በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የተበላሸ ብድር መጠን በመያዝና ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ በማስመዝገብ ይወድቃል ተብሎ ነበረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የተበላሸ የብድር መጠኑን ወደ ሰባት በመቶ ማውረዱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በጋራ እንዳመለከቱት፣ ከአራት ዓመታት በፊት ባንኩ በኪሳራ ውስጥ ገብቶ ህልውናው አደጋ ላይ የነበረ ቢሆንም፣ የባንኩ ታሪክ ተቀይሮ የተበላሸ ብድሩን ማውረድ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አትራፊ ከሚባሉ ባንኮች መካከል አንዱ መሆን ችሏል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔ ከ40 በመቶ በላይ ደርሶ የነበረ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፣ ‹‹አሁን ግን ይህንን የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 7.1 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ ይህም ለልማት ባንክ ከተቀመጠው የተበላሸ ብድር መጠን ጣሪያ 15 በመቶ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ አፈጻጸም መሆኑን የሚያመለክት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ተገኘወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባንኩ ከኪሳራ ወጥቶ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተከታታይ የሆነ ትርፍ እያስመዘገበ ለመምጣቱ አንዱ ተጨባጭ ማሳያ፣ በኪሳራ ቆይቶ በ2015 የሒሳብ ዓመት ብቻ ከታክስ በፊት 6.5 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ገብቶበት ከነበረው ችግር የወጣው በብዙ ርብርብና ጥረት መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በምሳሌነት እንዲጠቀስ አስችሎታል ብለዋል፡፡
ባንኩ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ባስጀመረበት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የገንዘብ ሚኒስቴር ደኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ባንኩ አስመዝግቤያለሁ ያለው ውጤት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹ልማት ባንክ ተጋርጦበት ከነበረው የህልውና አደጋ በመንግሥት በተወሰዱ ቆራጥ ዕርምጃዎች ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የሚባል ውጤት ያስመዘገበው በአመራሮቹና በሠራተኞቹ ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ በዚህ ሒደት ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድን ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አመልክተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ቡድኑ ድጋፍ በተለየ ሁኔታ የሚታይ የነበረ መሆኑንና በወቅቱ ባንኩ ለገባበት ችግርና በነበረው የፖለቲካ ተፅዕኖ ሙሰኛ ኃላፊዎችና ተበዳሪዎች የሚያደርጉትን ጫና ለመቋቋም የማክሮ ቡድኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው በማለት ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ገብቶበት የነበረው ችግር ቀላል እንዳልነበረ ያወሱት ተገኘወርቅ (ዶ/ር)፣ ከተባላሸ ብድር ባሻገር የተከታታይ ዓመታት ኪሳራው ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይህም ኪሳራ 7.5 ቢሊዮን ብር የነበረውን የባንኩን ካፒታል በ2010 በጀት ዓመት ወደ ሁለት ቢለዮን ብር እንዲወርድ አስገድዶት እንደነበርም አመልክተዋል፡፡
መንግሥት የባንኩን ዳይሬክተሮች ቦርድ እንደገና በማዋቀር ኃላፊነት ከወሰደ በኋላ፣ ባንኩ የነበሩበትን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተለይም የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድና አዲስ ቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ በመግባቱ፣ ዕመርታዊ ውጤት ሊያስመዘገግብ መቻሉንም የቦርድ ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡
ይህ ማለት ግን የነበሩ ችግሮች መቶ በመቶ ተወግደዋል ማለት እንዳልሆነና ፈተናዎች መልካቸውን እየቀያየሩ ስለሚመጡና አዳዲስ በላተኞችና ሙሰኞች ስለሚፈለፈሉ፣ የባንኩ ማኔጅመንትና ሠራተኛ በጥናትና በትጋት መሥራት እንደሚገባቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
ባንኩ ለሚያቀርበው የልማት ብድር የሚረዳ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖረው በተደረገው ከፍተኛ ጥረት በመንግሥት ፀድቆ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ፣ የልማት ባንክን ቦንድ ለማሳተም የሀብት ማሰባሰብ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህም ከተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ከፍተኛ የብድር ጥያቄዎችንና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ የማድረግ አቅም የሚፈጥርለት መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡
ባንኩ አሁን የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር) ሁለት ቢሊዮን ብር የነበረውን ካፒታሉን 38 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የሆነው መንግሥት ለባንኩ ያደረገውን 21.8 ቢሊዮን ብር ጨምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገኘው ትርፍ ታክሎበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የባንኩ የሀብት መጠንም ከ80 ቢሊዮን ብር ወደ 160 ቢሊዮን ብር ማደጉንም ዮሐንስ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡