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዳበሪያ ግዥ ለማፋጠን የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቦርድ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዳበሪያ ግዥ እንዲፋጠን ለማድረግ የመንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቦርድ ሙሉ በሙሉ ለውጥ እንደተደረገበት ተገለጸ፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በወቅታዊ የግብርና ጉዳዮች ላይ ዓርብ ጥቅምት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኮርፖሬሽኑን ቦርድ እንደ አዲስ ማቋቋም ያስፈለገው በፊት በማዳበሪያ ግዥ ላይ የፍላጎት ማሰባሰብና ጨረታ የማውጣቱ ሒደት ከፍተኛ ጊዜ ስለሚወስድ ነበር ብለዋል፡፡

በሪፎርሙ መሠረት ለማዳበሪያ ግዥ የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርቡ፣ ኤልሲ የሚከፍቱ፣ እንዲሁም ትራንስፖርት የሚያቀርቡ ተቋማት አመራሮች ወደ ቦርዱ እንዲመጡ መደረጉን ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው የማዳበሪያ ግዥ አሠራር በኮርፖሬሽኑ ጨረታ ከወጣ በኋላ የግብርና ሚኒስቴር ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ አዲሱ ቦርድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ውሳኔ መስጠት እንዲችል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት የ2016 የበጀት ዓመትን ጨምሮ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለግዥ ሥርዓት የሚያስፈልገው የፍላጎት ማሰባሰብ ሥራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት 23 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ግርማ (ዶ/ር)፣ ከ2015 በጀት ዓመት አንፃር የዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ አለው ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የማዳበሪያ ግዥ የሚፈጸመው የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተት እንዲመጣጠን ለማድረግ መሆኑን፣ ግዥውን ለመፈጸም እንዲያግዝ የግብርና ሚኒስቴር የማዳበሪያ ግዥ መመርያ ማሻሻሉን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ለ20 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረ የግዥ መመርያና ሒደት፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ እንዲቀየር መደረጉን አስታው      ቀዋል፡፡

መመርያው በቀጥታ ግዥና መንግሥት ለመንግሥት በሚደረጉ የዲፕሎማቲክ ግንኙነቶችን መሠረት ያደረገ አሠራር እንደሚገኝበት ገልጸዋል፡፡

መመርያው ከፍላጎት አሰባሰብ ጀምሮ ቀድሞ የመዝሪያ ወቅቶችን ታሳቢ በማድረግ፣ የሦስት ዓመታት ማዳበሪያ ፍላጎት ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ግርማ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በመመርያ ለውጡ አማካይነት ማዳበሪያ ከሚያመርቱ ከአምራቾች ጋር በመገናኘት ያለ ምንም ጨረታ በቀጥታ ባለፈው ዓመት ከተገዛበት በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ማዳበሪያ የራሱ የሆነ ወቅታዊ የዋጋ ልዩነቶች ስላሉ እንደ ቻይናና ኢንዶኔዢያ ያሉ አገሮች ከፍተኛ የማደበሪያ ግዥ በሚፈጽሙበት ወቅት ገበያው ይረበሻል፡፡ በዚህ ወቅት በጨረታ ሒደት ጊዜ በማባከን ግዥ ሲፈጸም በከፍተኛ ዋጋ ለመግዛት እንገደድ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ተግባራዊ በሆነው መመርያ መሠረት የአንድ ዓመት ቀጥታ የማዳበሪያ ግዥ በዓለም ላይ ትልቁ የማዳበሪያ አምራች ከሆነው የሞሮኮ ኩባንያ ኦሲፒ መገዛቱን ገልጸዋል፡፡

መመርያው ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ከኦሲፒ ጋር የተገባው ውል በፊት በአንድ ቶን 650 ዶላር ይገዛ የነበረውን ኤንፒኤስ ማዳበሪያ በ500 ዶላር በመግዛት፣ በመንግሥት ላይ የተፈጠረው የድጎማ ጫና መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ዩሪያ የተገዛበት ዋጋ፣ በፊት ከነበረው በአንድ ቶን ከ680 እስከ 700 ዶላር ዋጋ በመቀነስ፣ ዘንድሮ በአንድ ቶን ከ400 እስከ 430 ዶላር መግባት ተችሏል ብለዋል፡፡

አፈጻጸምን በተመለከተ በአንዳንድ ቦታዎች ማዳበሪያን በመጋዘን በማከማቸት በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ከማሠራጨት አኳያ ክፍተት መፈጠሩን፣ ግርማ (ዶ/ር) በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለመስኖ ሥራ የሚያስፈልጉ አምስት ኤልሲዎች ተከፍተው የመጀመሪያው መርከብ ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ በመጫን ጂቡቲ ወደብ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡

በ2016 ምርት ዘመን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ላይ በማልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ በሩብ ዓመት ውስጥ በኦሮሚያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በአማራ፣ እንዲሁም በሰባት ዞኖችና በ16 ሥፍራዎች 41.3 ሚሊዮን የሚገመት የግሪሳ ወፍ ተከስቷል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች